አዲስ አበባ፡- በሰብልና በእንስሳት ላይ ለተከሰቱ አደጋዎች በተያዘው በጀት ዓመት ብቻ 10 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር ካሳ መክፈሉን የኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ አስታወቀ፡፡
የኩባንያው የማይክሮ ኢንሹራንስ ክፍል ሥራ አስኪያጅ አቶ መልካቸው ተመስገን ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት በተያዘው ዓመት በሰብል እና እንስሳት ላይ ጉዳት ለደረሰባቸው ባለ ሀብቶችና ዩኒየኖች የካሳ ክፍያ ፈፅሟል፡፡ ኩባንያው ለሰብል ጉዳት አሥር ሚሊዮን አንድ መቶ ስልሳ ሺ ብር ለእንስሳት ጉዳት ደግሞ ሁለት መቶ ሠላሳ አንድ ሺ ብር በድምሩ አስር ነጥብ አራት ሚሊዮን ብር ካሳ መከፈሉን አቶ መልካቸው ተናግረዋል፡፡
የካሳ ክፍያው የተፈጸመው ቀደምሲል በወለጋ አካባቢ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በመዝነቡ ሰብላቸው ለጠፋባቸው ባለሀብቶችና በተመሳሳይ በምዕራብ ሐረርጌ በዝናብ እጥረት ሰብላቸው ለተጎዳባቸው አርሶ አደሮች እንዲሁም በቦረና ዞን በድርቅ ምክንያት የግጦሽ ሳር ላጡ አርብቶ አደሮች እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የሰብል ኢንሹራንስ በሁለት ዓይነት መንገድ እንደሚፈጸም የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ ባለብዙ አደጋ የሰብል ኢንሹራንስ እና በአየር ንብረት ለውጥ ወይም በዝናብ እጥረት ምክንያት የሚከሰቱ ተብለው እንደሚለዩ ተናግረዋል፡፡ ባለብዙ የሰብል አደጋ ተብሎ የሚጠራው በሰብል ላይ ከሚከሰቱ ስድስት የተለያዩ አደጋዎች አንዱ ከተከሰተ የሚሰጥ ካሳ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ሁለተኛው የዝናብ እጥረትን ወይም ድርቅን መሰረት አድርጎ የሚሰጥ ሲሆን ይህም ከሳተላይት በሚገኝ መረጃ ከተረጋገጠ በኋላ ለአርሶ አደሩ ተገቢውን ካሳ በመክፈል እራሱን ከሚፈጠረው ችግር አስቀድሞ እንዲከላከል የሚያደርግ አሠራር ነው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ሥራ ላይ የዋለው የእንስሳት ኢንሹራንስ ከኬንያ የተገኘውን ልምድ በመቀመር በኢንሹራንሱ ተግባራዊ መደረግ ከጀመረ ወዲህ በቦረና ዞን ውጤታማ ሥራዎች እንደተሠሩ አስረድተ ዋል፡፡ የእንስሳት ኢንሹራንስ በሀገራችን የመጀመ ሪያ ነው ያሉት አቶ መልካቸው ሀገራችን ከእንስሳት ሀብት የምታገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም አስተማማኝ ለማድረግ አጋዥ እንደሆነና አርብቶ አደሩም ያለስጋት እንዲኖር የሚያደርግ አሠራር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኢንሹራንስ ኩባንያው የዛሬ አስር ዓመት አካባቢ በሁለት እህት ኩባንያዎች፣ በ34 ዩኒየኖች እና በተወሰኑ ባለድሻዎች እንደተ መሠርተ የገለጹት አቶ መልካቸው ማይክሮ ኢንሹራንሱ ከተመሰረተ አንድ ዓመት ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት አክሲዮኑን ከገዙ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ጎን በመቆም ለሚያ ጋጥሟቸው ተፈጥሯዊ አደጋዎች ካሳ ሲከፍል እንደቆየ ገልጸዋል፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 1/2011
በኢያሱ መሰለ