አዲስ ዘመን ከድሮ እስከ ዘንድሮ እለታዊ ዜናዎችን እየዘገበና ታሪክን እየሰነደ የመረጃና የእውቀት አድማስ ሆኖ ቀጥሏል። ለመሆኑ አዲስ ዘመን ድሮ ምን መልክ ነበረው?፣ የአዲስ ዘመን ድሮ አምዳችን ያስመለክተናል። የኢትዮጵያና የሶቪየት ደራሲን ስምምነት ፈረሙ፣ መካ የሔዱ ኢትዮጵያውን እስላሞች ደህና ናቸው፣ በማገገም ላይ ያሉ ሚሊሺያ አባላት ፊልም ተመለከቱ፣ አዲሱ ትውልድ ለምን ቶሎ ይገረጅፋል፣ ይድረስ ላገሬ ገበሬና ሌሎችም የጋዜጣው ቀደምት ዘገባዎችን አመታትን ወደ ኋላ ተጉዘን እናስታውስ።
የኢትዮጵያና የሶቪየት ደራሲያን ስምምነት ፈረሙ
የኢትዮጵያና የሶቪየት ሕብረት ደራሲያን አንድነት ማኅበራት በሚከተሉት የማርክሲዝም- ሌኒንዝም ርዕዮተ ዓለም አንጻር ፀረ-ኢምፔሪያሊዝም፣ ፀረ-ኮሎኒያሊዝም፣ ፀረ ዘረኝነትና በአጠቃላይ ፀረ-አድኅሮት በማጠናከር ሥነ ጽሑፍን ለማዳበርና በዚህ ረገድም የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ ለማሳደግ የሚያስችል የትብብር ስምምነት ጥቅምት 19 ቀን በሞስኮ ከተማ የተፈረመ መሆኑን ይህም የትብብር ስምምነት በአፍሪካ አህጉር የመጀመሪያ መሆኑን የኢትዮጵያ ደራሲያን አንድነት ማኅበር ዋና ጸሐፊ ጓድ አሰፋ ገ/ማሪያም ገለጡ። (አዲስ ዘመን ጥር 13 ቀን 1968ዓ.ም)
መካ የሔዱ ኢትዮጵያውያን እስላሞች ደህና ናቸው
ወደ መካ ለመሳለም የሄዱ ኢትዮጵያውያን የእስልምና እምነት ተከታዮች በሙሉ፤ ባለፈው ዓርብ በዚሁ ስፍራ ደርሶ በነበረው የእሳት አደጋ ምንም ጉዳት ያልደረሰባቸው መሆኑን ጂዳ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታወቀ።
በሳውዲ ዓረቢያ የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ አብደላ አብዱራህማን ለውጭ ጉዳይ በላኩት ቴሌግራም ሚና ከተባለው የድንኩአን ከተማ በተነሳው የእሳት ቃጠሎ አንድም ኢትዮጵያውያን አለመጎዳታቸውን አረጋግጠዋል።
ለሦስት ሰዓት በቆየው የእሳት ቃጠሎ ከሁለት ሚሊዮን ምእመናን መካከል በርከት ያሉ ሰዎች መሞታቸውና መቁሰላቸው ታውቋል። ( አዲስ ዘመን ታህሳስ 7 ቀን 1967ዓ.ም )
በማገገም ላይ ያሉ ሚሊሺያ አባላት ፊልም ተመለከቱ
ለገዳዲ፣(ኢ.ዜ.አ) የአብዮታዊት ኢትዮጵያ አንድነትና ሕልውና ለመጠበቅ በየጦር ሜዳው ከውስጥና ከውጭ አድኃሪ ኃይሎች ጋር በመዋደቅ ግዳጃቸውን አከናውነው በለገዳዲ የማገገሚያ ጣቢያ የአብዮታዊት ኢትዮጵያ የሚሊሺያ አባሎች ትናንት መሠረተ ትምህርትን የሚመለከት ትግል ድል፣ ድል ትግል የተሰኘውን ፊልም ተመለከቱ።
ከብሔራዊ መሠረተ ትምህርት የእርዳታና ቅስቀሳ ንዑስ ኮሚቴ የተላከውና በግብርና ሚኒስቴር የሲኒማ ቡድን አማካይነት የቀረበው ይኸው ፊልም ከመታየቱ ቀደም ሲል፣ የለገዳዲ ማገገሚያ ጣቢያ አስተዳዳሪ አባሎቹ ከመሠረተ ትምህርትና ከምርት ዕድገት ዘመቻው አንጻር ስላከናወኑዋቸው ሥራዎች በሥፍራው ለተገኙ የመሠረተ ትምህርት የእርዳታና ቅስቀሳ ኮሚቴ አባሎች ገለጻ አድርገዋል። (አዲስ ዘመን ታህሳስ 7 ቀን 1967ዓ.ም)
ዋናው ሊቀመንበር የደስታ መግለጫ መልዕክት ላኩ
ብርጋዴር ጄነራል ተፈሪ ባንቴ የጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ዋና ሊቀመንበር የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስተር ሆነው አዲስ ለተመረጡትና እንዲሁም ለባንግላዲሽ ሕዝባዊ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ትላንት የደስታ መግለጫ መልእክት አስተላለፉ። (አዲስ ዘመን ነሐሴ 10 ቀን 1967ዓ.ም)
ይድረስ ላገሬ ገበሬ
ያገሬ ገበሬ ሆይ ሰላም ላንተ ይሁን እነሆ ያልደከምክበትን እህልና ገንዘብ እየዘረፈ እሚወስደው፤ ያልወለደውን ልጅ ተየቤቱ እየለቀመ ወደ ጦርነት እሳት የሚማግደው፤ ያ አጋሚዶ መንግሥት ከተደመሰሰ ከአንድ አመት በላይ አለፈ-(እማያልፍ የለም) በድህነትህ ላይ ያለፍላጎትህ ለእናት አገር ጥሪ ለመኢገማ፣….ለአኢሴማ ለምንትስ…እየተባልክ ገንዘብህን ስትዘረፍ ኖርክ።
ያንተ ማምረት የእኛ የሁላችን ነፍስ መዝራት፣ ሕይወት መለምለም ነውና ዛሬ ነገ ታትል ለሁላችን ሕይወት ስትል በርትተህ ትሠራ ዘንድ እንማጠንሃለን። እንደምተውቀው እኛም እናታችንም ድኃ ነን። ተሁሉ ተሁሉ እሚደንቅ ነገር፤ ፈቺ ያጣ እንቆቅልሽ አለልህ። ለብዙ ዘመን “የዳቦ ቅርጫት” የኖረችው ይህች ሀገር “ተፈጥሮ ያደላት የተፈጥሮ ባለጠጋ” የምንላት ይህች የእኛ ሀገር፤ በምግብ እህል እንኳን እራሱን ሳትችል ይሄውና እሰተ ዛሬ በድህነት እሷም አለች። እኛም አለን። ዕንቆቅልሹም ይሄው ነው። (አዲስ ዘመን መስከረም 5 ቀን 1985ዓ.ም)
ሆስፒታል ለሕክምና የሔደችውን ልጃገረድ ክብረ ንጽሕና የደፈረ አንድ አመት ተፈረደበት
አርባ ምንጭ፤ (ኢ.ዜ.አ)- በገሙ ጎፋ ክፍለ ሀገር በጉማይዴ ወረዳ ውስጥ ለሕክምና የሔደችውን ልጃገረድ አስገድዶ ክብረ ንጽሕናዋን ደፍሮአል ተብሎ የተከሰሰው አንድ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ባልደረባ፤ በአንድ አመት እስራት እንዲቀጣ ሰሞኑን ተበይኖበታል። (አዲስ ዘመን መስከረም 10 ቀን 1989ዓ.ም)
አዲሱ ትውልድ ለምን ቶሎ ይገረጅፋል
“ለተሙአላ ጤንነት ለእድሜ ብልጽግና የተመጣጠነ ምግብ ተመገቡ” ይለን ነበር እስከ ቅርብ ጊዜ ሳይንስ አሁን ግን ነገሩ የተገላቢጦሽ ሊሆን ምንም አልቀረውም። ከወላጆቹ ይልቅ እንደ ነገሩም ቢሆን የሚመገበውን ምግብ የተመጣጠነ ለማድረግ የሚጥረው አዲሱ ትውልድ “ፋፋ ጀነሬሽን” ለእርጅና ሲጣደፍ ልብ ሳይሉ አልቀሩም። አባት በ30ኛው የእድሜ ዘመኑ የወለደው ልጁ ገርጅፎ የአባቱ የረዥም ጊዜ ጓደኛ መስሎ ሲታይ የትላንትዋ ማሚቱም ገርጅፋ አምስት የወለዱ እናትዋን ልትመስል መከጀልዋን ሲታዘቡ “ዋ እቴ የዛሬ ዘመን ልጆች ቶሎ ይወድቃሉ (ያረጃሉ)” ሲባል መሰማቱ የተዘወተረ ሆኗል።
……………………………..
ለረዥም ጊዜ በእንስሳት ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚሳዩት “አይጦችም ሆኑ ሌሎች እንስሳት ዝቅተኛ የኃይል መጠን ያላቸውን ምግቦች ሲመገቡ ረዥም ዕድሜ ይኖራሉ። ጤነኛ ይሆናሉ” (አዲስ ዘመን ኅዳር 20 ቀን 1992 ዓ.ም)
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ሰኔ 27/2015