አዲስ አበባ፡- ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ፍላጎት አሳይተው ከተመለመሉ የውጭ ባለሀብቶች ውስጥ 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መገኘቱን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር አቶ አበበ አበባየሁ ትናንት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን ለንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ባለሀብቶችን በመመልመልና በመሳብ ረገድ አመርቂ ሥራ ተሠርቷል፡፡ እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ተችሏል፡፡
አፈፃፀሙ ሲታይ 70 በመቶ ሲሆን ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 40 በመቶ ዕድገት አስመ ዝግቧል ብለዋል፡፡ በዘርፉ የተመዘገው አመርቂ ውጤት የተገኘው አንድ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ያስመዘገበውን የኢግል ሂልስ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ጨምሮ 225 ፕሮጀክቶች አዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃድ እንዲያወጡና ወደ ሥራ እንዲገቡ በመደረጉ መሆኑን ዋና ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡
በውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ከተገኘው 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በተጨማሪ 227 የሀገር ውስጥ ፕሮጀክቶች አዲስ ፈቃድ እንዲያወጡ በማድረግ 13 ነጥብ 04 ቢሊዮን ብር ኢንቨስት ለማድረግ በእቅድ ደረጃ እንዲመዘገብ መደረጉንም አመላክተዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር በኢንዱስትሪ ፓርኮች ከውጭ ቀጥተኛ ንግድ 103 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት የተቻለ መሆኑንም ዋና ኮሚሽነሩ ለቋሚ ኮሚቴው ገልጸዋል፡፡
በዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተከናወኑትን ሰፊ ኢንቨስትመንት የመሳብ ሥራዎች ተከትሎ አስራ ስድስት የውጭ ድርጅቶች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲገቡ ተደርጎ ሥራ ጀምረዋል፡፡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ኢንዱስ ትሪ ቋሚ ኮሚቴ አባላት በበኩላቸው ባለፉት ዘጠኝ ወራት ወስጥ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ለመሳብ የተደረገውን ጥረት በአድናቆት የሚመለከቱት መሆናቸውን በሰጡት ግብረ መልስ ገልጸዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ጌታቸው መለሰ በተለይም በተደረገው ኢንቨስትመንትን የመሳብ ጥረት የተመዘገበው ውጤት በጠንካራ ጎን የሚወሰድ ነው ብለዋል፡፡ የተገኘው 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የአርባ በመቶ ዕድገት ያሳየ ቢሆንም ከበጀት ዓመቱ ዕቅድ ጋር ሲነጻጸር በዕቅዱ ልክ የተፈጸመ ባለመሆኑ በቀጣይ የበጀት ዓመቱ ቀሪ ጊዜያት ዕቅዱን ለማሳካት ኮሚሽኑ በልዩ ትኩረት መንቀሳቀስ የሚገባው መሆኑን አመላክተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 1/2011
በይበል ካሳ