መንግሥት ኢትዮጵያዊ አንድነት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መናገራቸው ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ በሕገ መንግሥቱ የሰፈሩ ህጎችን ጨምሮ አሁን እየታየ ያለው የዜግነት ፖለቲካ እና የማንነት ፖለቲካ መስመር ካልያዙ የታሰበውን ዓላማ ለማሳካት ትልቅ እንቅፋት እንደሚሆኑ በርካቶች ይናገራሉ፡፡
የግንቦት ሰባት ፓርቲ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኤፍሬም ማዴቦ እንደሚሉት እንደ ሀገር ስለኢትዮጵያ አንድነት ያለን አረዳድም ሆነ ትርጓሜ ግልጽ ያልሆነና የተሳከረ ነው፡፡ የሀገር መገለጫ በሆነው ሰንደቅ ዓላማ ሳይቀር ልዩነቱ ሰፊ ሆኖ መጥቷል፡፡ እነዚህ ጉራማይሌ ሁኔታዎች የኢትዮጵያን አንድነት እያላሉ በመምጣታቸው ‹አንድነትን› በውል የማይረዳ ትውልድ እየተፈጠረ ነው ሲሉ ይወቅሳሉ፡፡
የዜግነት ፖለቲካና የማንነት ፖለቲካ በየራሳቸው የፖለቲካ ርዕዮት ገምደው የሚያራምዱ ወገኖች ፍላጎት ከአገራዊ አንድነት ጋር ያለውን ተዛምዶ በአግባቡ ያልተረዳ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወጣት አለ የሚሉት አቶ ኤፍሬም፣ ይህ ሁኔታ ደግሞ አገራዊ አንድነት ላይ ለሚሠራ ሥራ እንቅፋትነቱ በተግባር ጭምር ዕየታየ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ በባለፉት 27 ዓመታት በአገሪቱ የተሠራው ወደ አንድ ቡድን ያደላው የፖለቲካ አካሄድ በተፅእኖ ፈጣሪነቷ ለምትጠቀስ ኢትዮጵያ ቀርቶ በአንድ ቤተሰብ ደረጃም ቢሆን አይጠበቅም፤ አስፈላጊም አይደለም ይላሉ አቶ ኤፍሬም፡፡
በመሆኑም እንዲህ ባለው የላላ አገራዊ አንድነት ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት እና ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመፍጠር ማሰብ የዋህነት ብቻ ሳይሆን ሁኔታው ከባድ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ከአንድ መቶ ሚሊዮን የሚልቅ ህዝብና የተፈጥሮ ፀጋ ያላት ሀገር ናት፡፡ ከሀብቱ ጋር አስተባብረን ተፅእኖ ፈጣሪነትን ለማሳደግ አገራዊ አንድነትን መገንባት ግድ ነው›› የሚሉት አቶ ኤፍሬም፣ ሆኖም በሃሳብ አንድ መሆን ባይጠበቅም ሀገራዊ ጉዳይ ላይ መግባባት እና ኢትዮጵያዊ አንድነት ለድርድር መቅረብ እንደሌለበት ፓርቲያቸው ግንቦት ሰባት ፅኑ እምነት አለው ብለዋል፡፡
‹‹በተበታተነ ሁኔታ ስለኢትዮጵያ አንድነት፣ ትልቅነት መሥራት አስቸጋሪ መሆኑን በመረዳት ፓርቲያቸው ትልቅ እምነት ከጣለባቸው ስድስት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመሆን ሀገራዊ ፓርቲ ለመፍጠር ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አቶ ኤፍሬም አስታውቀዋል፡፡ ይህ ህብረት በአገሪቱ ጫፍ ዕየወጣ ያለውን የዜግነት ፖለቲካና የማንነት ፖለቲካ ፈር ያስይዛል የሚል አምነት እንዳለ የሚጠቁሙት አቶ ኤፍሬም ፣ይሕ ቀርቶ ሁለቱ አስተሳሰቦች የሚያደርጉት መጓተት የሀገሪቷን አንድነት በመፈታተን አደጋው ይሰፋል ብለዋል፡፡
ልዩነቱን በማጥበብ ወደ አገራዊ አንድነት ለማምጣት አርበኞች ግንቦት ሰባትም ሆነ የሀገራዊ ፓርቲ አባል ፓርቲዎች አንዱ የቤት ሥራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ይህ ከ2012 ዓ.ም ሀገራዊ ምርጫ በፊት መሠራት እንዳለበት አምኖ ፓርቲያቸው ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል፡፡ አቶ ኤፍሬም እንዳሉት በ107 ፓርቲዎች የጋራ የመግባቢያ ሰነድ ለመፈራረም ስድስት ወራት መውሰዱን አስታውሰው፣ በመሆኑም የወደፊቷ ኢትዮጵያ በ107 ፓርቲዎች ፍላጎት ሊወሰን አይገባም፣ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ መስማማት ካልተቻለ ስምምነቱ ኢትዮጵያን ለማጥፋት ሊደርስ ይችላል ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ የአቶ ኤፍሬምመን ሃሳብ በማጠናከር እንደገ ለጹት የኢትዮጵያ አንድነት ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ አሊያም ለድርድር ሊቀርብ አይገባም፡፡ ‹‹ፓርቲዎች የኢትዮጵያ አንድነት የተረጋገጠ ጉዳይ መሆኑን አምነን ነው በፖለቲካው ምህዳር ውስጥ የምንንቀ ሳቀ ሰው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሆኖ ኢትዮጵያዊ አንድነትን ማበላሸት አይቻልም፤ መሆንም የለበ ትም፡፡ ህገ መንግሥቱም ይህን አይፈ ቅድም፡፡ ‹የኢትዮጵያን አንድነት ለማጠናከር› በሚል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ በምን ዓውድ እንደተናገሩም ለእኔ ግልጽ አይ ደለም፡፡
ኢትዮጵያዊ አንድነት መነጋገሪያ ርዕሰ ጉዳይ መሆን የለበትም›› ብለዋል፡፡ ‹‹ባለፉት 27 ዓመታት የኢትዮጵያ ብሄር፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች እውቅና ያስፈልገናል ብለው ቢንቀሳቀሱም በኢትዮጵያ አንድነት ስር ሆነው ነው፡፡ ይሁን እንጂ በጋራ እሴቶች ላይ አልተሠራም፤ ዛሬ ደግሞ በእልህና በብስጭት ልቦናቸው ታውሮ ካልሆነ በስተቀር በኢትዮጵያዊ አንድነት ላይ መደራደር ተገቢነት የለውም ሲሉ አቋማቸውን ገልጸዋል፡፡ በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የስነምግባርና ሥነ ዜጋ መምህር ሃሳቡ ተስፋ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ ህዝብ ያሳየው አዎንታዊ ምላሽ ኢትዮጵያዊ አንድነት ላይ በሰጡት አጽንኦት ነው፤ ይሁን እንጂ አሁን መሬት ላይ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ከእርሳቸው የመጀመሪያ አቋም ጋር አብሮ የሚሄድ አይደለም፡፡
የአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሠረታቸው ብሄር ላይ መሆኑ ዛሬ ለሚታየው የፖለቲካ አስተሳሰብ አለመጣጣምና አለመቻቻል ምክን ያት ነው፡፡ በማንነት እንዲደራጁ የህግ ድጋፍ በመኖሩ ገዥው ፓርቲ ጭምር የአራት ብሄር ተኮር ፓርቲ ጥምረት እንደሆነ መምህሩ ይጠ ቅሳሉ፡፡ በሀገሪቷ ላይ የሚስተዋለው የሰላም እጦት እና አገራዊ አንድነት መላላት እየሰፋ ሄዶ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጽንፍ የወጡ አመለካከቶች ጋር ተዳምሮ ህዝቡም እየተከፋፈለ ነው፡፡ ይህን ለማስተካከል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግንባር ቀደም ሚና ሊጫወቱ ይገባል፡፡ ህገመንግሥቱም ስለሚደግፋቸው ከእርሳቸውና ከፓርቲያቸው ብዙ ይጠበቃል፡፡
የሀገሪቱ የፖለቲካ ሥነምህዳር ህገመንግ ሥታዊ መሰረት አለው፡፡ በብሄር መደራጀትን ያበረታታል፡፡ ይሄ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀገራዊ አንድነት ለማምጣት ካላቸው ፍላጎት ጋር ይቃረናል፡፡ ይሄ አንድ ፈተና ነው፡፡ ይህን ለማስተካከል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቁርጠኛ በመሆን ህገ መንግሥቱን እስከማሻሻል መዝለቅ ይችላሉ፡፡ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ፖለቲካል ሳይንስና ዓለምአቀፍ ጥናት ትምህርት ክፍል መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ውሂብ እግዜር የዜግነት ፖለቲካና የማንነት ፖለቲካ ያልታረቁ አስተሳሰቦች ናቸው፡፡
የዜግነት ፖለቲካ የማርክሲስት ጽንሰ ሃሳብ ሆኖ ከ40 ዓመታት በፊት የተተከለ ነው፤ በዚህም የማንነት ፖለቲካ ላለፉት 27 ዓመታት ተቋማዊ ቅርጽ ይዞ ባለበት በዚህ ወቅት ለዜግነት ፖለቲካ ጥሩ መደላድል የለውም ሲሉም ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠንካራ አንድነት ያላትን ኢትዮጵያ እገነባለሁ የሚሉት በተግባርም በፖሊሲም የተደገፈ አይደ ለም፡፡ ኢትዮጵያ አትፈርስም የሚለው ተደጋጋሚ ንግግራቸው በሁለቱ ጫፍ በወጡ አስተሳሰቦች እንደምትፈርስ ግን አመላካች ነገሮች አሉ›› የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ ፣በፖለቲካ ሳይንስ ቋንቋ እያዘቀዘቀች መሆኑን የሚያመለክቱ ነገሮች መሬት ላይ መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡
እርሳቸው እንዳሉት በ1966 ዓ.ም የተካሄደው አብዮት ኢትዮጵያ የነበረችበትን ስሪት ፣ታሪኳን፣ ሂደቷንና እሴቷን በሙሉ አፈራርሷታል፡፡ በሥርዓት ለውጥ ላይ የተገነባች ናት፡፡ ኢህአዴግ ወደ ሥልጣን ሲመጣ ኢትዮጵያን በአዲስ መንገድ ነው የገነባት፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ናቸው ብሎ ህገመንግሥታዊ አድርጎታል፡፡
ከመንግሥት አልፎም የኢትዮጵያ ሀገረመንግሥት መገለጫ አድርጎታል፡፡ ‹‹በመሆኑም አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ኢትዮጵያዊ የሚባል ታሪክ እና ማህበረሰብ የለም፡፡ ላለፉት 27 ዓመታት ኢትዮጵያ እየፈረሰች ብሄር እየተገነባ መሰረት ይዟል›› ሲሉ ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡ አስተያየት ሰጪዎቹ የዜግነት ፖለቲካና የማንነት ፖለቲካ ማስታረቅ ካልተቻለ ዜጎች በፖለቲካ ፓርቲዎችና በመንግሥት ላይ የሚኖራቸው እምነት ይዳከማል፡፡
በሂደትም ሁሉም በየአካባቢው መንግሥት መሰል ቅርጽ የያዘ ነገር ሊኖር ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ ለሃገር አንድነት አደጋ ነው፡፡ መፍትሔውም ኢትዮጵያ በዚህ መንገድ ትሂድ፤ ማን ምን ይሥራ በሚል ሁሉንም አካላት ያሳተፈ ፍኖተካርታ በማዘጋጀት እየላላ የመጣውን ሀገራዊ አንድነት መታደግ ጊዜ መውሰድ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለውን ኢኮኖሚ መዳከም መፍታት፤ የፀጥታ ቀውሶች እና ማንነት ጥያቄ ውስጥ እንዲወድቅ የሚሠራው ሥራ ማስቆም ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 1/2011
በለምለም መንግሥቱ