ስለ ትምህርት ቤቶች ችግር ሲወሳ ቅድሚያ ወደ አዕምሮ የሚመጣው በገጠር የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ያሉበት ደረጃ ነው። በተለይ ደግሞ ዳስ ተጠልለውና ድንጋይ ላይ ቁጭ ብለው የሚማሩ ተማሪዎች ትዝ ይላሉ። ይህንንም የተመለከቱ አንዳንድ አገር ወዳዶች ተማሪዎቹ በተሻሉ ትምህርት ቤቶች ውስጥ እንዲማሩ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ አድርገዋል። የዛሬን አያድርገውና በጦርነት ፈረሰ እንጂ አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ በአማራ ክልል በዋግ ኽምራ ዞን ፃግብጂ ወረዳ ያሰራው ትምህርት ቤት ተጠቃሽ ነው። ትምህርት ቤቱ በዳስ ጥላ ሲማሩ የነበሩ ሕፃናት በጥሩ የመማሪያ ክፍሎች ውስጥ እንዲማሩ አድርጓቸው ነበር።
በቀዳማዊ እመቤቶች በኩል የተሰሩ ትምህርት ቤቶችም እንዲሁ የበርካታ ተማሪዎችን የመማር ችግር ፈተዋል። በእርግጥ ህብረተሰቡም ሆነ ግለሰቦች ብሎም ተቋማት የትምህርት ቤት ግንባታ ላይ መሳተፍ የጀመሩት ዛሬ አይደለም። የትምህርት ቤቶች ግንባታ ተሳትፎው ትናንት ዘመናዊ ትምህርት ባልተጀመርበት ጊዜ ሁሉ ነው። በቆሎ ትምህርት ቤቶች ግንባታ ሂደት ውስጥ ሕዝብ የአንበሳውን ድርሻ ይዟል። ዛሬ ደግሞ ይህን ፈለግ ተከትለው ሌሎች ግንባታውን አስቀጥለውታል።
ይህንን የማድረጋቸው ምክንያት ደግሞ አንድና አንድ ነው። ይኸውም ትምህርት ቤቶችን በተሻለ ደረጃ በመገንባት የተሻለ ትውልድ መፍጠር ሁነኛ መፍትሄ መሆኑን በማግኘታቸው ነው። ከዚህም ጋር ተያይዞ ትምህርት ቤቶችን መገንባትና መሠረተ ልማቶቻቸውን የማሻሻል ተግባር በሀገር አቀፍ ደረጃ ትልቅ የንቅናቄ ሥራ ሆኖ ቀጥሏል።
በዚህም ግለሰቦችና ተቋማት እንዲሁም ማህበረሰቡ ተረባርቦ የትምህርት ተደራሽነትና ጥራትን በእኩል ደረጃ ለማምጣት በመንግሥት ደረጃ እቅድ ተይዞ ታላቁ ሀገራዊ የሕዝብ ንቅናቄ ተጀምሯል። ምክንያቱ ደግሞ መንግሥት ተደራሽነት ላይ ሲሰራ ጥራቱ ሊጓደል ይችላልና ያንን ማከም አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው። እንዲም ሆኖ ግን እንደመንግሥት ሁለቱንም ለመተግበር የአቅም ውስንነት ይታያል። ለዚህም ማሳያው ባለፉት ዓመታት በነበረው የትምህርት ጉዞ ተደራሽነት ሲሰፋ ጥራቱ መጓደሉ ነው። እናም ይህን ውስንንት ለማከም እንደሀገር ሕዝባዊ ንቅናቄ በማድረግ ለመሥራት ውጥን ተይዟል።
እ.ኤ.አ በ2018 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት የሳይንስ እና የባህል ተቋም /ዩኔስኮ/ ባወጣው መረጃ መሠረት በዓለም ዙርያ የሚገኙ 258 ሚሊዮን የሚሆኑ ሕጻናት የሚሄዱበት ትምህርት ቤት የላቸውም ወይም ምንም እውቀት አልቀሰሙም። ይህ ቁጥር በዓለም ውስጥ ከሚገኙ ወጣቶች መካከል 17 በመቶ ያህሉን ይሆናል። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ 258 ሚሊዮን ሕጻናት መካከል 90 በመቶው የሚገኙት ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት እና በእስያ ነው። ኢትዮጵያም ከነዚህ ሀገራት ተርታ ትሰለፋለች። ለዛም ነው ግለሰቦችና ተቋማት ጭምር በዚሁ ጉዳይ እንዲሳተፉ አቅጣጫ የተቀመጠው።
ከዚህ ጋር በተያያዘ በተሰራ ሥራ ተማሪዎች በአቅራቢያቸው ትምህርት ቤት እንዲያገኙ ሆነዋል። በርከት ያሉ ትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎችም ተፈጥረዋል። እነዚህ ትምህርት ቤቶች የተወሰነ ግብዓት ያሟሉ ብቻ መሆናቸው ግን አሁንም የትምህርት ጥራትን ጥያቄ ውስጥ እንዳስገባው ቀጥሏል። ብዙ ነገሮች እንደሚጎድላቸውም የትምህርት ሚኒስቴር በተደጋጋሚ የሚያወጣቸው መረጃዎች ያመላክታሉ።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ-ካርታ ጥናትና ሌሎች በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች የትምህርት ጥራት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን በመረጃ አስደግፎ ገልጿል። ለዚህ ችግር ዋነኛ መንስኤው ደግሞ ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር ምቹ አለመሆናቸው ጠቁሟል። የኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች ያሉበት ነባራዊ ሁኔታም ይህንኑ እንደሚያሳይ መረጃው ያመለክታል።
ለምሳሌ በሀገሪቱ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 33 ነጥብ 2 በመቶ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና 55 ነጥብ 67 በመቶ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ብቻ የንጹህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት አላቸው። ከነዚህ ውስጥ 21 ነጥብ 3 በመቶ በአንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም 49 ነጥብ 1 በመቶ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በቀጥታ የቧንቧ ውሃ ተጠቃሚ ሲሆኑ የተቀሩት ትምህርት ቤቶች ምንም አይነት የውሃ አቅርቦት አያገኙም።
በሌላ በኩል ደግሞ 37 በመቶ አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ እንዲሁም 43 በመቶ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ብቻ የመፀዳጃ አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆን 29 ነጥብ 4 በመቶ አንደኛ እና መካከለኛና 74 ነጥብ 5 በመቶ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ብቻ ናቸው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ የሆኑት። ይህም ትምህርት ቤቶች በቴክኖሎጂ የተደገፈ የ21ኛው ክፍለ ዘመን የትምህርት ክህሎትን እንዲያዳብሩ ለማድረግ የሚሰራውን ሥራ ፈታኝ አድርጎታል።
ከዚህ ቀደም የትምህርት ቤቶችን ቁጥር ከማሳደግ አንፃር የሚያበረታታ ሥራ የተሰራ ቢሆንም የትምህርት ቤት ቁጥር መጨመር በራሱ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ያለው አስተዋጽኦ እንደተጠበቀ ሆኖ ትምህርት ቤቶቹ ደረጃውን ጠብቀው እንዲመሰረቱ ከማድረግ አንፃር ሰፊ ክፍተት ነበረበት። ለዚህም የትምህርት ፋሲሊቲና ግብዓቶች እንደለብ አለመሟላት የራሱን አስተዋፅኦ አበርክቷል።
ምንም እንኳን የተማሪ መፃህፍት ጥምርታ አንድ ለአንድ መሆን እንዳለበት ቢታመንም አሁንም ድረስ የአንደኛ፣ መካከለኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የተማሪ መፃህፍት አንድ ለአንድ አይደለም። ጥምርታውም ከክልል ክልል ይለያያል። ይህ ደግሞ በአሁኑ ጊዜ የትምህርት ጥራትን ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አሳድሯል።
ከዚህ ባሻገር ተማሪዎች በክፍል ውስጥ ከሚሰጣቸው ትምህርት በተጨማሪ የተማሩትን ትምህርት በተሻለ ደረጃ እንዲገነዘቡና እንዲመራመሩ በስታንዳርድ መሠረት የተሟላ ቤተ መጻህፍት ያስፈልጋል። አብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች በግብዓት የተሟላና ስታንዳርዱን የጠበቀ የቤተ መፃህፍት አገልግሎት የላቸውም። ያላቸውም ቢሆኑ በስታንዳርዱ መሠረት በግብዓት የተሟሉ አይደሉም።
ተማሪዎች በንድፈ ሃሳብ የተማሩትን ትምህርት በተሻለ መልኩ እንዲረዱ ከማገዝ በተጨማሪ የተማሪዎችን የፈጠራ ችሎታ በማሳደግ በኩል ቤተ ሙከራዎች ትልቅ አስተዋፅኦ አላቸው፤ አስፈላጊም ናቸው። ተማሪዎች ንድፈ ሃሳቦችን የመገምገምና የመተንተን ችሎታቸውን የሚያበለጽጉት በእነዚህ ቤተሙከራዎች ውስጥ ነው። በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስታንዳርድ ውስጥ ለትምህርት እርከኑ አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶችን ያሟሉ ቤተ-ሙከራዎች እንዲኖሩ ይጠበቃል። እንደመረጃዎች ከሆነ ግን አስፈላጊውን አገልግሎት ሊሰጡ የሚያስላቸውን ቁሳቁሶች አሟልተው የተገኙ ቤተ-ሙከራዎች ያሏቸው 59 በመቶ አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሲሆኑ፤ 79 በመቶ የሚሆኑት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ብቻ ናቸው።
ሌላው መምህራን በሚያስተምሩት የትምህርት ዓይነት የትምህርት መርጃ መሳሪያ የሚያዘጋጁበትና ትምህርት ቤቱም ከአካባቢ ቁሳቁስ ከሚሰሩ አጋዥ የመማሪያ ማስተማሪያ ቁሳቁሶች በተጨማሪ የፋብሪካ ምርቶችን በመግዛት የሚያደራጁበት ማእከል ሲሆን፤ መምህራን ከማእከሉ የትምህርት መርጃ መሳሪያዎችን እየተዋሱ የሚያስተምሩትን ትምህርት ይበልጥ ተጨባጭ በማድረግ የተማሪዎችን የትምህርት አቀባበል ለማሳደግ ይገለገሉበታል። ይህም ብዙ ጉድለት ያሉበት እንደሆነ በጥናት ታይቷል።
የትምህርት ቤቶች መሰረተ ልማት ችግር ትምህርት ቤቶች በስታንዳርዱ መሠረት ማሟላት ያለባቸውን መሠረተ ልማቶች እና ፋሲሊቲዎች አሟልተው ከመከፈት ይልቅ ትምህርትን ተደራሽ ለማድረግ ሲባል ስታንዳርዱን ያላሟሉ ትምህርት ቤቶች በመክፈት አገልግሎት እንዲሰጡ በመደረጉ እና ችግሮቹ በሂደት እየተቀረፉ ባለመምጣታቸው የተፈጠረ እንደሆነም መረጃው አስቀምጧል።
እናም መፍትሔው ምንድን ነው? ከተባለ ሀገራዊ የሕዝብ ንቅናቄውን በተሳካ ሁኔታ ማከናወን እንደሆነ ብዙዎችን ያስማማል። ንቅናቄው መሠረታዊ በሆኑ ችግሮች ላይ በማተኮር እና ሁሉንም የትምህርት ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል በትኩረት ለመስራት የሚያስችል እንደሆነም ታምኖበታል።
የትምህርት ቤት መሠረተ ልማት ለትምህርት ጥራት ያለውን ፋይዳ ማንም ይረዳዋል። ሁሉንም የትምህርት ባለድርሻ አካላት በማስተባበር መፍታት ካልተቻለ ግን አደጋው የከፋ እንደሆነ ሁሉንም ያስማማል። ምክንያቱም ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች መማሪያ ማዕክል ከመሆን ይልቅ መዋያ ብቻ እየሆኑ በመምጣታቸው ነው። ይህ ደግሞ የትምህርት ሥርዓቱን በብዙ መልኩ ይጎደዋል። ለዚህም የ2014 ዓ.ም የተማሪዎችን የ12ኛ ክፍል ፈተና ውጤት ማየት ብቻ በቂ ነው።
ስለዚህ የተለያዩ አማራጮችን በማየት የትምህርት ቤት መሠረተ ልማቶችን በስታንዳርዱ መሠረት ማሟላት ያስፈልጋል ይላሉ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ። እርሳቸው እንደሚሉት ሀገራዊ የሕዝብ ንቅናቄው ዋና ዓላማ በየደረጃው ባለው ማህበረሰብና ልዩ ልዩ አካላት ተሳትፎ የትምህርት ቤቶችን መሠረተ-ልማት ማሻሻል ነው። የአሠራር ሥርዓት ተዘርግቶ ሥራው በዘላቂነት እንዲቀጥልና ማህበረሰቡ በትምህርት ሥርዓት ውስጥ በመሠረተ-ልማት መሻሻል ሥራ ሳይወሰን የመማር ማስተማሩን ሂደት በባለቤትነት እንዲደግፍ ማስቻል ነው። በተለይም ትምህርት ቤቶች ከአራቱ አበይት ጉዳዮች አንፃር ታይተው ችግሮችን በቅደም ተከተል በማስቀመጥ ያለባቸውን ክፍተቶች በመፍታት የተማሪዎችን ውጤትና ሥነምግባር ማሻሻል ነው።
ከዚህ አኳያ ሀገራዊ የሕዝብ ንቅናቄው እንዲሳካ የተለያዩ መንገዶችን ተቀይሰዋል። የድርጊቱ ፈጻሚም ሆነ አስፈጻሚ ሕዝብ በመሆኑ ሥራውን የሚያስተባብር የራሱን ሰው መርጦ በየደረጃው እንዲደራጅ ተደርጓል። ይህንን የሚከታተልም ሰው ተመድቧል። በተመሳሳይ ሥራዎች እንዲቀላጠፉ ቴክኖሎጂውን በመጠቀም የትምህርት ቤቶችን አሁናዊ ፍላጎትና ያሉበትን ደረጃ የሚያሳይ ‹‹ፖርታል›› በመፈጠሩ ማንኛውም ግለሰብ ወይም የግል ተቋም ማገዝ የሚፈልገውን ትምህርት ቤት መርጦ በአይነትና በመጠን እንዲደግፍ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል። ለዚሁ ሥራም ‹‹sip.moe.gov.et›› የተሰኘ ድረ ገፅ ተዘጋጅቷል። ግለሰቦች፣ ማህበረሰቡና ሌሎች ልዩ ልዩ ተቋማት ይህን ድረ ገፅ ተጠቅመው የሚፈልጉትን እገዛ ማድረግ ይችላሉ።
ሚኒስትሩ እንደሚገልፁት በሀገር ደረጃ ከ 49 ሺህ በላይ ከሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ውስጥ አብዛኞዎቹ ለመማር ማስተማር አስፈላጊ የሆኑ መሠረተ-ልማት የሌላቸው በመሆኑ ተማሪዎች በተጓደለ የትምህርት ከባቢ ውስጥ እንዲማሩ ተገደዋል። በዚህም 86 በመቶ አንደኛ ደረጃ እና 71 በመቶ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች ናቸው። እናም የትምህርት ቤቶችን መሠረተ-ልማት ማሻሻል ሀገራዊ ንቅናቄ ዘላቂነት ባለው መልኩ ማከናወን ያስፈልጋል።
ለዚህ ደግሞ በየደረጃው ያለውን የአካባቢ ማህበረሰብ፣ ከየአካባቢው ተምረው የወጡ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚኖሩ ተወላጆችን፣ ባለሀብቶችን፣ ታዋቂ ግለሰቦችን፣ ማህበራትን፣ የግልና የመንግሥት ተቋማትን፣ የልማት አጋሮችን፣ በየደረጃ ያሉ የመንግሥት አካላትን ወዘተ…. በንቃት እንዲሳተፉ ማድረግ ያስፈልጋል።
ከሀገራዊ ንቅናቄው በዋናነት የሚጠበቀው ነገር በማህበረሰቡና በልዩ ልዩ አካላት አስተዋጽኦና ጥረት እያደጉ የመጡ መሠረተ ልማታቸውን (ንጹሕ ውሃ፣ መፀዳጃ ክፍሎች፣ በቂ መማሪያ ክፍሎች፣ ወንበር፣ ጠረጴዛ፤ የስፖርት ሜዳ፣ መጻሕፍት፣ የኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ ቤተ-መጻሕፍት፣ ቤተ-ሙከራ ወዘተ.) ያሻሻሉ ትምህርት ቤቶች በብዛት እንዲፈጠሩ ማድረግ ነው። ለዚህ ሥራም ዋነኛ ባለድርሻ አካላት ሕዝቡ በመሆኑ የበኩሉን ማበርከት ይኖርበታል። የመገናኛ ብዙኃኑም ዘገባውን ከመስራት ባለፈ የራሳቸውን አሻራም ማሳረፍ ይኖርባቸዋል።
የትምህርት ቤቶችን መሠረተ-ልማት ማሻሻል ሀገራዊ ንቅናቄው ትውልድን የመሥራት ጉዳይ በመሆኑ ማህበረሰቡም ሆነ መገናኛ ብዙኃን አጀንዳውን በመውሰድ ሀገራዊ አጀንዳ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። የትምህርት ቤቶችን ነባራዊ ሁኔታ መረዳትና ለትምህርት ቤቶቹ ስለሚያስፈልገው እገዛ በማሳወቅና በማስረዳት የተቻላቸውን ሁሉ ማድረግ አለባቸው።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 26 ቀን 2015 ዓ.ም