የሰኔ ወር መጨረሻ እና የሐምሌ ወር መጀመሪያ አካባቢ ያሉ ሳምንታት (የዘንድሮው የራሱ ፕሮግራም የወጣለት ቢሆንም) በዩኒቨርሲቲዎች የምርቃት ፕሮግራም ዝግጅት ይደምቃሉ፡፡ እዚህ ላይ ታዲያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መነጋገሪያ መሆን የጀመረ አንድ ጉዳይ አለ፤ ይኸውም የዩኒቨርሲቲዎች የክብር ዶክትሬት ጉዳይ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎቻቸውን ሲያስመርቁ ለታዋቂና አንጋፋ ሰዎች የክብር ዶክትሬት ይሰጣሉ፤ የተሰጣቸው ሰዎችም ‹‹የክብር ዶክተር›› ይባላሉ፡፡ የማክበር (የዕውቅና) እንደማለት ነው፡፡
ታዲያ ምን ይገርማል? ለምን መነጋገሪያ ይሆናል? ከተባለ፤ አጀንዳ የሚያደርገው ያው የተለመደው (በፖለቲካው ማለት ነው) የጎጥ ጣጣ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች ምንም አስበው ያድርጉት አንድ ታዋቂ ሰው የክብር ዶክትሬት ተሰጠው ሲባል የሰውየውን ብሔር ማጥናት ይጀመራል፡፡ የሰውየው የትውልድ አካባቢ ዩኒቨርሲቲው ያለበት ክልል ውስጥ ከሆነ ዩኒቨርሲቲውን ከማድነቅ ይልቅ በብሔር ነው የሰጠው የሚሉ ወቀሳዎች ይሰነዘራሉ።
ወቀሳው የሚነሳው ግን ዝም ብሎ ከመሬት ተነስቶ አይደለም፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች የክብር ዶክትሬት ሲሰጡ ዘር እየቆጠሩ የሚሰጡ ስለሚመስል ነው፡፡ እርስ በእርሳቸው የሚፎካከሩበት ስለሚመስል ነው። አንዱ ዩኒቨርሲቲ ለክልሉ ሰው ከሰጠ ሌላኛውም ዘር አጥንቶ ያደርገዋል ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ በአንድ ዓመት ውስጥ የክብር ዶክትሬት የሰጡ ዩኒቨርሲቲዎች፤ የሰጧቸው ሰዎች ዩኒቨርሲቲው ያለበት ክልል ተወላጅ ከሆኑ የምርም ያስጠረጥራል ማለት ነው፡፡ ወይም ደግሞ አንድ ዩኒቨርሲቲ በተደጋጋሚ ለአንድ አካባቢ (ዩኒቨርሲቲው ላለበት ክልል) የክብር ዶክትሬት የሚሰጥ ከሆነ ለወቀሳ መዳረጉ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡
እዚህ ላይ ግን አንድ በትልቁ ልብ ማለት ያለብን ነገር አለ፡፡ ይኸውም፤ ‹‹ዩኒቨርሲቲዎች የክብር ዶክትሬት የሚሰጡት በብሔር ነው›› የሚሉ ወቃሾችም ራሱ የጎጠኛነት አስተሳሰብ ያላቸው ሊሆኑም ይችላሉ፡፡ ምክንያቱም መባል ያለበት፣ ሰውየው ምን ሠርቶ ነው የሚመሰገነው? የክብር ዶክትሬት ማግኘት ይገባው ነበር ወይ? የሚለውን ነው እንጂ መታየት ያለበት የዩኒቨርሲቲውንና የሰውየውን ብሔር ማዛመድ አልነበረም፡፡ አንድ ሰው በየትኛውም ዘርፍ ለሀገር የዋለው ውለታ ለክብር ያበቃዋል ከተባለ ማንም ዩኒቨርሲቲ ቢሰጠው ችግር የለውም፡፡
ከዚህ ይልቅ ችግሩ ዩኒቨርሲቲዎች የክብር ዶክትሬት የሚሰጡት ትክክለኛ ሥራዎችን በማጥናት ሳይሆን ዝናን ብቻ መሠረት በማድረግ ለማስታወቂያ በሚመስል መንገድ መሆኑ ነው፡፡ ዝነኛ ሁሉ ለሀገር ባለውለታ ነው ማለት አይደለም፣ ዝነኛ ሁሉ በሆነ ዘርፍ ላይ አስተዋፅዖ አበርክቷል ማለት አይደለም። ዝና በየትኛውም አጋጣሚ ይገኛል፤ ሀገር አጥፊ ሆኖም እኮ ዝና ሊገኝ ይችላል፡፡ ያ ሰው የሠራው ሥራ በሁለንተናዊነት እንደ ሀገር ምን አበርክቷል የሚለው ነው መታየት ያለበት፡፡ ምክንያቱም ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የንግድ ካምፓኒ አይደለም ማስታወቂያ የሚፈልገው፣ እንደ ቢዝነስ ተቋም አምባሳደር የሚሆነውን አይደለም መምረጥ ያለበት። ዩኒቨርሲቲዎች ከፍተኛ የምርምር ተቋም ስለሆኑ ቢያንስ ለማኅበራዊ አገልግሎት የቀረቡ ቢሆን፤ የግድ በዚያ ብቻ ይገደብ ባይባል እንኳን የክብር ዶክትሬት የሚሰጠው አካል የሠራው ሥራ ለሀገር ምን አበርክቷል የሚለው ቢቀድም የተሻለ ነው፡፡
የምር ግን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሚሰጥ የክብር ዶክትሬት መፎካከሪያ አይመስልም? ዶክትሬቱ ከተሰጠው ሰውየ ሥራዎች ይልቅ ለምን አሰጣጡ አጀንዳ ሆነ? ችግሩ የምርም የዩኒቨርሲቲዎች የአሰጣጥ ሁኔታ ነው ወይስ የሰዎች የአተያይ ችግር? እነዚህ ነገሮች ልብ መባል አለባቸው፡፡
ትዝብቴ ብሔርን መሠረት አድርገው ዕውቅና ስለሚሰጡ ዩኒቨርሲቲዎች እና ብሔርን መሠረት አድርገው ትርጓሜ ስለሚሰጡ ሰዎች ስለሆነ እንጂ በፍፁም የብሔር ስሜት ሳይኖራቸው ዶክትሬት የሚሰጡ ዩኒቨርሲቲዎች መኖራቸውን የማላውቅ ሆኖ አይደለም፡፡ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ ምንም ነገር ሳይገድባቸው በሰዎች ሥራ ብቻ የክብር ዶክትሬት የሰጡ አሉ፡፡ ዩኒቨርሲቲው ያለበት ክልል እና የክብር ዶክትሬት የተሰጠው ሰውየ የተለያየ ብሔር የሆኑ ማለት ነው። በብዛት ያለውን እንቁጠር ከተባለ ግን ዕውቅና የሚሰጠው ሰው ዩኒቨርሲቲው ያለበት ክልል ብሔር ተወላጅ የሆነ ነው፡፡
እዚህ ላይ አሁንም አንድ ልብ መባል ያለበት ነገር አለ፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች የማኅበረሰብ ችግር ፈቺ ምርምሮችን ይሠራሉ፡፡ የማኅበረሰብ ምርምሮችን የሚሠሩ ደግሞ በብዛት ዩኒቨርሲቲው ባለበት አካባቢ ነው፡፡ ስለዚህ ምናልባትም ብዙ በጎ ነገሮችን የሚያገኙት በዚያ አካባቢ ከሚንቀሳቀሱ ሰዎች ነው፡፡ ስለዚህ የክብር ዶክትሬት የሚሰጡት ሰው የዚያ አካባቢ (ዩኒቨርሲቲው ያለበት ክልል ብሔር) ተወላጅ መሆናቸው የሚጠበቅ ነው፡፡ ይሄ ማለት ግን አስበውበት (ብሔርን መሠረት አድርገው) አይሠሩም ብሎ ለመደምደም አያስችልም፤ ምክንያቱም ቀደም ሲል እንዳልኩት ዝናን ብቻ መሠረት አድርገው ሊሰጡ ይችላሉ፡፡
በዚህ አጋጣሚ ግን የክብር ዶክትሬትን በተመለከተ ሌላኛው ትዝብቴ (ዩኒቨርሲቲዎችን ባይመለከትም) የማዕረግ አጠቃቀስ ጉዳይ ነው። በዚሁ ጉዳይ ላይ ከዓመታት በፊት አንድ ፒ ኤች ዲ ያላቸው ሰውየ በአንድ መጽሔት ላይ የጻፉትን ትዝብት አንብቤ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ‹‹ዶክተር›› የሚለው ቃል ተደበላልቆ ነው የሚነገር፡፡ ሐኪሙም ዶክተር ነው፣ ፒ ኤች ዲ የሠራውም ዶክተር ነው፣ የክብር ዶክትሬት የተሰጠውም ዶክተር ነው። ስለዚህ ስለሰውየው ዝርዝር መረጃ የሌላቸው ሰዎች ‹‹ዶክተር እገሌ›› ሲባል የምን እንደሆነ ራሱ አያውቁም፡፡ ሐኪም የነበረ የሚመስለውም ይኖራል።
የክብር ዶክትሬት ተሰጥቷቸው ‹‹ዶክተር›› ካልተባልኩ ብለው የሚቆጡ እንዳሉም ትዝብቶች ነበሩ፡፡ የክብር ዶክትሬት የተሰጠው ሰው የክብር መሆኑ ተገልጾ ነው የሚጠቀስለት እንጂ በቀጥታ ዶክተር በሚል ማዕረግ መጥራት ልክ አይደለም፤ ምክንያቱም በአካዳሚ አይደለም ያገኘው፣ ለሠራው ሥራ የተሰጠው ክብር ነው፡፡ እንኳን የክብር ዶክትሬት ፒ ኤች ዲ እና የሙያ ዶክተርነት ራሱ ልዩነት አላቸው።
ወደ ዋናው ትዝብታችን ማጠቃለያ ስንመለስ፤ ዩኒቨርሲቲዎች የክብር ዶክተር ስትሰጡ በዝምድና አታድርጉ፡፡ ታዛቢዎችም ሁሉንም ነገር የግድ አይተረጎምም፡፡ ሰውየው ያ ክብር የሚገባው ከሆነ ማንም ይስጠው፤ እንዲያውም ቀድሞ የሰጠ ነው ሊመሰገን የሚገባ፡፡ ከዚህ ይልቅ ትኩረት መሰጠት ያለበት ‹‹የሚገባቸውን ሰዎች ልብ በሉ!›› የሚለውን ነው! የተሰጣቸው ሰዎች አይገባቸውም ሳይሆን ሊሰጣቸው የሚገባ ሆነው፣ ዳሩ ግን ስላልተጮኸላቸው ልብ ያልተባሉ አሉና እነርሱም ልብ ይባሉ!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሰኔ 28/2015