“የአክሲዮን ገበያ” ማለት አክሲዮኖች የሚሸጡበት እና የሚገዙበት ገበያ ማለት ነው። ሰፋ ብሎ ሲተረጐም ደግሞ “የካፒታል ገበያ” ይባላል። ምክንያቱም የሚሸጡት አክሲዮኖች የካፒታል ምንጭ ስለሚሆኑ ነው። አክሲዮን የሚሸጠው ለሻጩ ኩባንያ ካፒታል ለማመንጨት ታስቦ ነው። የካፒታል ገበያ ከአክሲዮኖች በተጨማሪ ሌሎች ባለቤትነትንና ባለዕዳነትን የሚገልጹ ሰነዶች የሚሸጡበትና የሚገዙበት ገበያ ነው።
በኢትዮጵያ ካፒታል በማሰባሰብ የገንዘብ ሥርዓቱን በአዳዲስ ፈጠራዎች በመደገፍ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ልማት የሚያጠናክር የካፒታል ገበያ ‘በካፒታል ገበያ አዋጅ ቁጥር 1248/2013’ ተቋቁሟል። በዚህ አዋጅ መሰረት ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሆነ “የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን” መስሪያ ቤት ተቋቁሞ ወደ ስራ ገብቷል። የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን የሰነድ መዋዕለ ንዋዮችን በማውጣት የግብይት ሥርዓቱን ፍትሃዊ፣ ቀልጣፋና ግልጽ በማድረግ የተሟላ የካፒታል ገበያ ስነ- ምህዳር የመፍጠር ስልጣን ተሰጥቶታል። ኢንቨስተሮችን በመጠበቅና ከለላ በመስጠት ኢንቨስትመንቱን ለማበረታታት ምቹ ሁኔታን መፍጠርና የካፒታል ገበያው ተዓማኒነት እንዲኖረው የማድረግ ኃላፊነትም አለበት።
በኢትዮጵያ የአክሲዮን ገበያው መኖሩ የበለጠ ግልጽነት እንዲሰፍንና የኢትዮጵያን የተፋጠነ ዕድገት የበለጠ ለማቀጣጠል የሚያስችል ተጨማሪ ካፒታል እንዲመደብ እንደሚያስችል ብዙዎች ያናሳሉ። ኢትዮጵያ መደበኛ የአክሲዮን ገበያ ሳይኖራት እንኳን፣ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ከአፍሪካ ሀገራት በአንደኛ ደረጃ ላይ ስለመቀመጧ በማሳያነት በመጥቀስ።
ገበያ መር ኢኮኖሚ የሚያራምዱ ሀገሮች ሁሉ የፋይናንስ መሠረተ ልማትን በአግባቡ ማሟላት ግድ የሚላቸው ሲሆን፣ የአክሲዮን ገበያዎችም የፋይናንስ መሠረተ ልማት ዋነኛ ምሰሶዎች ናቸው። ኢትዮጵያ መደበኛ የአክሲዮን ገበያ ሳይኖራት እንኳን እጅግ ሰፊ፣ ነገር ግን ብዙ ችግሮች ያሉበት ኢመደበኛ የአክሲዮን ግብይት የደራባት ሀገር እንደሆነች ይገለፃል። የአክሲዮን ገበያው ከመንግሥት የቁጥጥር ማዕቀፍ በእጅጉ ርቆ ወደፊት ቢጓዝም፣ አካሄዱ ግን አደገኛና አግባብነት የሌለው እንደሆነ ይነሳበታል። ከላይ የተዘረዘሩ የተለያዩ ምክንያቶች የኢትዮጵያን የአክሲዮን ገበያ ማቋቋም አስገዳጅና የማያደራድር ወሳኝ ሀገራዊ ጉዳይ ያደርጉታል።
መንግሥት ዘግይቶም ቢሆን በኢትዮጵያ የአክሲዮን ገበያ እንዲጀመር መወሰኑ በጣም የሚደገፍ ስለመሆኑ የተለያዩ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ይናገራሉ። ለማክሮም ሆነ ለማይክሮ ኢኮኖሚው ብዙ ጥቅም ይዞ የሚመጣ እና የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚያግዝ ነው። የአክሲዮን ገበያ ወይም ግብይትን ማቋቋም ግን ጥያቄ የማይነሳበትና ወቅቱ የሚጠይቀው ወሳኝ አገራዊ ጉዳይ ስለመሆኑም እንዲሁ።
በዚሁ ጉዳይ ላይ የምጣኔ ሃብት እና ኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ክቡር ገና እናደሚናገሩት፤ ካፒታል ገበያ ማለት አንድ ግለሰብ ገበያ ወጥቶ እንደሚገበያየው ሁሉ የአክሲዮን ገበያ ውስጥ የሼር ባለቤቶች ሼር የሚለዋወጡበት ቦታ ነው። አቶ ክቡር ገና ለአብነት ሲያነሱም የካፒታል ገበያ ሲቋቋም ባንኮች በእጃቸው ያለውን አክስዮን ይሸጣሉ፤ የገንዘብ ልውውጥ የሚካሄደውም ሼር በያዘው ግለሰብ ወይም ድርጅት አማካኝነት ነው። አንድ ሰው የአንድ ባንክ ድርሻ ቢኖረው በፈለገው ጊዜ ሄዶ አትርፎ ይሸጣዋል። እዚህ ጋር ግን መሰመር ያለበት ባንኩ ከመጀመሪያው አክስዮኑን ለባለአክሲዮኖች ስለሸጠው፤ የሽያጭ ሂደቱ በምንም መልኩ ባንኩ ጋር አይደርስም።
ስለዚህ የካፒታል ገበያ ሲቋቋም ሁለት ገበያ ይኖራል ይላሉ። አንደኛው ገበያ መጀመሪያ ድርጅቶች ሼር የሚያወጡት እና የሚሸጡት በአብዛኛው ለኢንቨስትመንት ባንክ እና ትልልቅ ገንዘብ በእጃቸው ያለ የመጀመሪያውን ድርሻ ይይዛሉ። ከድርጅቱ ሼር የገዙት ደግሞ ወደ ሁለተኛው ገበያ ይሄዱና በዚህ ገበያ ለማንኛውም ግለሰብም ሆነ ድርጅት አትርፈው ለመሸጥ በማሰብ ገበያ ላይ ያቀርቡታል። በአጠቃላይ መታወቅ ያለበት ጉዳይ በሁለተኛ ደረጃ የሚካሄደው የሼር ልውውጥ የተሻለ ነገር ሊያስገኝ ይችላል ወይም ከነጭራሹ ሊታጣ ይችላል። ስለዚህ በጥንቃቄ መካሄድ ያለበት ጉዳይ ነው።
በርካታ የሀገር ውስጥ ባንክ እና ኢንሹራንሶች ሲመሠረቱ እና ከምሥረታቸውም በኋላ የአክሲዮን ድርሻዎችን ሲሸጡ መቆየታቸውን በማስታወስ፤ የካፒታል ገበያን ከዚህ የተለየ የሚያደርገው፤ ይፋዊ በሆነ መልኩ ተደራጅቶ ቁጥጥር እየተገደረገበት በግልጽ መገበያየት ማስቻሉ ነው ይላሉ ባለሙያው።
ለሀገሪቱ ምን ይበጃል የሚለውን አቶ ክቡር ገና ሲናገሩ፤ በአብዛኛው አክሲዮን የሚገዛ ሰው አቅም ያለው ነው። በዚህም ሥርዓቱ ገንዘብ ያለውን ነው የሚጠቅመው ይላሉ። ሀሳቡም ገንዘብ ያለው በእጁ ሼር ይዞ ለኢንቨስትመንት ወይም ለንግድ ሥራ በአንድ ነገር ላይ ገንዘቡን ለማዋል በሚፈልግበት ጊዜ በተለይ በእጁ ጥሬ ገንዘብ ከሌለው ድርሻውን አውጥቶ በመሸጥ ገንዘብ እንዲያገኝ የሚያስችለው ነው። በሚያገኘው ገንዘብም ድርጅቱን ያስፋፋል ወይም ያሰበውን ኢንቨስትመንት ያደርጋል ማለት ነው። የካፒታል ገበያ ሳይንሱም ይሄ ነው። በአብዛኛው ግን ይህ ይሆናል የሚለው ሌላ ጥያቄ ነው ይላሉ።
ስለዚህ ሂደቱ የራሱ የሆነ አካሄድ አለው። በአንድ በኩል ከውጭ ያሉ ድርጅቶች ድርጅታቸው ኢትዮጵያ ውስጥ በሚያቋቁሙበት ጊዜ ወደ ሁለተኛው ገበያ ይሄዱ እና ሼር መለዋወጥ ይጀምራሉ። በዚህ ሂደት ሕዝብ ካሹን ወደ አክሲዮን በመለወጥ የንግድ እንቅስቃሴው ተሳታፊ ይሆናል።
በውጭ ሀገራት አሁን ትልልቅ ድርጅቶች የሚባሉት በተለያዩ ኢንቨስመንቶች ላይ የራሳቸውን ሼር ይገዛሉ። ምክንያቱም ሼራቸው እያደገ ወይም ዋጋው ከፍ እያለ በሄደ ቁጥር ጥቅማቸው እያደገ መሄዱን ስለሚያውቁ ሼር መግዛት ላይ ያተኩራሉ። በዚህ ሂደት የድርጅቶች አቅም ከፍ እያለ ይሄዳል ብለዋል።
ባለሙያው እንደ ስጋት የሚያነሱት፤ የሼር ዋጋው ከፍ እና ዝቅ ሊል የሚችለው በመረጃ ነው። ለአብነት ሲያነሱ አንድ በካፒታል ገበያ የሚገባ ድርጅት መሟላት ያለበት እና ግዴታዎች አሉ። እነዚህ ግዴታዎችና መመሪያዎች ከሀገር ሀገር የሚለያዩ የተለያዩ መስፈርቶች አሏቸው። እነዚህን ደንቦች እና መመሪያዎች የሚያወጣ፤ የሚያስተዳድር እና የሚቆጣጠር አካል አለ። ግብይቱም በሕዝብ መካከል የሚካሄድ ስለሆነ ከማጭበርበር የጸዳ እንዲሆን ጠንካራ ቁጥጥር ያስፈልገዋል ብለዋል።
ለአብነት ብንወስድ መረጃ ያለው ባለአክሲዮን ድርጅቱ መክሰሩን እያወቀ ሼሩን አሳልፎ ሊሸጠው ይችላል። ይህ እንግዲህ በገዢው ላይ የሚያስከትለው ኪሳራ ስለሚኖር ይህ ከመሆኑ በፊት የሚከለክሉ ሕጎች እና ደንቦች ስላሉ በደንብና መመሪያዎቹ መሰረት ሰዎችን ከኪሳራ መታደግ ይገባል። ሆኖም ወደ ስራ ከመገባቱ በፊት መጀመሪያ በሥነ ሥርዓት ለሕዝቡ ግልፅ በሆነ መንገድ መቀመጥና ሕዝቡም ዝርዝር መመሪያና ደንቦቹን ሊያውቃቸው ይገባል።
በሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር የሆኑት ዶክተር ሞላ ዓለማየሁ በበኩላቸው፤ አሁን ባለው ዘመናዊ የኢኮኖሚ ሥርዓት ውስጥ የካፒታል ገበያ መምጣት ጥያቄ የሚነሳበት አይደለም። ቴክኖሎጂ ለማሳለጥ እና ኢኮኖሚው በታሰበው ልክ በፍጥነት እንዲያድግ የዚህ ገበያ ሥርዓት ጥቅሙ ዘርፈ ብዙ ነው። ነገር ግን አካሄዱ በደንብ ካልተያዘ በኢኮኖሚ ዕድገቱ ላይ ጫና ይዞ ሊመጣ ይችላል ይላሉ።
ዶክተር ሞላ እንደሚሉት የካፒታል ገበያው መጀመር የካፒታል ፍሰቱ በደንብ እንዲንሸራሸር ያደርጋል። በተለይ ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባውን የካፒታል ፍሰት ያሳልጣል። ይህ ከሆነ ደግሞ ካፒታል የሚፈልጉ የኢኮኖሚ ዘርፎች አስፈላጊውን ግብዓት ያገኛሉ ማለት ነው። በዚህም በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አይነተኛ ሚና ይጫወታል። ይህ ሲሆን ደግሞ የተሻለ ዕድገት እና ብልጽግና ይመጣል።
ሆኖም ኢትዮጵያ ውስጥ የካፒታል እጥረት በመኖሩ የካፒታል ገበያ መፈጠሩ ያለውን የካፒታል ማነቆ ለመቅረፍ በር ይከፍታል። የካፒታል ገበያው መረጃን መሰረት በማድረግ እና በገበያው ውስጥ ያለውን የፍላጎት እና የአቅርቦት እንቅስቃሴ በማየት የካፒታል ዋጋውን ይታመናል፤ የሚቋቋሙ አክሲዮኖች ሁሉ የዛን ጊዜ ዋጋቸው ተመን ይወጣለታል። በእያንዳንዱ ጊዜ ከፍ እና ዝቅ ሊል ስለሚችልም ይህንን ሁሉ የሚቆጣጠር የገበያ ሥርዓት ይኖረዋል ይላሉ።
በየትኛውም የኢኮኖሚ ዘርፍ ላይ መረጃ በጣም ወሳኝ ነው። ብዙ ሀገሮች እድገታቸው የተመሰረተው በካፒታል ገበያ ላይ ነው። ዛሬ አደጉ የምንላቸው አሜሪካ እና አውሮፓ ሀገራት የእድገታቸው መሠራት ይህ ነው። ካፒታል አላገኝም ብሎ የተቀመጠ ሰው ሁሉ ወደ ኢንቨስትመንት ስለሚገባ በዚህ ሥርዓት የሚንቀሳቀሰው ካፒታል መጠኑ እጅግ ከፍተኛ ነው። ለማንኛውም ግለሰብ ግልጽ በሆነ መልኩ በምን ያህል ዋጋ/ወለድ እንደሚያገኝ እና ትርፍ እንዲሚሰላለት መረጃው በየደቂቃው ስለሚወጣ ሁሉም በካፒታል ማርኬቱ ውስጥ የመሳተፍ ፍላጎት ያድርበታል።
ካፒታል ገበያ ሲባል ገንዘብ ነው። አንድ ነጋዴ አንድ ነገር ገዝቶ አትርፎ እንደሚሸጠው ሁሉ በዚህም የገበያ ሥርዓት ጨዋታው የሚካሄደው አክሲዮን ላይ ነው። ሼር በመግዛት እና ዋጋ ሲጨምር መልሶ በመሸጥ የሚደረግ የገበያ ሥርዓት ነው። ለኢኮኖሚው እጅግ በጣም በብዙ መልኩ ጠቀሜታ አለው። ነገር ግን ከፍተኛ ጥንቃቄ ይፈልጋል ብለዋል።
ዶክተር ሞላ እንደሚያብራሩት በአንዳንድ ሀገራት መልካም አበርክቶ እንዳለው ሁሉ ችግሮችንም ፈጥሯል። በተለይ በ90ዎቹ መጨረሻ በሩቅ ምስራቅ ሀገሮች ላይ የተፈጠረው ችግር ቀላል አልነበረም። ይህንን እንደ ልምድ ወስዶ የካፒታል ገበያውን በትክክል ለመምራት የሚፈልገውን ውጤት እንዲያመጣ ምን ግብዓት ይፈልጋል የሚለውን መለየት አስፈላጊ ነው። ከህግ አንፃር ብዙ ነገሮችን ደግም ማየት ይጠይቃል። እንዲሁ ዝም ብሎ አሁን ባለው የንግድ ወይም የገበያ ሥርዓት ውስጥ የሚገባ ስላይደለ በቂ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተሰርተው ወደ ትግበራ ቢገባ የተሻለ ስለመሆኑ አበክረው ተናግረዋል።
የአክሲዮን ገበያ ሶስት የባለድርሻ አካላት አሉ የሚሉት ዶክተር ሞላ ሕዝብ፣ መንግስት፣ እና ባለሀብቱ የራሳቸው ሚና እንዳላቸው ይጠቁማሉ። መንግሥት የማሰለጥ እና ሁኔታዎችን የማመቻቸት የተሻለ የማድረግ ሥራውን ይሰራል፤ ባለሀብት ደግሞ ገንዘቡን ይመድባል። ሕዝብ በአክሲዮኑ ሽያጭ ይሳተፋል። ስለዚህ ይህ ሁሉ መቀናጀት ሲችል ነው በትክክል የሚሰራው እና ውጤታማ የሚሆነው።
የአክሲዮን ገበያው ውጤታማ የሚሆነው እያንዳንዱ አካል ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት ሲችል በመሆኑ መንግሥት ወደ ሥራ ከመግባቱ በፊት የሚያሰራ ፖሊሲ እና ስትራቴጂ ማውጣት ይጠበቅበታል። መንግሥት የመሪነት ሚናውን ይይዛል፤ ሌሎች ደግሞ የራሳቸውን ኃላፊነት ከተወጡ ፍሬያማነቱ የሚያጠያይቅ አይደለም ብለዋል።
አሁን ሀገሪቱ ለካፒታል ገበያው የሚሆን ሕግ የላትም፤ የአክሲዮን ድርጅት እንኳ ባለአክሲዮኖችን ክዶ ቢገኝ ለመዳኘት የሚሆን ሕግ የለም። ይህንን ሁሉ መስተካከል እንዳለበትና ችግር ተከስቶ ቢገኝ እንኳን በምን አግባብ መፍታት ይቻላል የሚለውን መንግሥት በትኩረት ወስዶ መስራት ይኖርበታል። ከዚህ ባሻገር የአክሲዮን ገበያውን በአንድ ጊዜ መልቀቅ እና ደረጃ በደረጃ እንዲተገበር ማድረግ ያስፈልጋል። የቁጥጥር እና ክትትል ሥርዓቱንም ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑንም ዶክተር ሞላ አስምረውበታል።
በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን የካፒታል ገበያ ሲኒየር አማካሪ የሆኑት አቶ ሰለሞን ገብሬ በበኩላቸው፤ በ2016 ይጀመራል የተባለው የአክሲዮን ገበያ በተባለው ጊዜ ለማስጀመር ላለፉት አንድ አመት ተኩል ዝግጅት እየተደረገ ቆይቶ በአሁኑ ወቅትም አብዛኛው የዝግጅት ሥራ እየተጠናቀቀ ይገኛል ብለዋል።
አቶ ሰለሞን ባለስልጣኑ የካፒታል ገበያን የሕግ ማእቀፍ በተመለከተ በርካታ ሥራዎች መሰራታቸውን የገለጹ ሲሆን ከአንድ አመት ተኩል በፊት በወጣው አዋጅ መሰረት ዝርዝር ነገሮችን የሚይዙ 10 መመሪያዎችና ሁለት ደንቦች ረቂቅ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል። ከመመሪያዎቹ ውስጥ ሶስቱ የሕዝብ አስተያየት ተሰብስቦባቸው በአቃቤ ህግ ማስመዝገብ የቀረ ሲሆን አንዱ ደንብም ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ለመጨረሻ ውሳኔ እንደተላከ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ገና እየተጀመረ በመሆኑ በዘርፉ ለሚሳተፉ ኩባንያዎች፣ ለህብረተሰቡ እንዲሁም አገልግሎት ለሚሰጡ አካላት ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ በመሰራት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል። በዚህም ከፋይናንስ ተቋማት፣ ከባንኮች እንዲሁም በዘርፉ ላይ ፍላጎት ያላቸው 600 ሰዎች ስልጠና እንዲወስዱ መደረጉን አብራርተዋል።
በተጨማሪ ባለስልጣኑ ትኩረት ሰጥቶ ከሚሰራባቸው ጉዳዮች አንዱ አገልግሎቱ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይወሰን በተለያዩ ክልሎችና አካባቢዎች እንዲስፋፋ መሆኑን ገልጸው በቅርቡም አራት አካባቢዎች ላይ ካፒታል ገበያ ምን ጠቀሜታ እንዳለውና በተለያዩ ዘርፎች ላይ ያሉ ዜጎች እንዴት ሊጠቀሙት እንደሚገባ ስልጠና ይሰጣል ብለዋል። የካፒታል ገበያ ኢንቨስተሮች በካፒታል ገበያ ለመሳተፍ ከፍተኛ ፍላጎት እያሳዩ ነው ያሉት አቶ ሰለሞን፣ ባለፉት 6 ወራት ብዙ ተሳትፎዎች መታየታቸውን አብራርተዋል።
በአጠቃላይ ምሁራኑ እንደተነገሩት፤ ለአክሲዮን ገበያው የሚሆን ከባቢያዊ ሁኔታ መፍጠር የግድ ይላል። ከሕግ አኳያ የንግድ ሕጉ በዛ መቃኘት አለባት። የአክሲዮን ገበያ ፍጥነቱ ከፍተኛ ስለሆነ ለአጭበርባሪዎች የመገለጥ ዕድሉ ሰፊ ነው ። ስለዚህ ይህንን የሚቆጣጠር እና የሚከታተል ጠንካራ የሆነ አካል ሊኖር ይገባል። ይህ ከሆነ በ2016 የሚጀመረው የአክሲዮን ገበያ ለሀገርም ብሎም የእንዳንዱን ዜጋ ሕይወት ከመለወጥ አንጻር ፋይዳው ከፍተኛ እንደሚሆን ምሁራኑ በጋራ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ሰኔ 27/2015