አዲስ አበባ፡- መንግሥት ዜጎችን ከመኖ ሪያቸው በማፈናቀል፣ በማንገላታትና በተለ ያዩ ወንጀሎች ተሰማርተው ሲንቀሳቀሱ በነበሩ ግለሰቦችና አመራሮች ላይ የተጀመረው ለህግ የማቅረብ ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል የተለያዩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ጠየቁ፡፡
የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮቹ የሰላም ሚኒስቴር ከትላንት በስቲያ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረበውን የ2011 ዓ.ም በጀት ዓመት የዘጠኝ ወር እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት መሰረት አድርገው ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት መንግሥት አጥፊዎችን ለህግ በማቅረብ የወሰደው ዕርምጃ የዘገየ ቢሆንም በህዝብ የሚደግፍና ተጠናከሮ መቀጠል ያለበት ነው፡፡ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረሥ ፓርቲ(ኦፌኮ) ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና እንደገለጹት የዘገየ ዕርምጃ መውሰድ በገዥው መንግሥት የተለመደ ነው፡፡
እንደተለመደው የአንድ ሰሞን ከመሆን ባለፈ ዘላቂ መፍትሔ የሚያስገኝ መሆን አለበት ብለዋል፡፡ መንግሥት ፈተና ሆነውብኛል ያላቸው አንዳንድ የፀጥታ አካላትና አመራሮችን ጠንቅቆ የሚያውቃቸው እንደሆኑም ጠቁመው ተገቢ ዕርምጃ የመውሰድ ኃላፊነቱም የመንግሥት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ እንደ ፕሮፌሰሩ ገለጻ ፓርቲያቸው አባሎቻ ቸውን በመምከር እና በሚያገኘው መድረክም በየአካባቢው ያለውን ችግር ለመንግሥት በማሳወቅ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱንና አሁንም እንደሚያደርግ አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት ኮንግረስ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ገረሱ ገሳ መንግሥት አጥፊዎችን ለህግ ማቅረብ መጀመሩን በበጎ ቢወስዱትም በማባበል የተወሰደው ጊዜ አግባብ እንዳልሆነ አመልክተዋል፡፡ ዕርምጃ ውጤት ካላመጣ ለወገን ተስፋም ተገንም ሊሆን እንደማይችል ተናግ ረዋል፡፡ አንዳንድ የፀጥታ ኃይሎች ለመተባበር ፈቃደኛ ያለመሆናቸው ጉዳይ ስሜት የሚነካ መሆኑን ጠቅሰው፣ መንግሥት ልዩ ኃይል በሚል በሁሉም ክልሎች ያደራጀውን ኃይል መቆጣጠርና ትጥቅ ማስፈታት የመጀመሪያው ሥራ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
ይህን ኃይል አሠልጥኖ ወደሰላም መመለስ ካልተቻለ በዕርምጃ ብቻ መፍታት እንደማይቻል አመልክተዋል፡፡ ዜጎችን በማፈናቀልና ከግጭት ተጠቃሚ የሆነ ኃይል ከመንግሥት ጋር ይተባበራል የሚል እምነት እንደሌላቸው የሚናገሩት አቶ ገረሱ መንግሥት ለህግ ያቀረባቸው ተልዕኮ የሚፈጽሙትን እንጂ በሚያንቀሳቅሰው፣ ስምሪት በሚሰጠው ላይ ደርሶ ዕርምጃ አለመውሰዱን አመልክተዋል፡፡ በዚህ ላይ ትኩረት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ፓርቲያቸው የክልል ኃይል ማደራጀት አስፈላጊ እንዳልሆነ ግን በተደጋጋሚ ለመንግሥት ማሳወቁንም ተናግረዋል፡፡ ፓርቲያቸው ከህዝብ ሰላም ጎን መሆኑንና በተለያየ መድረክ ላለፉት ዓመታት ስለሰላም ሲያንጸባርቅ የነበረውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል፡፡ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር ፓርቲ ሊቀመንበር ዶክተር አረጋዊ በርሄ በሀገር ላይ ቀውስ በሚያስከትል ነገር ላይ ጊዜ መስጠት እንደማይገባ ገልጸዋል፡፡
‹‹ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ በቅርቡ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፈረሙት መግባቢያ ሰነድ ሀገርና ህዝብን ማስቀደም፣ ሰላም ማስፈን፣ ከመንግሥት ጋር በመሆን መርሆዎቹን መተግበር የሚል ያለው በመሆኑ ይህንን መሰረት በማድረግ የሚጠበቅብንን እንወጣለን›› ይላሉ፡፡ ፓርቲያቸው ጽንፍ የረገጠ አካሄድን በመቃወም አቋሙን እያሳወቀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 1/2011
በለምለም መንግስቱ