የመጽሐፉ ስም፡- ኅብር ሕይወቴ
ግለ ታሪክ
ደራሲ፡- ባሕሩ ዘውዴ
የገጽ ብዛት፡- 313
የመጽሐፉ ዋጋ፡- አምስት መቶ አምሳ ብር
በዚሁ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ‹‹ሳምንቱ በታሪክ›› በተባለው ዓምድ ስማቸው በተደጋጋሚ ይጠቀሳል፡፡ በታሪክ መጻሕፍት ውስጥ የእርሳቸው ስም አይጠፋም። በተለይም በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ተደጋግሞ የሚነሳው የእርሳቸው ስም ነው፤ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ።
የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ በቅርቡ የራሳቸውን ግለ ታሪክ ጽፈዋል፡፡ ገና መጽሐፉ ገበያ ላይ የመዋሉ ዜና እንደተነገረ በስስት ነበር ወደተጠቀሰው የመጽሐፍ መደብር የሄድኩት፤ ያልቅብኛል የሚል ፍርሃት ነበረኝ፤ ምክንያቱም የፕሮፌሰር ባህሩ መጽሐፍ ነው፡፡
መጽሐፉን እንደገዛሁ በቀጥታ ነው ወደ ንባብ የገባሁት፡፡ ከምንም በላይ ያስገረመኝ የስነ ጽሑፍ ሰው መሆናቸው ነው፡፡ የታሪክ ተመራማሪ ስለሆኑ ደረቅ የሆነ ነገር ነበር የጠበቅኩትም የለመድኩትም፡፡ ታሪክ የግድ ደረቅ መሆን አለበት ማለቴ ሳይሆን ቢያንስ የኔ ግምት ግን ጠንካራ(serious) የሆነ ነገር ነበር፡፡ ጭራሽ መዝናኛ ጭምር ሆኖ አገኘዋለሁ አላልኩም ነበር፡፡
መጽሐፉ ከአንዲት የተጠይቅ ስህተት በስተቀር(መጨረሻ ላይ እጠቅሳለሁ) ልቅም ያለ አርትዖት የተደረገለት መጽሐፍ ነው፡፡ ቢያንስ የፊደል ስህተት የሌለበት መጽሐፍ ማግኘት ከባድ ነው፤ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ግን የለም፡፡ ይህ የሆነው ከባህሪያቸው አንፃር ነው፡፡ ራሳቸውም እንደገለጹት የተወለካከፈ ዓረፍተ ነገር አይመቻቸውም፡፡ ተማሪዎቻቸውን እንኳን ሲያማክሩ የመጀመሪያ ሥራቸው ቃላትና ዓረፍተ ነገሮችን ማቃናት ነው፡፡ የዚያ ልምድ ይመስላል ይህ መጽሐፍ በጥንቃቄ የተጻፈ ነው፡፡ የህትመት ጥራቱ ለመጽሐፉ ደህንነት ብቻ ሳይሆን ለአንባቢም ምቾት ይሰጣል፡፡
የትልልቅ ሰዎችን የልጅነት ታሪክ ማወቅ ያጓጓል፡፡ እንደኛ ሆነው ያደጉ አይመስለንም፡፡ የሚገርመው ግን እኛ ተራ ግለሰቦች ያደረገውነውን አድርገው ያደጉ ናቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ እኔ ያደረኩትን ነገር ትልቅ ደረጃ ላይ የደረሱ ሰዎች አድርገውት ሳገኝ ኩራት ነገር ይሰማኛል፤ ዳሩ ግን እነርሱ የደረሱበት አለመድረሴን ሳስበው ደግሞ ቁጭት ይሰማኛል፡፡ ስለዚህ የትልልቅ ሰዎች የአስተዳደግ ሁኔታ ራሳችንን እንድናይ ያደርገናል፡፡
የፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ግለ ታሪክ የአንድ ትልቅ ምሁር ግለ ታሪክ ብቻ አይደለም፤ የሀገር ታሪክ ነው፤ የሀገር ብቻ ሳይሆን የዓለም ታሪክ ነው፡፡ ከልጅነት እስከ ዕውቀት የወጡ የወረዱበት ሁሉ ታሪክ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ትልልቅ የታሪክ ክስተቶች ሲከናወኑ በሕይወት ኖረው ያስተዋሉ ናቸው፡፡ በተለምዶ የታኅሳስ ግርግር የሚባለው የ1953ቱ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ሲደረግ ሮጠዋል፣ የነ ጀኔራል ጽጌ ዲቡ አስከሬን ሜዳ ላይ ተዘርሮ አይተዋል፤ እነ ኮሎኔል ወርቅነህ ገበየሁ ፒያሳ አራዳ ጊዮርጊስ በስቅላት ሲቀጡ አይተዋል፡፡
አብዮቱ ሲያብብ፣ ሲፈነዳ፣ ሲከስም አይተዋል። ለሺህ ዘመናት የኖረው ንጉሣዊ ሥርዓት ተገርስሶ ወታደራዊው ደርግ አገር ሲያስተዳድር በታሪክ ምሁርነት ክስተቶችን ከትበዋል፡፡ የደርግን የእስር ገፈት ቀምሰዋል። ምንም እንኳን የእርሳቸውን ባያማርሩትም ይደረጉ የነበሩ የግፍ አይነቶችን ታዝበዋል፡፡ የደርግ መሪ ከነበሩት ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ጋር በአንድ አዳራሽ ተገናኝተዋል፡፡ በ1981 ዓ.ም በደርግ ላይ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ሲደረግ እርሳቸው የታሪክ ምሁር ነበሩ፡፡ 1983 ዓ.ም ኢህአዴግ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር እርሳቸው የታሪክ ምሁር ነበሩ፡፡ 1985 ዓ.ም ኤርትራ ስትገነጠል እርሳቸው የታሪክ ምሁር ነበሩ፡፡ ይሄ ሁሉ የታሪክ ክስተት እየተመዘገበ ያለው በተራ ግለሰብ ሳይሆን በታሪክ ባለሙያ ነበር ማለት ነው፡፡ ሰነድ በማገላበጥ ሳይሆን በዓይን በማየትና በጆሮ በመስማት ሰነዱ ሳይሆን ራሳቸው አንደኛ ደረጃ የመረጃ ምንጭ ሆነው ነው፡፡ ሦስት መንግሥታት ሲፈራረቁ የነበረውን ሁነት አይተዋል፡፡
ግለ ታሪካቸው የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የዓለም ታሪክ ጭምር ነው፡፡ ከዓለም ሀገራት ውስጥ ከሄዱባቸው ይልቅ ያልሄዱባቸውን መጥቀስ ይቀላል፡፡ ከአውሮፓ እስከ አሜሪካ፣ ከእስያ እስከ አፍሪካ፣ የመካከለኛው ምሥራቅ፣ የሩቅ ምሥራቅ ሀገራትን አዳርሰዋቸዋል፡፡ መሄድ ቢባል ደግሞ የጥቂት ቀናት ጉብኝት አይደለም፤ በዓመታት በሚቆጠሩ ቆይታዎች ነው፡፡ ዝቅተኛው ቆይታ በወራት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ አንዳንድ ሀገራትን ደግሞ በተደጋጋሚ በመሄድ ከኢትዮጵያ ያላነሰ የኖሩባቸው ናቸው ማለት ይቻላል፡፡
የዓለምን ታሪክ ራሱ በመኖር የሚያውቁት ይበዛል። ሰውየው ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ የታሪክ ምሁር ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡ የወጡ የወረዱበትን ሁሉ በታሪክ ባለሙያ ዓይን ነው የሚያስተውሉት፡፡ ለዚህም ነው እነዚህ የሄዱባቸውን የዓለም ሀገራት ታሪካቸውን በርብረው የሚያውቁት፡፡ በሄዱባቸው ሀገራት ሁሉ ብሔራዊ ቤተ መዛግብቶቻቸውን ነው የሚበረብሩት፡፡
ይህ የፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ግለ ታሪክ ከተለመዱት የታሪክ መጽሐፎቻቸውና መጣጥፎቻቸው የተለየ መረጃ ነው የሚሰጠን፡፡ መጽሐፎችና መጣጥፎች ታሪካዊ ክስተቶች ላይ የሚያተኩሩ ናቸው፡፡ ይህኛው ግን የየሀገራቱን ማህበራዊ ሕይወት ሁሉ የሚናገር ነው፡፡ ባህላዊና ጥበባዊ እሴቶቻቸውን ሁሉ በዓይነ ህሊና የሚስል ነው፡፡ ገጠመኞቻቸው የእነዚያን ሀገራት ባህልና ወግ፣ ሕግና ልማድ ይነግረናል፡፡ መጽሐፉ መዝናኛም ነው ማለት ይቻላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ መጽሐፉን አጥፌ(ያለሁበት ቦታ ላይ ጣቴን አድርጌ ማለት ነው) የሳቅኩበት አጋጣሚም አለ። በተለይ በልጅነታቸው ብዙ አስቂኝ ነገሮች ነበሯቸው፡፡ የዛሬውን የፕሮፌሰር ባህሩን ማንነት የሚያውቅ ሊያምነው የማይችለው ነገር ልጅ እያሉ ነውጠኛ ነገር ነበሩ፡፡ በዚህ የልጅነት ታሪካቸው ውስጥ ብዙ አስቂኝ ገጠመኞች አሉ፡፡
ያዝናናል ስል የግድ ሳቅ ብቻ አይደለም፤ በዚያን ዘመን የነበሩ ሁነቶችን በማሰብ እንድንቆዝም ያደርጋል። ለምሳሌ የሥጋ ወጥ በ15 ሳንቲም በልተዋል፡፡ በዚያን ዘመን(1950ዎቹ) ለሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በወር 10 ብር አበል ይከፈል ነበር፡፡ ይህን ታሪክ ስናነብ ካለንበት ዘመን ጋር ማነፃፀሩ የግድ ነው፡፡ ምንም እንኳን ያንን ዘመን ከዚህ ዘመን ጋር ማነፃፀሩ አግባብ ነው ባይባልም ልዩነቱ ግን ግርምትን ይፈጥራል፡፡ ዛሬ ላይ ያለ 10 ሺህ ብር ደሞዝ የያኔውን 10 ብር አገልግሎት አይሰጥም፡፡ የዛሬ 10,000 ብር ከያኔው 10 ብር በታች መሆኑ ከማስገረምም አልፎ ያዝናናል፡፡
እግረ መንገድ የሚነገሩ ታሪኮች ያንን ዘመን እንድናስተውል ያደርጋሉ፡፡ ለምሳሌ በሳንቲም የሚሰሩ የግድግዳ ስልኮች በ1973 ዓ.ም ያሉ አይመስለኝም ነበር። እነዚህን ስልኮች የማውቃቸው 1990ዎቹ መጨረሻ አውቶብስ ተራ አካባቢ ነበር፡፡ ያኔ ሳያቸው እነዚያ ስልኮች ከ25 ዓመት በላይ የቆዩ ነበሩ ማለት ነው፤ በቀጥታ ራሳቸው ባይሆኑ እንኳን አገልግሎቱ ከጀመረ ቆይቶ ነበር ማለት ነው፡፡
መጽሐፉ 15 ምዕራፎች ያሉት ሲሆን ሁሉም ምዕራፎች የሚነግሩን ታሪክ የግለሰብ ሳይሆን የሀገርና የዓለም ነው፡፡
የመጀመሪያው ምዕራፍ ‹‹የትውልድ ሐረግ›› የሚል ነው፡፡ በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ያስተዋልኩት ነገር ኢትዮጵያውያን ምን ያህል አንዱ ከአንዱ የተሳሰረ መሆኑን ነው፡፡ በትውልድ ሐረጋቸው ውስጥ የተለያዩ ቋንቋዎችን የያዙ ስሞች ናቸው ያሉት፡፡
ሁለተኛው ምዕራፍ ‹‹ልጅነት›› ነው፡፡ በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ቀደም ሲል የጠቀስኩት የልጅነት ባህሪዎቻቸው፣ ያደጉበት የጌጃ ሠፈር ክስተቶችና አስቂኝ ገጠመኞቻቸው ይገኙበታል፡፡
ሦስተኛው ምዕራፍ ‹‹በትምህርት ዓለም›› ይላል። ይህ ምዕራፍ የትምህርት ቤት ገጠመኞቻቸውን፣ የመምህሮቻቸውን ባህሪ(የውጭ መምህራን ነበሩ)፣ የተሳተፉባቸው ክበባት፣ ጨዋታዎች፣ የታሪክ ትምህርት የወደዱበት አጋጣሚ፣ በታኅሳስ ግርግር የነበረው የተማሪዎች ስጋትና ምኞት የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡
አራተኛው ምዕራፍ ‹‹የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሕይወቴ›› የሚል ሲሆን የዩኒቨርሲቲ ሕይወታቸውን የያዘ ነው፡፡ የ1960ዎቹ የተማሪዎች ንቅናቄን በሰፊው ያስተዋሉበት ነው፡፡ በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ዛሬ በፖለቲካው፣ በምሁርነቱ፣ በኪነ ጥበቡ፣ በተለያየ ዘርፍ የሚታወቁ ሰዎችም ተጠቅሰዋል፡፡ ከእነዚህ ሰዎች ጋር አብረው ተምረዋል፡፡ እነ ጥላሁን ግዛው ሲገደሉ የነበረውን ግርግር ከብዙ ገጠመኞች ጋር ተርከውታል፡፡
በዚሁ ምዕራፍ ውስጥ በዩኒቨርሲቲ አገልግሎት ወደ ደምቢ ዶሎ ተመድበው የቆዩባቸውን ጊዜያትና ገጠመኞቻቸውን እናገኛለን፡፡ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት የነበሩት የዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ አባት (አቶ ጊዳዳ) ጋር ስለታሪክ አውርተዋል፡፡
ምዕራፍ አምስት ‹‹የድኅረ ምረቃ ትምህርት በእንግሊዝ አገር›› የሚል ሲሆን በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የተሸጋገሩባቸው የዓለም አገራትም አሉ፡፡ የአረብኛ ትምህርት ለመማር የከፈሉት ዋጋ ይገኝበታል፡፡ አውሮፓ የነበረው የተማሪዎች ፖለቲካም የዚሁ አካል ነው፡፡
ከዚያ በኋላ ያሉ ምዕራፎች ከልጅነትና ወጣትነት በኋላ ያሉት ናቸው፡፡ ከአውሮፓ እንደመጡ የተቀበላቸው እስር ነበር፡፡ በዘመነ ደርግ ለአምስት ዓመታት ያህል ምክንያቱ ያልታወቀ እስር ታስረዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ወደ ማስተማርና ምርምር ሥራዎቻቸው ተመልሰዋል፡፡ ‹‹የእብደት ዘመቻ›› ሲሉ በገለጹት ወደ መተከል ተጉዘዋል። የዘመቻው ዓላማ በ1977 ዓ.ም ለሠፋሪዎች ጎጆ ለመቀለስ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ በዚሁ ጉዳይ ላይ አንድ የዘመቻው ተሳታፊ የሆኑ ሰው ከአንድ ዓመት በፊት በፍትሕ መጽሔት ላይ ጽፈው አንብቤያለሁ( የጻፉበት ዓውድ የተለየ ቢሆንም)፡፡ ፕሮፌሰር ባህሩ የእብደት ዘመቻ ያሉት ያልተጠና እና ያልተደራጀ ስለነበር ነው፤ በታሰበው ልክም አልሄደም፡፡ በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ብዙ አሳዛኝና አስቂኝ ገጠመኞች አሉ፡፡
በትዳርና በረከቱ ምዕራፍ ለብዙ ሰዎች አርዓያ የሚሆን ቤተሰብ እናገኛለን፡፡ በተለይም የባለቤታቸው ወይዘሮ መሰንበት ሸንቁጤን (እርሳቸውም ታዋቂ ናቸው) ስኬት ላስተዋለ ‹‹ባልና ሚስት ከአንድ ባህር ይቀዳል›› የሚለውን አባባል ለማመን ይገደዳል፡፡
ሙያዊ የውጭ አገራት ቆይታዎቻቸው የተዳሰሱበት ምዕራፍ ቀደም ሲል እንዳልኩት የዓለምን ታሪክ ብቻ ሳይሆን ማህበራዊና ባህላዊ እሴቶቻቸውን ጭምር የሚነግረን ነው፡፡
‹‹የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ዳይሬክተርነት›› በሚለው ምዕራፍ 11 ውስጥ ከተጠቀሱት አንደኛውን ርዕሰ ጉዳይ ሳልጠቅሰው አላልፍም፡፡ ይሄውም በ1988 ዓ.ም የዓድዋን 100ኛ ዓመት ለማክበር ያበረከቱት አስተዋጽኦ ነው፡፡ ዝግጅቱ የታሰበው ከአንድ ዓመት ቀደም ብሎ ሲሆን ብዙ ውጣ ውረድ ያዩበት ነው፡፡ የወቅቱ መንግሥት በዝግጅቱ ብዙም ደስተኛ እንዳልነበር ያስታውቃል፡፡ እንዲያውም የእነርሱ ዝግጅት ድምቀት እንዳይኖረው መንግሥት ተመሳሳይ ኮሚቴ ያቋቁም ነበር፡፡ አዘጋጆቹ እነ ፕሮፌሰር ባህሩ ግን እንደምንም ታግለው በታሰበው ልክ ባይሆንም የዓድዋን 100ኛ ዓመት በደማቁ አክብረዋል፡፡
ፕሮፌሰር ባህሩ በርካታ ብሔራዊ አገልግሎቶችን ሰጥተዋል፡፡ በተለያዩ ማህበራትና አካዳሚዎች አገራቸውን አገልግለዋል፡፡ አህጉራዊ የሲቪል ማህበረሰብ ተሳትፎዎችን አድርገዋል፡፡ ለምሳሌ፤ በአፍሪካ የማህበራዊ ጥናት ልማት ምክር ቤት(Council for the development of Social Science research in Africa)፣ የአፍሪካ የታሪክ ባለሙያዎች ማህበር እና ትረስት አፍሪካ በመሳሰሉ አህጉራዊ የሲቪል ማህበረሰብ ተሳትፎዎችን አድርገዋል፡፡ በእነዚህ ተቋማትም የኢትዮጵያን ገጽታዎች አስተዋውቀዋል፡፡
ከገጽ ብዛት ይልቅ በወርድ እና በስፋት ዳጎስ ያለው የፕሮፌሰር ባህሩ መጽሐፍ የ76 ዓመታት ክስተቶችን ይነግረናል፡፡ በአራት መንግሥታት ውስጥ ያሳለፏቸውን የልጅነት፣ የወጣትነት፣ የጎልማሳነትና የሽማግሌነት አስተውሎቶችን ይነግረናል፡፡ የሒሳብ ሊቅ ሊሆኑ የነበሩ ሰው እንዴት የታሪክ ተመራማሪ እንደሆኑ አጋጣሚውንም ይነግረናል፡፡
መጽሐፉ ከሆሄያት ግድፈት የጸዳ ሲሆን አንድ ቦታ ግን ልብ ሳትባል የገባች ስህተት አለች፡፡ ይሄውም በ1997 ዓ.ም ሚያዚያ 29 እና ሚያዚያ 30 የተደረጉ የኢህአዴግና የቅንጅት ሰልፎች ሰኔ 29 እና ሰኔ 30 ተብለው ነው የተገለጹ፡፡ የቅርብ ታሪክ ሲሆን ችግሩ ይህ ነው፡፡ ሰዎች ክስተቱን በቅርበት ስለሚያውቁት ቀኑ ልብ አይባልም፡፡ አርትዖት የሚሰራው ሰው ታሪኩን ስለሚያውቀው ምናልባትም ሚያዝያ ብሎ ነው በውስጡ የሚያነበው፡፡
ፕሮፌሰር ባህሩ በኢትዮጵያ ታሪክ ፀሐፊነት በሚዛናዊና ሙያዊ ፀሐፊ የሚጠሱ ናቸው፡፡ ልዩ የሚያደርገው ደግሞ የታሪክ ባለሙያ መሆናቸው ነው፡፡ ብዙ የታሪክ መጻሕፍት የተጻፉት በዘመኑ በነበሩ ዜና መዋዕል ፀሐፊዎች ነው። ከቅርብ ዘመናት ወዲህ ደግሞ በፖለቲከኞችና በወቅቱ ከፍተኛ አመራርነት ላይ በነበሩ ሰዎች ነው፡፡ እነዚህ አካላት ደግሞ ምንም እንኳን ክስተቶችን ቢነግሩንም በሙሉ ልብ ለማመን ግን አያስደፍርም፡፡ ምክንያቱም ይመሩት ለነበረው የፖለቲካ ኃይል ማዳላታቸው አይቀርም፡፡
ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ግን የታሪክ ባለሙያ ናቸው። ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ ታሪክን በፍቅር የተማሩ፣ ዕድሜ ዘመናቸውን በታሪክ ምርምር የቆዩ ናቸው፡፡ የግል ሕይወታቸው ራሱ የኢትዮጵያ እና የዓለም ታሪክ ነው፡፡ ለዚህ ታላቅ አበርክቷቸውም 2009 ላይ የበጎ ሰው ሽልማትን አግኝተዋል፡፡
ፕሮፌሰር ባህሩን ለዚህ አብርክቷቸው እያመሰገንን ሌሎችም ምሁራን በየዘርፋችሁ ያለውን እንድትጽፉልን አደራ እንላለን
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሰኔ 29/2015