ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ «ጋርመንት» አካባቢ ባለው አደባባይ የተገነባው የክቡር ዶክተር አርቲስት አሊ ቢራ መታሰቢያ ሐውልት ተመርቋል። ለዚህ ተወዳጅ የኪነ ጥበብ ሰው ሐውልት መቆሙ ተገቢና መለመድም ያለበት ነው። ለዚህ ታላቅ የሙዚቃ ሰው ሐውልት መቆሙ ብቻ ሳይሆን ሐውልቱ ላይ የሰፈረው ጽሑፍም ድንቅ ነው። በሐውልቱ ላይ ዘመን አይሽሬ ከሆኑት የአሊ ቢራ ሙዚቃዎች አንዱ ከሆነው ሥራ ላይ የተመዘዙ ስንኞች በአፋን ኦሮሞና በአማርኛ ተተርጉሞ እንዲህ የሚል ጽሑፍ ሰፍሯል ፦
Rabbi moo namumaa
Kan seera jallisee ?
Haati teenya takkaa
Maaltu addaan nu baasee ?
አምላክ ወንይስ ሰው ፤
ሕግን ያጣመመው ?
የአንድ እናት ልጆች ነን ፤
የሚለያየን ማን ነው ?
ይህ ታላቅ መልዕክት ያዘለ ትውልድ አስተማሪ የሆነ ስንኝ በአሊ ሐውልት ላይ እንዲሰፍር መደረጉን ሳያደንቁ ማለፍ አይቻልም። ይህን ትልቅ ነገር ፈፅሞ አንድ ቦታ ላይ የሚታየውን ግድፈት ወይም ስህተት ሊባል ይችላል መጠቆሙም ተገቢ ነው። ሐውልቱ ላይ አሊ የተወለደው 26/05/1948 ነው የሞተው ደግሞ በ06/11/2022 ነው ይላል። ይህ ስህተት ነው። አሊ ቢራ ኢትዮጵያዊ እንደመሆኑ የተወለደበትና ሕይወቱ ያለፈበት የዘመን አቆጣጠር በኢትዮጵያ መሆን አለበት። ምናልባት ሐውልቱን የውጭ አገር ዜጎች የሚመለከቱት እንደመሆኑ እነሱን ታሳቢ ያደረገ እንዲሆን ታስቦም ከሆነ በኢትዮጵያም በአውሮፓም ዘመን አቆጣጠር ማስፈር ይቻላል። በእርግጥ ሌሎች ታላላቅ ሐውልቶች ላይም እንዲህ ዓይነት ጥቃቅን ስህተቶች ቢፈለጉ አይጠፉም። ያምሆኖ ወደ ፊት ለሚገነቡ ሐውልቶች ጥንቃቄ እንዲደረግባቸው ትምህርት ይሆናልና መጠቆሙ አይከፋም።
የሐውልት ነገር ሲነሳ በኢትዮጵያ ብዙ አከራካሪ ጉዳዮች አብረው ይነሳሉ። ለምሳሌ ያህል በተለያዩ ዘርፎች ለሀገር ትልቅ ውለታ የሠሩ በርካታ ጀግኖች ሐውልት አልቆመላቸውም የሚሉ ጥያቄዎች ይነሳሉ። እውነት ነው ኢትዮጵያ ለበርካታ ጀግኖቿ የሚገባቸውን ሐውልት ገና አቁማ አልጨረሰችም። ወደ ፊት አቅም በፈቀደ ልክ እንደ አሊ ቢራ በጉልህ የሚታይ ሐውልት አደባባይ ላይ የሚቆምላቸው አያሌ የሀገር ባለውለታና ጀግኖች ይኖራሉ።
እዚህ ላይ መዘንጋት የሌለባቸው ሐውልት ሊቆምላቸው የሚገባ ነገር ግን ብዙም ትኩረት ሲሰጣቸው የማይታዩ ጀግኖችን በጥቂቱ እንታዘብ። እነዚህ ጀግኖች ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ ከፍ ያደረጉና ያስከበሩ ብርቅዬ አትሌቶቻችን ናቸው። እነዚህ የኢትዮጵያ ምልክቶች በየከተሞቻችን ሐውልት ሊቆምላቸው እንደሚገባ አያከራክርም። እንኳን ሀገራቸው ሌሎች ሀገራትም ለእነዚህ ብርቅዬ አትሌቶች ሐውልት አቁመው ሲያከብሯቸው አይተናል። ለምሳሌ ሻምበል አበበ ቢቂላ በሮምና ቶኪዮ በሠራቸው ገድሎች ሐውልት ባይቆምለት እንኳን በስሙ በርካታ ጎዳናዎች፣ድልድዮች ተሰይመውለት ይገኛሉ። ሌላኛው የኦሊምፒክ ማራቶን ጀግና ማሞ ወልዴም ቢሆን ስፔን ውስጥ ሐውልት ቆሞለት ይገኛል(በእርግጥ የማሞ ሐውልት በስፔን አራት ጊዜ የሀገር አቋራጭ ቻምፒዮና በማሸነፉ ነው)። የአፍሪካ እግር ኳስ አባት የሆኑት ይድነቃቸው ተሰማም ሞሮኮ ላይ በስማቸው ስቴድየም ተሰይሞ ይገኛል።
አበበ ቢቂላ አዲስ አበባና አዳማ ላይ በስሙ ስቴድየም ተሰይሞለታል። ነገር ግን አበበ የጥቁር ሕዝቦች ሁሉ የአሸናፊነት ተምሳሌት ነውና ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ከተሞች አደባባይ ላይ ሐውልት ሊቆምለት የሚገባ ሰው ነው። እንደ አበበ ቢቂላ ሁሉ ሌሎች በርካታ ዘመን የማይሽረው ታሪክ ያኖሩ አትሌቶችም ሐውልት ሊቆምላቸው እንደሚገባ ጥርጥር የለውም። በዚህ ረገድ ጀግናዋ አትሌት ደራርቱ ቱሉ በአዲስ አበባ ሃያት ተብሎ ይጠራ የነበረው አደባባይ በስሟ ተሰይሞ አበረታች ጅምር ታይቶ ነበር። ይህ መቀጠል አለበት።
እዚህ ጋር ሌሎች ሀገራት ያላቸውን ተሞክሮ ማሳያ እንዲሆን ላንሳ። ጃክ ሌዝሊ፤ የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድንን ማልያ አጥልቆ ታሪክ ከሠራ 100 ዓመታት ሊሞላው ቢሆን እንኳ በቅጡ የሚያስታውሰው ሰው አልነበረም። ይህ የሆነው በቆዳው ቀለም ብቻ ነው። ጊዜው 1925 ነበር። እንግሊዝ ከአየርላንድ ጋር ለነበራት የወዳጅነት ጨዋታ መልማዮች ተጫዋቾችን እየመለመሉ ነበር። በወቅቱ ሌዝሊ የፕላይማውዝ ተጫዋች ነበር። መልማዮቹ የሚጫወትበት ሜዳ መጥተው ሲመለከቱ ሌዝሊን ጥቁር ሆኖ ያገኙታል። በዚህም ምክንያት ሌዝሊ ለእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን የተሰለፈ የመጀመሪያው ተጫዋች በመሆን ታሪክ የሚሠራበትን አጋጣሚ መና ያደርጉበታል። ይኸው ሌዝሊ አሁን ገንዘብ ተዋጥቶለት ሐውልት ሊሠራለት እየታቀደ ነው። እስካሁን ቢያንስ 135 ሺህ ፓውንድ ተዋጥቶለታል። ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ 240 ስፖርተኞችን የሚዘክሩ ሐውልቶች አሉ። ከዚህ የምንማረው ትልቅ ቁም ነገር አለ። ይህም እንኳን የሀገርን ስም በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ከፍ አድርገው ያስጠሩ ጀግኖች እንደ ሌዝሊ በሆነ አጋጣሚ የተዘነጉ ሳይቀሩ ሐውልት እንደሚቆምላቸው ነው። እኛም ሐውልቶች ከመስብህነት ባሻገር ነገ ሌሎች ጀግኖችን ለመፍጠር ዛሬ ያሉንን ጀግኖች የምናከብርበትና ለመጪው ትውልድ ህያው ታሪካቸውን አስቀምጠን የምናልፍበት አንዱ መንገድ ሐውልት ማቆም ነውና ይልመድብን።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኔ 24/2015