አዲስ አበባ፡- የዋጋ ግሽበቱን ወደ ነጠላ አሃዝ የማውረድ ሥራ ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሻ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የገንዘብ ሚኒስቴር የ2011 ዓ.ም የዘጠኝ ወር እቅድ አፈጸጸም ሪፖርት መሰረት አድርጎ ትንናት በሰጠው ማብራሪያ ባለፉት 8 ወራት የዋጋ ግሽበቱ ከነጠላ አሃዝ በላይ ሆኗል፡፡ አጠቃላይ ወርሃዊ የዋጋ ግሽበት 10 ነጥብ 9 በመቶ ሲሆን፣ የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ዕቃዎች የዋጋ ግሽበት በቅደም ተከተል 10 ነጥብ 7 እና 11 ነጥብ 2 በመቶ ሆኗል፡፡
በስድስት ወር ዕቅድ አፈጸጸም ቋሚ ኮሚቴው ለሚኒስቴሩ ግብረ መልስ የሰጠ ቢሆንም ወደ ነጠላ አሃዝ ሊያወርድ አልቻ ለም፡፡ ይህም የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እጥረት ነው፡፡ የአንዳንድ መሰረታዊ ዕቃዎች ዋጋ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በእጥፍ መጨመሩን የተናገሩት የቋሚ ኮሚቴው አባላት፤ሸዋ ዳቦ በዳቦ ዋጋ ላይ ያደረገው ጭማሪ ለአብነት የሚጠቀስ ነው ብለዋል፡፡ የዋጋ ግሽበቱ በተለይም የሀገሪቱን አብዛኛውን ቁጥር የሚይዘውን ዝቅተኛ ገቢ ያለውን የህብረተሰብ ክፍል የሚነካ በመሆኑ እንደቀላል ሊታይ እንደማይገባ ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል፡፡
መንግሥት የዋጋ ግሽበቱን ወደ ነጠላ አሃዝ ለማውረድ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ ለምለም ሀድጉ እንደተናገሩት፤ የዋጋ ግሽበቱ በአሃዝ ከሚገለጸውም በላይ ነው፡፡ አብዛኛው የሀገሪቱ ህዝብ ዝቅተኛ ገቢ ያለው በመሆኑ ይጎዳል ብለው የህዝቡን ኑሮ ሊያናጋ የሚችል የዋጋ ግሽበት በቀላሉ መታየት እንደሌለበትና ሀገራዊ ጉዳይ ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡ የዋጋ ግሽበቱ በአቅርቦትና በፍላጎት መካከል ባለው ክፍተት የተፈጠረ ነው ያሉት የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዋ ችግሩ በገንዘብ ሚኒስቴር ጥረት ብቻ እንደማይፈታና ቅንጅታዊ ጥረት እንደሚጠይቅ ገልጸዋል፡፡
ሚኒስቴሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ገበያውን በማረጋጋት ኢኮኖሚው ጤናማ እንዲሆን ጥረት ማድረግ አለበት ብለዋል፡፡ መንግሥት ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት፤ በይነ መንግሥታት፤ የልማት አጋር ድርጅቶችና ከተለያዩ መንግሥታት በዕርዳታና ብድር የተገኘው ሀብት እንደ ጥንካሬ የሚታይ ነው፡፡ ይህን ጥንካሬ በማስቀጠል በዋጋ ግሽበትና በሌሎች ላይ የታዩ ድክመቶችን ለማስተካከል መረባረብ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ፣ በተያዘው ዓመት የዋጋ ንረቱን በነጠላ አሃዝ እንደሚቆይ ቢታቀድም ማሳካት አልተቻ ለም፡፡ በምርትና አገልግሎት አቅራቢዎች የሚፈጠሩ የዋጋ ይጨምራል ተስፋ፤ በአንዳንድ ቦታዎች የተከሰቱ አለመረጋጋቶችና የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት እጥረት ለዋጋ ንረቱ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ የዋጋ ንረቱን ወደ ነጠላ አሃዝ ለማውረድ የተለያዩ ዕርምጃዎች ተወስደው በትኩረት እየተሠራ ነው፡፡
የዋጋ ንረቱ ዝቅተኛ ገቢ ያለው ህብረተሰብ ክፍል ላይ ከፍተኛ ጫና እንደሚያስከትል ከግምት በማስገባት የግብርና ምርትን ለማሳደግ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን ያብራሩት ሚኒስትሩ የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ በቂ ጥናት ተደርጎባቸው አዋጪ ነታቸው እርግጠኛ የተሆነባቸውን የመስኖ ፕሮጀክቶችን መንግሥት ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ የውጭ ኢንቨ ስትመንትን መሳብም ሌላው አማራጭ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 1/2011
በመላኩ ኤሮሴ