አንዳንዴ “ሁሉም ነገር ድሮ ቀረ” የሚባለው ዝም ብሎ ከሜዳ ተነስቶ አይመስለኝም። ሁሉም ድሮ ቀረ የሚሉ ሰዎች የአሁኑን ዘመን በማጣጣል የድሮውን ናፍቂ ተደርገው የሚታዩበት አጋጣሚ ብዙ ቢሆንም ድሮ ቀረ እንድንል የሚያስገድዱ በርካታ ጉዳዮች እንዳሉ ግን ልብ ማለት አለብን።
ያለፈው ሳምንት በሀገር ደረጃ የዓመቱ የትምህርት ዘመን ተጠናቆ ተማሪዎች የክረምቱን እረፍት የጀመሩበት ነው። ታዲያ በትምህርት መጠናቀቂያ ወቅት በተለይም ሰኔ ሠላሳ ላይ ድሮ የነበረ ግርግርና ድምቀት አሁን የለም። የሰኔ ሠላሳ ወግ ባይኖርም ተማሪዎች ዓመቱን ሙሉ የለፉበትን የትምህርት ውጤት ማየታቸው ሊቀር አይችልም። የውጤት ነገር ሲነሳም ብዙ አስተዛዛቢ ጉዳዮች መታየታቸው እንደቀጠለ ነው። የዛሬው ትዝብቴ ግን ከተማሪዎች ውጤት መጋሸብ ጋር የተያያዘ አይደለም። የውጤት መጋሸብ በአንድ ስሙ ቢያንስ ተማሪዎች ተምረው አግባብ ያልሆነ ውጤት አግኝተዋል ወይም አላገኙም በሚል ሊያከራክር ይችላል። በተቃራኒው ጭራሽ ያልተማሩትን ትምህርት ውጤት ተሞልቶላቸው ማየትን ምን ይሉታል?
ለጊዜው ስሙን የማልጠቅሰው በከተማችን መካከለኛ ከሚባሉ የግል ትምህርት ቤቶች በአንዱ እግር ጥሎኝ ተከስቻለሁ። በዚህ ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ ከሆነው የወንድሜ ልጅ ጋር ሰኔ ሠላሳን ጠብቀን የዓመቱን የትምህርት ውጤት ለመቀበል ነበር ወደ አስኳላ ያቀናነው። ተማሪውን የወንድሜ ልጅ ጥሩ ውጤት ካመጣ ልሸልመው በገባሁት ቃል መሠረት አጠቃላይ ውጤቱን የሚገልፀውን ካርድ ተቀብለን እየተጓዝን በየትኛው የትምህርት አይነት ምን አይነት ውጤት እንዳመጣ አንድ በአንድ መመልከቱን ተያያዝኩት። አንድ ቦታ ላይ ግን ጆሮን ጭው የሚያደርግ ውጤት ከተያያዝነው መንገድ ቆም ብዬ እንዳስብ አደረገኝ። ይህ ውጤት ከፍተኛ የሚባል ሲሆን ለአካል ማጎልመሻ(ስፖርት) የትምህርት አይነት የተሰጠ ነው። በእርግጥ አስደንጋጩ የውጤቱ ግሽበት አይደለም፣ አንድ ተማሪ እስከ ተማረ ድረስ መቶ ከመቶ ሊያመጣ ይችላል። ያልተማረውን መቶ ከመቶ አመጣ ሲባል ግን እዚያ ጋር ወራጅ አለ ማለት ተገደድኩኝ።
ትምህርት ቤቱን ለዓመታት አውቀዋለሁ፣ የአካል ማጎልመሻ ትምህርት እንደሚሰጥ ግን አላውቅም ነበር። ትምህርት ቤቱን አንድ ቀን እግር ጥሎት የተመለከተ ሰውም ቢሆን የአካል ማጎልመሻ ትምህርት አስተምራለሁ ቢል ሊያምነው አይችልም። ምክንያቱም ትምህርት ቤቱ ለስፖርት ትምህርት የሚሆን መፈናፈኛ ቦታ የለውምና። ታዲያ ምኑ ላይ አስተምሮ ነው የተማሪዎችን ውጤት የሞላው? ማንም ሊጠይቀው የሚገባ ጉዳይ ነው። ወይስ የአካል ማጎልመሻ ትምህርት እንደ ድሮው በተግባር ቀርቶ በንድፈ ሃሳብ ብቻ የሚሰጥ ሆነ?
ድሮ ባይባል እንኳን እስከ ቅርብ ጊዜ የአካል ማጎልመሻ ትምህርት በአብዛኛው ከንድፈ ሃሳብ ይልቅ በተግባር የተደገፈ መሆኑን ነው የማውቀው። ይህን የትምህርት አይነት በተግባር ለማስተማር ደግሞ ሰፋ ያለ የስፖርት መሥሪያ ቦታ የግድ ያስፈልጋል። አብዛኞቹን የአዲስ አበባ በተለይም የግል ትምህርት ቤቶች ካስተዋልን በየመንደሩ በሚገኙ ቀድሞ መኖሪያ ቤት የነበሩ ግቢዎች ውስጥ የተመሠረቱ ናቸው። እነዚህ ግቢዎች ደግሞ እንኳን ለስፖርት ማሠሪያ ትምህርት ቀርቶ ለንድፈ ሃሳቡም አመቺ ስለመሆናቸው አጠራጣሪ ነው። ስለዚህ ትምህርት ቤቶቹ ተማሪዎች በተግባር መማር ያለባቸውን ትምህርት በንድፈ ሃሳብ የክፍል ውስጥ ትምህርት ብቻ እየሰጡ ነው ወይም ከነ ጭራሹ ሳያስተምሩ ውጤት እየቸሩ ነው እንደማለት ነው።
የአካል ማጎልመሻ ትምህርት እንደ ማንኛውም የትምህርት አይነት በኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ የተካተተ ነው። የተካተተበትም ምክንያት አስፈላጊነቱና ያለው ጥቅም ታምኖበት እንጂ እንዲያው ለመርሐ ግብር ማሟያ እንዲሆን አይደለም። በዚህ ረገድ ለሚስተዋለው ችግር ትምህርት ቤቶቹን ብቻ ተጠያቂ ማድረግ አይቻልም። ትምህርት ቤቶቹ መጀመሪያ በዘርፉ ሲሠማሩ ከመንግሥት ፍቃድ ማግኘታቸው የግድ ነው። ይህን ፍቃድ ከማግኘታቸው አስቀድሞም ለመማር ማስተማር ሂደቱ አስፈላጊውን ነገር ማሟላታቸው ይፈተሻል ተብሎ ይታመናል። የአካል ማጎልመሻ ትምህርት በትምህርት ሥርዓቱ የተካተተ እንደመሆኑ ለዚህ አስፈላጊውን ነገር ማሟላታቸውን ማረጋገጥ የሚመለከተው አካል ተግባር ነው። አሁን ጥቂት በማይባሉ የግል ትምህርት ቤቶች የምንታዘበው ጉዳይ ግን ከዚህ የተቃረነ ነው።
የአካል ማጎልመሻ ትምህርት በግል ትምህርት ቤቶች ብዙ ትኩረት ያልተሰጠውና ችላ እንደተባለ ሌሎችንም ምሳሌዎች መደርደር ይቻላል። እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ ዩኒቨርስቲዎች ሳይቀሩ ለተማሪዎች ጥሪ ሲያደርጉ ከቤታቸው ይዘው እንዲመጡ ከሚሰጣቸው ማሳሰቢያዎች አንዱ የስፖርት ትጥቅ ነው። ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ትምህርት ድረስ ሲጋዙ ለአካል ማጎልመሻ የተግባር ትምህርት የስፖርት ትጥቅ ይዘው ያልተገኙ ተማሪዎች የሚቀጡበት ዘመን ነበር። ዛሬ ዛሬ ግን ተማሪዎች የስፖርት ትጥቅ ለብሳችሁ ኑ የተባሉበትን ቀን የሚያስታውስ ካለ ይደንቃል።
በቅርቡ ጉማ በተሰኘ የፊልም ሽልማት ላይ አሸናፊ የሆነው አስኳላ የተሰኘ ድራማ ምን ያህል የትምህርት ቤቶችን ገመና ዘርዝሮ እንዳሳየ ሳናስተውል አይቀርም። እዚያ ድራማ ላይ አንድ መምህር ካለ ሙያና እውቀቱ ሌላ የትምህርት አይነት ደርቦ እንዲያስተምር ሲደረግ ይታያል። ይህ ድራማ ይሁን እንጂ የትምህርት ቤቶችን የገሐዱ ዓለም እውነታ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው። ትምህርት ቤቶች እንዲህ የሚያደርጉት በእያንዳንዱ የትምህርት አይነት ብዙ አስተማሪ ቀጥረው ብዙ ወጪ ላለማውጣት ነው። ይህ እውነታ ደግሞ በአካል ማጎልመሻ ትምህርት ላይ ይበረታል። እንዲያውም ሙዚቃ የሚያስተምር መምህር ስፖርትን ደርቦ እንዲያስተምር ይደረጋል ተብሎ ብዙ ጊዜ በቀልድ መልኩ ሲወራ ማየት የተለመደ ነው። እንዲህ የሚደረገው ግን በዚህ የትምህርት ዘርፍ የተማረና የሰለጠነ የሰው ኃይል ጠፍቶ አይደለም። በሙያው ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ዶክትሬት የተማሩ ብዙ ሰዎች አሉ፤ ግን ማን ይጠቀማቸው።
ቦኤዝ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 8/2015