‹‹ነጋ አልነጋ›› ብሎ ከየቤቱ የወጣው ነዋሪ የህንጻውን ዙሪያ ከቦታል። እንደው ‹‹ከቦታል›› ይባል እንጂ ‹‹ወሮታል›› ቢባል ሳይሻል አይቀርም ። ቦታው ‹‹የሰው ነጭ›› ይሉት የሚታይበት ነው ። ወጣቱ፣ ሴቱ፣ ጎልማሳው ፣ ሽማግሌና አሮጊቱ አይኑን እያሸ ካሰበው ከተገኘ ሰአታት ተቆጥረዋል። ሁሉም ከጣፋጭ ዕንቅልፉ ፣ ከሞቀ መኝታው ተገዶ መነሳቱ ያስታውቃል። ያኮረፉ፣ ፊቶች፣ የሚያዛጉ አፎች፣ ዕንቅልፍ ያልጠገቡ ዓይኖች ጎን ለጎን ይጋፋሉ።
ብርድ ነው። ለሌቱን ሲረግጠው ያደረው ዝናብ ‹‹በቃኝ›› ያለ አይመስልም። በነጎድጓዱ እያስፈራራ፣ በካፊያው መልዕክት ‹‹መጣሁላችሁ›› እያለን ነው። የአካባቢው ህንጻዎችና የንግድ ሱቁች ዕንቅልፍ ላይ ናቸው። አልፎ አልፎ ‹‹ሽው›› የሚሉ ከባድ መኪኖች የመንገዱን ጭርታ እየሰበሩት ያልፋሉ። አብዛኛው የክረምቱን አየር ለመጋፋት ካፖርትና ፣ ፎጣ ደርቧል። ብርድ ልብስ ቢጤ የተጎናጸፈውም ብዙ ነው።
እኔን ጨምሮ በርከት ያልን ጎረቤታሞች ፊትና ኋላ እየተመራራን በስፍራው ደርሰናል። ከየቤታችን ለመውጣት የመጨረሻው ቀጠሯችን ከለሊቱ አስር ሰአት ነበር። የዘንድሮ ግብር ጉዳይ ከማነጋገር አልፎ የዕለት ጭንቀት ከሆነ ሰነብቷል። የክፍያው መጠን፣ የኢኮኖሚው ችግር የወረፋወና ውጣወረዱ ነገር የሁሉ ሰው ራስ ምታት ሆኗል። ጉዳዩ የግብር ጉዳይ፣ ለዛውም አይቀሬው ግዴታ ነው ስለተባለ ሁሉም ወገቡን አስሮ ለክፍያውተሯሩጧል።ከየአአቅጣጫው የሚሰማው ወሬ ደግሞ መልከ ብዙ ነው። ግብር ክፈሉ የሚለው መረጃ ከሚመለከታቸው አካላት ለነዋሪው የደረሰው በቅርብ ቀን ነው ።
ከዚሁ ተያይዞ ጉዳዩን በቅጡ ያልሰማና ከነጭራሹም ያላወቀው ይበረክታል። መረጃው ኖሮት ግብር ልክፈል፣ ግዴታዬንም ልወጣ ያለው ደግሞ በወጉ አይስተናገድም። በቂ መረጃ የሚሰጠው አካል ያለመኖር፣ ባግባቡ የሚቀበለው አለማገኘት የየወረዳ ጽህፈት ቤቶቹን ደጃፍ ሲያተራምሰው ይውላል። እውነቱን ለመናገር ከአገልጋዩ ይልቅ ‹‹ግዴታዬን ልወጣ፣ ሕግንም ላክብር›› የሚለው ነዋሪ ሲጎዳ ሰንብቷል። ለቀናት ሲንገላታ ውሎ ያለአንዳች ፋይዳና በቂ መስተንግዶ ውጤት አልባ የሆነውን ቤት ይቁጠረው።
ከቤት ግብር፣ከካርታ ይዞታና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር ቀድሞ በእጅ መግባት የሚኖርበትሰነድ ከሚቀርበው ማስረጃ ጋር አለመያያዙ ግብር ከፋዩን ሲያንገላታው ቆይቷል። ለምሳሌ ቤቱ በሽያጭ፣ በውርስ፣ አልያም በዝውውር ተገኝቶ ከሆነ ሂደቱ አስቀድሞ ሲከናወን ከሚመለከተው አካል ይህንኑ የሚያስረዳ ደብዳቤ ሊሰጥ ይገባል። ግዴታውን መወጣት ያለበትም የሚመለከተው ክፍል ነበር።
በዚህ የግብር መክፈያ ጊዜ ግን አስቸጋሪ የሚባል አሰራር ተስተውሏል። ይህን መሰሉን ሰነድ ተመሳሳይ ምክንያት ላላቸው የቤት ባለቤቶች ይሰጥ የነበረው ጉራማይሌ በሆነ መልኩ ነበር። ለአንዳንዱ ተገቢው ማስረጃ ተሰጥቷል። ለሌላው ደግሞ ይህ አይነቱ እውነታ ፈጽሞ አልተሞከረም።
በግብር መክፈያ ጊዜ ወረዳው ላይ ሊያልቅ የሚገባው ጉዳይ ወደክፍለከተሞች እየተመለሰ ማስረጃው በአስቸኳይ እንዲመጣ ሲደረግ ቆይቷል። ችግሩ እንዲህ መሆኑ ብቻ አይደለም። የተባለውን የማረጋገጫ ደብዳቤ ለማምጣት የክፍለከተሞች አገልግሎት የሚወሰነው ለወረዳ ነዋሪዎች በተቀመጠው የቀን ተራ መሰረት ብቻ ነው። ወረፋ ጠብቀው ተራቸው ደርሶ ደብዳቤውን እንዲያመጡ የሚታዘዙ ነዋሪዎች ስፍራው ሲደርሱ እንዳሰቡት አይስተናገዱም። አጋጣሚ ሆኖ የወረዳቸው ተራ ካልሆነ ከበር እንዲመለሱ ሆኖ ለሳምንት ቀናቸውን እንዲጠብቁ ይገደዳሉ።
ይህ አይነቱ ክፍተት ተመልሰው የጀመሩትን ጉዳይ እንዳያጠናቅቁ ለማድረግ አስተዋጽኦው የጎላ ነው። እንዲህ ከመሆኑ በፊት ግን የሚመለከታቸው አካላት የሚጠበቅባቸውን አስፈላጊ ማስረጃ ለተገቢው አካል መስጠት በተገባቸው ነበር። ወዳጆቼ! የመነሻዬን ፈጽሞ አልዘነጋሁም። አስቀድሜ እንዳልኳችሁ ከጎረቤቶቻችን ጋር ሰአቱ ደረሰ ፣ አልደረሰ ስንል ቆይተን ከየቤታችን ወጥተናል። ልክ ከለሊቱ አስር ሰአት ላይ። ጨለማው በወጉ አልገፈፈም፣ በጣም ይበርዳል ፣ ሌቱን ያደረበት ዝናብ ጋብ ቢልም አሁንም ማስፈራራቱን ቀጥሏል። በዚህ ሰአት መውጣት ያስፈራልና ግማሹ ወደል ዱላ፣ ጨብጦ ሌላው በየኪሱ ተለቅ ተለቅ ያለ ድንጋይ አኑሯል።
አስፓልቱን ተሻግረን ከወረዳችን ጽህፈትቤት ጥግ ለመድረስ ጥቂት ርምጃዎች ሲቀሩን የሁላችንም ዓይን በድንጋጤ ፈጦ ቀረ ። ‹‹ወፈ ሰማይ›› የሚመስለው ነዋሪ በቦታው ደርሶ እየተተራመሰ ነበር። ‹‹ጉድ ፈላ!›› በኛ ቤት እኮ ! ከሁሉም ቀድመን በአንደኝነት መገኘታችን ነበር። ከእኛ በፊት ይህ ሁሉ ሰው ይቀድመናል የሚል ግምት አልያዝንም።
በግራ መጋባት ተፋጠን ተያየን። ከስራ ቀርተን፣ ዕንቅልፋችንን አጥተን ወረፋ ተቀድመን እንዴት ይሆናል? አንዳች ነገር ስላለመፈየዳችን አንዳችንም መመለስ የሚቻለን አልሆነም። እየተገፋፋን ፋይል ይዘው ስምና የቤት ቁጥር ከሚመዘግቡት ዘንድ ደርሰን ማንነታችንን አስከተብን።
ለወጉ ስም ለማስመዝገብ ካልሆነ በቀር ያሰብነው እንዳማይሳካ ሁላችንም አልጠፋንም። አዎ! የፈራነው አልቀረም። የስማችን ዝርዝር ከብዙ መቶዎች ስም ኋላ መመዝገቡ ውጤት አላስገኘም። ሌቱን እዛው አንግተን፣ የጠዋቷን ጸሀይ ተቀብለን፣ የቀትሩን ወበቅ ሸኝተን ፣ ጨረቃዋ በላያችን ልትወጣ ስትዘገጃጅ በ‹‹ደህና እደሩ›› ሰላምታ ተለያየን።
ተስፋ አልቆረጥንም። ከቀናት በኋላ የሌሊቱን የመውጫ ሰአታችንን በሁለት ሰአት አሳንሰን ከወረዳችን ጽህፈትቤት ደጃፍ ደርሰን ተኮለኮልን። በወቅቱ ያገኘናቸው አቅመ ደካሞች፣ ሴቶችና ልጅ ያዘሉ እናቶችን ነበር። እኔ በበኩሌ ዕንባ ያንቀኝ፣ ሆድ ይብሰኝ ይዟል። ከክፍለ ከተማው እንዲመጣ የታዘዝኩትን ደብዳቤ ለማግኘት ስንገላታ፣ ስሰቃይ ከርሜያለሁ። ደግሞም ለደብዳቤው ክፈይ የተባልኩት የአምስት መቶ ብር ምክንያት ፈጽሞ አልገባኝም።
ደግነቱ እኔ ግብር ካልከፈልኩ እያልኩ ፣ የሚመለከታቸውን እባካችሁ ብር ተቀበሉኝ›› ስል በመከራ የባጀሁባቸው ፈታኝ ቀናት አልፈው ዛሬን በነበር እያወራሁት ነው። ልክ እንደኔው ሁሉ በዚህ መንገድ ያለፉ ግብር ከፋዮች እልፍ እንደሚሆኑ ግን አልጠራጠርም ። ሕግ አክብረን ግዴታችንን እንወጣ ፣ የመንግሥትን ቃል እናክብር ባልን በእንግልት መሰቃየታችን ተገቢ አልነበረም።
ከቀናት በአንዱ ከጥቂት ሰዎች ጋር ሻይ ቡና እያልን ስለጉዳዩ ማውጋት ይዘናል። ሁላችንም በዘንድሮው ግብር ክፍያ ያለአግባብ ስንገላታ የቆየን ቁስለኞች ነን። እኛ እኮ! በድንገቴው የግብር ክፈሉ ዙሪያ ያላየነው የለም። የአሰራሩ ዝርክርክነት፣ የአንዳንድ ስራ አስፈጻሚዎች አለመታመንና ግልጽ የወጣውን የሙስና ጉዳይ ሁሉ ታዝበናል።
በውይይታችን መሀል ጥቂት የማይባሉት ከሌሎቻችን በተለየ በአንድ ጉዳይ ላይ ይብከነከናሉ። እነሱ ገና በጠዋቱ የግብር ክፈሉ ጭምጭምታ ሲሰማ ሕግ አክብረው በጊዜው የከፈሉ ናቸው። ሰዎቹ እንደኔና መሰሎቼ ሌቱን ከጅብ ባይጋፉም ጥቂትም ቢሆን እንግልት አግኝቷቸዋል። በእነሱ ዕምነት የሚጠበቅባቸውን ግዴታ በአግባቡ ተወጥተዋልና ሽልማት ጭምር ይገባቸው ነበር። ነገሩ ግን ‹‹ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ›› ሆኖ ታሪኩን ቀይሮታል። በጊዜና በወቅቱ ሕግ አክብረው ግብር መክፈላቸው እንኳን ሽልማት ምስጋና አላስቸራቸውም።
አዎ! እውነት ነው። እነሱ በጠዋቱ የተጠየቁትን የቤት ግብር በአግባቡ ከፍለዋል። ‹‹ከፍለዋል›› ሲባል ግን ግብሩን ከነገበሩ እንጂ ለብቻው አልነበረም። አስቀድሞ የተተመነላቸውን መጠን ቢያውቁትም ክፍያውን ሲፈጸሙ ቅጣት ተብሎ ከታከለው ተጨማሪ ገንዘብ ጋር ሆኗል። ስለከፈሉት ቅጣት ተብዬ ጉዳይ ስለምን ብለው መጠየቃቸው አልቀረም። ምላሹ አዲስ ነገር የለውም። ሕግ አክብረው በወቅቱ የመክፈላቸው እውነት የቅጣት ሽልማትን አጎናጽፏቸዋል። ‹‹ሕግን ያከበረ እንዲህ ይቀጣል›› እንዲሉ።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 26 ቀን 2015 ዓ.ም