ታላቁ ሰው በጥበብ ታዛ

 የእውቀትና የጥበብ ላምባ ለኩሰው፣ የኢትዮጵያን የሥነ ጽሑፍ ዓለም ዞረዋታል ለማለት ከሚያስደፍር ልዩ ተሰጥኦ ጋር ተወልደው፣ ኖረውና እንደ ኦሪዮን ኮከብ የሚያበሩ ሥራቸውን አኑረውልን ሄደዋል። ታላቁ ኢትዮጵያዊ የክብር ዶክተር ከበደ ሚካኤል። የተሰጥኦ ገጸ በረከቶቻቸው በርካታ ናቸው። የቅኔና የሥነ ጽሁፍ ሊቅ፣ ደራሲና ተርጓሚ፣ የፍልስፍና ሃዲድ፣ የፖለቲካው ጀንበር ወዘተ.. የቀለም እውቀትን በጥበብ ብሩሽ በመንከር የኢትዮጵያን ሥነ ጽሁፍ ህብረ ቀለማዊ ለዛና ውበት አጎናጽፈውታል። በኢትዮጵያ የሥነ ጽሁፍ ታሪክ ውስጥም ስማቸው ገኖ ከትላንት እስከ ዛሬ፣ ከዛሬ ወዲያ ማዶም ቢሆን ከፍ ብለው ከሚታዩት መካከል አንደኛው እኚሁ ታላቅ ሰው ስለመሆናቸው አያጠራጥርም።

የታላቁ ሰው የሕይወት ጉዞም ከጥቅምት 23 ቀን 1909 ዓ.ም ከደብረ ብርሃን ከተማ ይጀምራል። እለቱ የክብር ዶክተር ከበደ ሚካኤል ወደዚህች ዓለም የተቀላቀሉበት ነው። የሕይወት ዓለም ንጋታቸው ነግታ እንደ ማለዳ ጀምበር ጉዞዋን ስትጀምር ከበደ ሚካኤል ወደ ቤተ ክርስቲያን ደጅ በመዝለቅ የቤተ ክህነት ትምህርታቸውን መከታተል ጀመሩ። ካገባደዱ በኋላም ፊታቸውን ወደ ዘመናዊ ትምህርት አዞሩ።

የዘመናዊ ትምህርት ለመከታተልም ከትውልድ ቀዬአቸው ወደ አዲስ አበባ መጡ። ከዚያም በአሊያንስ ፍራንሲስ የዘመናዊ ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ተማሩ፣ እውቀትንም ሸመቱ። ተማሪ በነበሩበት ወቅት ከመምህራኖቻቸው የሚያገኙት እውቀት ብዙ ቢሆንም ለእርሳቸው ግን ይህ ብቻ በቂ አልነበረም። ከሀገር ውስጥና ከውጭ በርካታ መጽሐፍትን አገላብጠዋል። ከፍልስፍናው እየጨለፉ፣ ከመንፈሳዊውም እየቀዱ የእውቀት ረሃብ ጥማቸውን ለማርካት ይታትሩ ነበር። ቋንቋ የእውቀት መግቢያ በራቸውን አልዘጋውም። የግሪክ፣ የሮማውያን፣ የፈረንሳይ፣ የጀርመን፣ የሩሲያ እና የሌሎችንም ሀገራት ፀሐፊያንን መጽሐፍት በማንበብ የጥበብ ቤታቸውን በ26 ልዩ ልዩ መጽሐፍት ውስጥ በስብጥር ወራጅ ማገር ሰርተውታል። በጊዜ ርዝመት የማያረጅ፣ የማይዘምና የማይፈርስ የእውቀትና የጥበብ ጎጆ ከእርሳቸው በኋላ ላለው ትውልድ በሙሉ መጠለያ ሆኗል።

ከተሰጣቸው ተሰጥኦ አንዳችም ሳያጎድሉ ሁሉንም በየፈርጁ አድለውናል። ከእያንዳንዱ ስጦታዎች መሃከል ለአብነት ያህልም፣ ከግጥም ሥራዎች፤ ብርሃነ ህሊና፣ የቅኔ አዝመራ፣ የቅኔ ውበት፣ የድርሰት ስልጣኔ… ከድርሰት ሥራዎች ደግሞ፤ የትንቢት ቀጠሮ፣ ሐኒባል፣ ካሌብ፣ አክአብ፣ ቅዱስ ገብርኤል በምድረ ገነት… ከታሪክ፤ ግርማዊነታቸው በአሜሪካ ሀገር፣ የኢትዮጵያ የጥንት ስልጣኔ የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው ሥራዎቻቸው በብዛት ቅኔ አዘል ሆነው ቀለል ባሉ ቃላት ከውስጠ ህሊና የሚሰርጹ ናቸው።

ውስብስብ ሃሳቦችን ለመረዳት በሚያስችል መልኩ የፍልስፍና አውድ የያዙ ሃሳቦችን በምናባዊ ምስል ያስመለክቱናል። ከእነዚህም አንደኛው የሾላ ፍሬና የዱባ ፍሬ ነው። ፍልስፍናን ከቅኔ ጋር አዋህዶ የያዘ የግጥም ሥራ ነው። የግጥሙን የሃሳብ ዳራ ለመመልከት ያህል እነዚህን ስንኞች እንመልከታቸው።

 አንዱ ባላገር ሰው ከገበያ ውሎ፣

ሲመለስ ቢደክመው በፀሐይ ቃጠሎ፣

ከሾላ ዛፍ ጥላ ሄደ ተጠግቶ፣

አየ ከነፍሬው ዛፍ ሾላ አፍርቶ።

 ከሾላው አጠገብ ትንሽ እልፍ ብሎ፣

አስተዋለ ደግሞ የዱባ እንጨት በቅሎ፣

ያንዱን ፍሬ ካንዱ መዝኖ አስተያይቶ፣

እንዲህ ሲል ፈረደ በአምላክ ሥራ ገብቶ፣

እውነትም ፈጣሪ ዓለምን ዘርግቶ፣

ሁሉን በየፊናው ሲሰራው አስማምቶ።

የተፈጠሩ እለት እነዚህ ሁለቱ፣

በጣም ተሳስቷል ባለመመልከቱ።

የሾላ ዛፍ ትልቅ ተራራ የሚያህል፣

ፍሬው በጣም ትንሽ ጠጠር የምትመስል፣

የዱባ እንጨት ሽቦ መሬት የሚጎትት፣

ፍሬው ጉልቻሮ ተወዝፏል መሬት።

ለትንሹ ትልቅ ለትልቁ ትንሽ፣

አዘዋውሮ ሰጥቶ እንዲህ ከሚያበላሽ፣

ሾላውን አውርዶ ዱባው ላይ ቢጥለው፣

ዱባውን አውጥቶ ሾላው ላይ ቢሰቅለው፣

ይስማማ ነበረ ሲሆን በየመልኩ፣

ሲያሸክሙትማ መጠኑን ሳይለኩ፣

ያስጠይፍ የለም ወይ ለተመለከተው፣

ዱባ ፍሬው ከብዶት መሬት ሲጎትተው፣

አልገባኝም ከቶ የዚህ ነገር ፍቺ፣

ለምን አደረገው የላዩን እታች?

…………..

 ከበደ ሚካኤል ይጽፉ የነበሩት በሀገር ውስጥ ስላሉ ጉዳዮች ብቻ አልነበረም። በዓለም ታሪክ አዋቂነታቸውም ይታወቃሉ። ከኦሜር ተነስተው እስከ ናፖሊዮን የምናብ አድማሳቸውን አስፍተዋል። ‘ንግስት አግሪፒና’ የተሰኘው ተወዳጅ የግጥም ሥራቸው ይህንኑ ይመሰክራል። ከዚህ ረገድ የሚጽፏቸው ጽሁፎችም ሆኑ የትርጉም ሥራዎች ከአንባቢው ዓይን እየተወነጨፉ አሊያም ከአድማጩ ጆሮ እየሾለኩ ከልብ ላይ ዘልቀው ልብን የሚሰሩ ናቸው። እሳትን በውሃ፣ በረዶውንም በእሳት የማትነን ኃይል አላቸው። የሼክስፒርን ሮሜዎና ዡልየትን እንዲሁም ማክቤዝን በመተርጎም እውቅናን ለማትረፍ ችለዋል። ሌላኛው ተወዳጅ የትርጉም ሥራ ደግሞ ከይቅርታ በላይ የተሰኘው መጽሐፍ ነው።

በግጥም ሥራዎቻቸው በብዛት ማህበራዊ  ጉዳዮችን የሚዳስሱ ቢሆንም ወሰን አልባ ከሆነው ሁለገብ አዋቂነታቸው የተነሳ በብዕር እየቧጠጡ የማይነኳቸው የሃሳብ ዳር ድንበሮች የሉም። ከበደ ሚካኤል በሽታን መርምሮ መድኃኒትን እንደሚያዝ ዶክተር ናቸው። በእጃቸው ብዕር ከመጨበጣቸው በፊት የሃሳባቸውን ስር መሠረት ደህና አድርገው ይመረምሩታል ከዚያም አውጥተውና አውርደው ትክክለኛውን ሃሳብ ያሰፍሩታል።

ሥራዎቻቸው ለትውልድ ፍቱን መድኃኒት መሆን የቻለውም ለዚሁ ነው። ይህችን ሃሳብ ሳነሳ እንዲያው አንዲት የግጥም ሥራቸው ትዝ አለችኝ። በዚህ ግጥም ውስጥ በሁለት የተለያዩ ዓለማት መሃከል እየዋለሉ የሕይወት ፍልስፍናችን ምን አይነት መሆን እንዳለበት ይነግሩናል። ሁሉም ነገር ጊዜና ቦታ አለው። የበዛ ከፍታም ሆነ የበዛ ደግነት ሁለቱም ችግር ማስከተላቸው አይቀርም። ብልጥ ሁን እንደ እባብ፣ የዋህ እንደ እርግብ….

 መርዝም መድኃኒት ነው ሲሆን በጠብታ፣

እንዲሁም ለተንኮል አለው ቦታ ቦታ።

ምን ቢሰለጥኑ ቢራቀቁ በጣም፣

ሁልጊዜ ደጋግመው ብልጠት አያዋጣም።

በእጅ የተበተቡት ተንኮል ዞሮ ዞሮ፣

ማጋለጡ አይቀርም እጅና እግር አስሮ።

መጽሐፉም ይለናል ሲያስተምረን ጥበብ፣

ብልጥ ሁን እንደ እባብ የዋህ

እንደ እርግብ።

ስለዚህ በብልጠት ተንኮል ስትሰሩ፣

በዝቶ እንዳይገላችሁ ገርነት ጨምሩ።

የቅናት በሽታ ህመሙ የከፋ፣

የህሊናን አይኖች ጨርሶ የሚያጠፋ።

በዚህ ክፉ ደዌ የሰው ልጅ ሲለከፍ፣

የተጣራው ነገር ይመስለዋል ሰፈፍ።

ልቡም እያደላ ወደ ክፋት ወገን፣

መሞትን ይመርጣል ሰውን ከማመስገን።

ሕይወት ጦርነት ነው ዋጋህን የሚያሣይ፣

መታገል ግድ ነው ስትኖር ባለም ላይ።

በገዛ እጁ ወድቆ በቁሙ እየሞተ፣

መታገል ያልቻለ ልቡ እየታከተ።

የሚያነሳው የለ በፍቅር በእርዳታ፣

 በዚህች በመሬት ላይ ፍጡር ካልበረታ፣

ጥንቱን አልተሰራም ለሰነፎች ቦታ።

ዓይን የለውም አሉ የሰነፍ ልምና፣

ወደ አምላክ ሲጸልይ ማታ በልቦና፣

መንገዱ ሳይመታኝ ባቡአራ በጭቃ፣

አድርገኝ ይለዋል ላገሬ እንድበቃ፣

እንጦጦ ተኝቼ ሐረር እንድነቃ።

 ከ1934 ዓ.ም እስከ 1962 ዓ.ም ድረስ ያለውን አብዛኛውን ጊዜ በትምህርት ሱባኤ ላይ ነው ያሳለፉት ለማለት ይቻላል። በዚህ ጊዜ ላይ ለአንደኛና ለሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ይሆን ዘንድ ያሰናዷቸው የታሪክ፣ የፍልስፍና፣ የሃይማኖት፣ የቋንቋ፣ የሥነ ግጥም፣ የተውኔትና የተረት መጽሐፍትን ለሀገራቸው አበርክተዋል። ከእነዚህም መካከል ታሪክና ምሳሌ እንዲሁም ብርሃነ ሕሊና፣ ሐኒባል፣ ከይቅርታ በላይ፣ የእውቀት ብልጭታ፣ ጃፓን እንደምን ሰለጠነች፣ ታላቁ እስክንድር እና ታላላቅ ሰዎች የተሰኙት ሥራዎቻቸው የእርሳቸውንም የታላቅነት ልክ የሚያሳዩ ናቸው። እያንዳንዱ ሥራዎቻቸው ውስጥ አንድ ትልቅ ትምህርታዊ ጉዳይ አለ። ‘ሥነ ምግባር’ የሕይወት ፍልስፍናቸውም ከዚሁ የተቀዳ መሆኑን ያሳየናል። በሥነ ምግባር ምሰሶ የታነጹት ሥራዎቻቸው ትውልድን ባማረ መልኩ የመቅረጽ ኃይል አላቸው። በብዛት በትምህርቱ ዘርፍ የነበሩ የሥነ ጥበብ ትምህርቶችም ከእርሳቸው የተቀዱ በመሆናቸው ከ1950ዎቹ ጀምሮ ያለ ተማሪ የእርሳቸውን ሥራዎች በሚገባ አጣጥሞታል። ፋኖስና ብርጭቆ፣ ጽጌረዳና ዳመና የተሰኙት እኚህ ሁለት ግጥሞች በመማሪያ መጽሐፍት ላይ ከታተሙት መካከል ሲሆኑ በብዙ ተማሪዎች አእምሮ ላይ የልጅነት ትዝታ፣ የኋሊዮሽ ትውስታ ሆነው ተቀርጸዋል። ለትምህርት ያዘጋጇቸው መጽሐፍት እንኳንስ ተማሪውንና አስተማሪውንም የሚያስተምሩ ናቸው።

ከበደ ሚካኤል የጥበብና የቀለም ሰው ብቻ አልነበሩም። በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የነበራቸው ሚና ከፍተኛ ነበር። በትምህርት ሚኒስቴር ውስጥ ሚኒስትር ዳይሬክተር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ምክትል ዳይሬክተር፣ የብሔራዊ መጻህፍት ቤት ዳይሬክተር እንዲሁም የካቢኔ ሚንስትር በመሆን አገልግለዋል። ዘመናዊት ኢትዮጵያን ለማደራጀት በተደረገው ትግል በግንባር ቀደምትነት በመሳተፍ ለሀገራቸው ያላቸውን ቆራጥነት አሳይተዋል።

ካበረከቷቸው ሥራዎች ባሻገር ለብዙ የጥበብ ሰዎች መሪ መንገድ መሆን ችለዋል። ከ1950ዎቹ ጀምሮ የተነሱ ደራሲያን አብዛኛዎቹ በከበደ ሚካኤል የሥነ ጥበብ በር የወጡ ናቸው። ሥራዎቻቸው የከበደ ሚካኤልን አይነት ይዘት ያለው፣ ተምሳሌታቸውም ከበደ ሚካኤል ነው።

ሕይወታቸው ከማለፉ ከአንድ አመት በፊት 1990 ዓ.ም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለሀገርና ለሀገር እውቀት ላበረከቱት አስተዋጽኦ የክብር ዶክተሬትን ሰጥቷቸዋል። በተረፈም ከፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ሶቪየት ህብረትና ሜክሲኮ በሰሯቸው ሥራዎች ሽልማትን ለመቀበል የቻሉ ታላቅ ኢትዮጵያዊ የጥበብና የቀለም ሰው ናቸው። መቼም የማይቀር ነገር አይቀርምና የሁሉም ሰው የመጨረሻው ማረፊያ ቃል ሞት ነው። የክብር ዶክተር ከበደ ሚካኤል ኅዳር 3 ቀን 1991 ዓ.ም በተወለዱ በ83 አመታቸው የእረፍት ጉዞ አደረጉ፤ ይህቺን ዓለም ጥለው ነጎዱ። ቅሉ እንዲህ ቢሆንም ነገሩ፤ የጢቢብ ሰው እስትንፋሱ ጥበብ ናት።

በማትሞተው ጥበብ ውስጥ የሚኖር ጠቢብም እንዲሁ አይሞትም። ጠቢብ ሁሌም በሥራው ይኖራል። እኛም እሳቸው በቀለሷት ጎጆ ታዛ ሥር ሆነን ስናስታውሳቸውና ስናመሰግናቸው እንኖራለን።

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን እሁድ ሐምሌ 9 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *