የምድር በረከት ከሆኑ አያሌ ማዕድናት መካከል የከበሩ ድንጋዮች ይገኙበታል፡፡ እነዚህ የከበሩ ድንጋዮች ወይም ማዕድናት ከሚገኙባቸው አካባቢዎች መካከል የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ይጠቀሳል። በክልሉ በተለይ በደቡብ ወሎ ዞን ደላንታ ወረዳ የሚገኘው የኦፓል ማዕድን እዚህ ላይ ሊጠቀስ ይገባዋል። ከዚህ አካባቢ የሚመረተው የኦፓል ማዕድን ለበርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች የኑሮ መሰረት ከመሆኑም ባሻገር የውጭ ምንዛሬም እያሰገኘ ነው፡፡
የክልሉ ዋግ ህምራ ዞን ሰቆጣ አካባቢውም ሌላው በከበረ ድንጋይ ማዕድኑ የሚታወቅ ሆኗል፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች በአካባቢው የሚገኙ የተለያዩ የከበሩ ማዕድናትን አውጥተው በማልማት ተጠቃሚ እየሆኑ እንደሚገኙ ይገልጻሉ፡፡ ይሁንና በአካባቢው ያለውን ይህን እምቅ የማዕድን ሃብት አሟጠው መጠቀም እንዳልቻሉም ነው ነዋሪዎቹ የሚናገሩት፡፡
በዋግ ህምራ ዞን ሰቆጣ አካባቢ ከሚገኙ የከበሩ ድንጋዮችን ቆርጠውና አስውበው ለገበያ ከሚያቀርቡ ባለሙያዎች መካከል አቶ ዮሀንስ ጌታሁን አንዱ ነው። አቶ ዮሀንስ የከበሩ ድንጋዮችን የመቁረጥና የማስዋብ ሥራን መተዳደሪያው ካደረገው ቆይቷል፡፡ ማዕድናቱን ወደ ተለያዩ ጌጣ ጌጦች ቀይሮ ለገበያ የሚያቀርብ ሲሆን፤ ምርቶቹም ጃስፐር፣ ሞስአጌት፣ ኦፓልና ኦፕስድያ በመባል እንደሚታወቁ ይገልጻል፡፡ ጌጣ ጌጦቹ በብር ታቅፈው የሚሠሩና በብር ሳይታቀፉ የሚሠሩ ሲሆኑ፣ አገልግሎታቸውም ለአንገት፣ ለጆሮ፣ ለእጅና ለተለያዩ አካላት ጌጣጌጥነት የሚውሉ ናቸው፡፡
የከበሩ ድንጋዮቹ በመሬት የላይኛው ክፍል በቀላሉ እንደሚገኙ አቶ ዮሀንስ ይናገራል፡፡ በተለይም በወንዞች አካባቢ በቀላሉ እንደሚገኙ ጠቅሶ፤ መሬት ተቆፍሮ የሚገኙ ማዕድናት እንዳሉም ይገልጻል፡፡ ከእነዚህም መካከል ኦፓል አንዱ እንደሆነም ጠቅሶ፣ ሌሎች በርካታ የከበሩ ድንጋዮች በአካባቢው ስለመኖራቸውም ነው የሚናገረው፡፡
እንደ አጌትና ጃስፐር የመሳሰሉ በቀላሉ ከመሬት የላይኛው ክፍል የሚገኙትን ማዕድናት በሚፈለገው ቅርጽ አልምቶ የሚጠቀመው አቶ ዮሀንስ፤ ድንጋዩ በቅድሚያ የሚቆራረጥና ተውቦ ለገበያ የሚቀርብ መሆኑን ነው ያብራራል፡፡ የአካባቢው ወጣቶች በዘርፉ ስልጠና ሳያገኙ በልምድ ሲሰሩ መቆየታቸውን በማስታወስ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በዘርፉ ስልጠና ማግኘት በመቻላቸው ከዚህ ቀደም ከሚሠሩት በተሻለ መንገድ እሴት ጨምረው እየሠሩ እንደሆነ አስረድቷል፡፡
በአማራ ክልል ከሚገኘው ሜዳ ከተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት መሰረታዊ የጌጣ ጌጥና ተጨማሪ የጌጣጌጥ ማምረት ስልጠና ማግኘት የቻሉት ጌጣ ጌጦችን በተሻለ ጥራትና ዲዛይን በመሥራት ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውንም ይገልጻል፡፡
የዋግ ህምራ ዞን በበኩሉ የከበሩ ድንጋዮቹ ያሉበትን አካባቢ በጥናት መለየት እንዲቻል ድጋፍና ክትትል በማድረግ እገዛ እያደረገላቸው መሆኑንም አቶ ዮሀንስ ጠቅሶ፤ ባገኘው ስልጠና የተለያዩ ጌጣ ጌጦችን አልምቶ ለገበያ ማቅረብ መቻሉን አስታውቋል፡፡ ለሶስት ሰዎችም የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ነው ያመለከተው፡፡
እሱ እንደሚለው፤ አብዛኛው የአካባቢው ሰው ከብር በተሠሩ ጌጣጌጦች የሚጠቀም በመሆኑ ከከበሩ ድንጋዮች የሚዘጋጁ ጌጣ ጌጦችን ብዙ አይፈልጋቸውም። ይህም ጌጣ ጌጦቹ በሀገር ውስጥ ብዙ ገበያ የማያገኙ እንደሆነ ያመለክታል፡፡
አቶ ዮሀንስ በአገር ውስጥ በከበሩ ማዕድናት የሚያጌጥ ሰው መመልከት ብዙም የተለመደ እንዳልሆነም ይናገራል፡፡ እነዚህን የከበሩ ድንጋዮች ማህበረሰቡ መጠቀም እንዲችል ከብር ጋር ቀላቅሎ በመስራት ብርና ወርቅ ቤቶች ውስጥ ለመሸጥ ጥረት እያደረገ መሆኑን ይገልጻል፡፡
በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የከበሩ ድንጋዮች ስለመኖራቸው በስፋት እንደሚነገር የሚጠቅሰው አቶ ዮሀንስ፤ ይሁንና ይህን የማዕድን ሀብት በሚገባ መጠቀም እንዳልተቻለ ነው ያመለከተው። ለአብነትም በአማራ ክልል ብቻ የሚገኘው የወሎ ደላንታ ኦፓል ተወዳዳሪ እንደማይገኝለት በመጥቀስ፣ የከበሩ ድንጋዮቹን አልምቶ የሚጠቀመው ሰው ግን እጅግ በጣም አነስተኛ እንደሆነ ያመለክታል፡፡ በዚህ ላይ በስፋት ቢሠራበት ብዙ የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚቻልም ይጠቁማል፡፡
የማዕድን ሃብቱ ገና አልተነካም የሚለው አቶ ዮሀንስ፤ በአማራ ክልል ከሚገኘውና በከፊል ከከበሩ ድንጋዮች በተጨማሪ በደቡብ ክልል፣ በኦሮሚያ ክልልና በሰሜኑ የአገሪቷ አካባቢዎች እንደ ሳፋየር፣ ሩቢ ኢምራልድና ሌሎችም እጅግ ውድ የሆኑ ማዕድናት እንደሚገኙ አቶ ዮሀንስ ጠቁሟል፡፡ እነዚህ ማዕድናት በዶላር እንደሚሸጡ በመጥቀስ፣ ማዕድናቱን በስፋት አልምቶ አገሪቷ ከዘርፉ የውጭ ምንዛሪ ተጠቃሚ መሆን እንድትችል ትኩረት እንዲሰጥ መልዕክቱን አስተላልፏል።
ኦፓል የተሰኘውን የከበረ ድንጋይ አልምቶ በመሸጥ የሚተዳደረው አቶ አከለ አባተ በበኩሉ ኦፓሉን ከአምራቾች በመረከብ እሴት ጨምሮና አለስልሶ ነው ለገበያ የሚያቀርበው፡፡ ኦፓልን አስመልክቶ አቶ ዮሀንስ ያነሳውን ሃሳብ የሚጋራው አቶ አከለ፤ በደቡብ ወሎ ደላንታ ወረዳ የተለያዩ የከበሩ ድንጋዮች ከመሬቱ የላይኛው ክፍል በቀላሉ እንደሚገኙ ይገልጻል፡፡ ኦፓል ግን በብዙ ልፋትና ድካም ተቆፍሮ እንደሚገኝ ነው ያስረዳው፡፡
እንደ እሱ ገለጻ፤ ኦፓል በአካባቢው በስፋት የሚገኝ ቢሆንም፣ የአካባቢው ማህበረሰብ ሃብቱን በሚገባው ልክ እየተጠቀመበት አይደለም፡፡ ለዚህም ዋናው ምክንያት ለዘርፉ ትኩረት አለመሰጠቱ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ የአካባቢው ማህበረሰብ የማዕድን ሃብቱን አልምቶ መጠቀም አልቻለም፡፡ ለዚህም ከመንግሥት አካላት የሚደረግ ድጋፍና ክትትል ካለመኖሩም በላይ በብዙ ድካምና ልፋት የተዘጋጀው ማዕድን ለገበያ የሚቀርብበት መንገድም አልሚውን ተጠቃሚ እያደረገ አይደለም፡፡ ከአልሚው በበለጠ ተጠቃሚው ደላላው ነው፡፡
የከበሩ ድንጋዮችን ከመሬት ውስጥ በማውጣት ሥራ ላይ የተሰማሩት ቆፋሪዎች የልፋታቸውን ያህል ተጠቃሚ ናቸው ማለት እንደማይቻልም አቶ ታከለ ጠቅሶ፤ ለዚህም ምክንያቱ የገበያ ሰንሰለቱ መርዘሙ መሆኑን ተናግሯል፡፡ ማዕድናቱን ከቆፋሪዎቹ በቀጥታ የሚቀበሉት አዘዋዋሪዎች ግን የከበሩ ድንጋዮቹ ገና ከመሬት እንደወጡ ምንም አይነት እሴት ሳይጨምሩባቸው ለገበያ እንደሚያቀርቡም ነው ያመለከተው፡፡ ከአዘዋዋሪዎቹ ተቀብለው እሴት በመጨመር ወደ ገበያ የሚያቀርቡት ደግሞ እንደ አቶ ታከለ ያሉ ሌሎች አልሚዎች እንደሆኑ ነው ያስረዳው፡፡
ከመሬት ተቆፍሮ የወጣውን ኦፓል ቆርጦ፣ በተለያየ ቅርጽ አዘጋጅቶና አስውቦ ለገበያ ለማቅረብ መቁረጫና የተለያዩ ማሽኖች እንደሚያስፈልጉ ጠቅሶ፣ በአሁኑ ወቅት ዊል የተባሉትን በማሽን ውስጥ የሚሽከረከሩ አላቂ መቁረጫዎችን ማግኘት እንዳልተቻለ ተናግሯል። ማዕድናቱ በዚህ መንገድ ካልተዘጋጁ መልካቸው የማያምርና ጥሩ ዋጋ ማውጣት የማይችሉ እንደሆኑም አመላክቷል፡፡
አቶ ታከለ እንደተናገረው፤ የክልሉም ሆነ የፌዴራል መንግሥት ከማዕድን ሃብቱ መጠቀም እንዲችሉ በዘርፉ ለተሰማራው የአካባቢው ማህበረሰብ ድጋፍና ክትትል ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተለይም በቁፋሮ ላይ የተሰማሩ አካላት መቆፈሪያው በፍጥነት ይጎዳባቸዋል፤ አፈር የሚያወጡበት መሳሪያም ያስፈልጋቸዋል። እነዚህንና ሌሎች ድጋፎችን መንግሥት ቢያደርግ ከዘርፉ አሁን ከሚገኘው በበለጠ ገቢ ማግኘት ይቻላል። የአካባቢው ማህበረሰብ የሚያርሰው መሬት የለውም፤ በማዕድን ልማት ብቻ የሚተዳደር ነው፡፡
ሚዳ የተሰኘው ግብረ ሰናይ ድርጅት የከበሩ የጌጣ ጌጥ ማዕድናት ስልጠና አስተባባሪ አቶ አደራው ዳኘው እንዳሉት፤ ድርጅቱ ከ60 በላይ ከሆኑ አገራት ጋር ይሰራል፡፡ የ70 ዓመት ልምድ ያለው ሲሆን፤ መቀመጫውም በካናዳና አሜሪካ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በአማራ ክልል ብቻ ይሰራል፡፡
ድርጅቱ በአማራ ክልል ከሚሰራቸው ሥራዎች መካከልም አንደኛው የከበሩ ማዕድናት ያሉበት አካባቢ የሚኖረው ህብረተሰብ በከበሩ ማዕድናት የሚሠሩ ጌጣ ጌጦች የእሴት ሰንሰለቱን ጠብቀው እንዲያለሙ ያደርጋል፡፡ ሌላኛው ሩዝ ከማምረት ጀምሮ በገበያ ትስስርም እንዲሁ በአትክልትና ፍራፍሬ የሚሠራ ድርጅት ነው፡፡
ለድርጅቱ የፋይናንስ ድጋፍ የሚያደርገው ሚዳ የተሰኘው የካናዳ ድርጅት በአማራ ክልል ሥራውን ከጀመረ ስድስት ዓመታትን ማስቆጠሩንም ተናግረዋል። በአካባቢው የሚገኙ ዜጎች ማዕድናቱን አልምተው መጠቀም እንዲችሉ ድርጅቱ ከፍተኛ እገዛ እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
አስተባባሪው እንደሚሉት፤ በአማራ ክልል በስፋት የሚገኙ የከበሩ ማዕድናትን በማልማት በኩል ሰፊ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራው ሚዳ ፕሮጀክት፤ ህብረተሰቡ በአካባቢው የሚገኙ ማዕድናትን አውጥቶና አልምቶ ወደ ለውጭ ገበያ እንዲያቀርብ ሰፊ ሥራ እየሠራ ይገኛል፡፡ በመላው ኢትዮጵያ 60 የሚደርሱ የከበሩ ማዕድናት የሚገኙ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል በአማራ ክልል በስፋት የሚገኘውን ኦፓልን ጨምሮ ሌሎች በከፊል የከበሩ ማዕድናት አልምተው ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡም አሉ፡፡
ፕሮጀክቱ በክልሉ በዋነኛነት እየሠራ ያለው በዘርፉ የሥራ ዕድል በመፍጠር ላይ ነው፡፡ ለዚህም በከበሩ ማዕድናት ላይ እሴት መጨመር ይኖርበታል፡፡ ምርቱ ከመሬት እንደወጣ ምንም እሴት ሳይጨመርበት ማለትም ሳይቆራረጥና ሳይዋብ ለውጭ ገበያ ቢቀርብ የተወሰነ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት ቢችልም፣ የሥራ ዕድል መፍጠር ግን አይችልም፡፡ የውጭ ምንዛሬውም ቢሆን እሴት ተጨምሮበት እንደሚላከው አጥጋቢ አይደለም። እሴት በመጨመር ሂደት ውስጥ ከሚፈጠረው የሥራ ዕድል በተጨማሪ እሴት ተጨምሮበት የሚላከው ጌጣጌጥ በጥሬው ከሚላከው ይልቅ ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሪ ያስገኛል፡፡
ድርጅቱ በዋነኛነት ትኩረት አድርጎ የሚሠራው የሥራ ዕድል ኢትዮጵያ ውስጥ መፈጠርና ቴክኖሎጂው ማደግ አለበት በሚል ተናግረዋል፡፡ የከበሩ ድንጋዮቹን ለመቁረጥና ለማስዋብ የሚያገለግሉ መሳሪያዎችን ድጋፍ በማድረግ ስልጠና በመስጠት ከማዕድን ሃብቱ መጠቀም እንዲቻል ሰፊ ሥራ መስራቱንም አስተባባሪው ይገልጻሉ፡፡ በክልሉ በዘርፉ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ከ10 የማይበልጡ እንደነበሩ ያስታወሱት አስተባባሪው፤ በአሁኑ ወቅት በሚዳ ፕሮጀክት ብቻ የሚደገፉ ከ125 የሚበልጡ ኢንተርፕራይዞች እንዳሉ ነው ያመላከቱት፡፡
እነዚህ ኢንተርፕራይዞች ማሽን ገዝተው የከበሩ ድንጋዮቹን በመቁረጥና በማስዋብ ሥራ ተሰማርተው ለሌሎችም የሥራ እድል መፍጠር መቻላቸውን ጠቅሰው፣ የተለያዩ ጌጣ ጌጦችን አምርተው ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል ሲሉም ይገልጻሉ። በአሁኑ ወቅት የአካባቢው ማህበረሰብ በተለይም እህቶችና እናቶች ጌጣ ጌጦቹን ከሀገር ባህል አልባሳት ጋር መጠቀም መጀመራቸውንም ጠቅሰው፣ ይህን ተከትሎም የጌጣጌጥ ምርቱ ከውጭ ገበያ ባለፈ በአገር ውስጥ ገበያም እየተለመደ እንደመጣ ነው ያመለከቱት፡፡
ድርጅቱ ከክልሉ መንግሥት ጋር እንደሚሠራ የጠቀሱት አስተባባሪው፤ መንግሥት ኢንተርፕራይዞችን በመደገፍ፣ ቴክኖሎጂ እንዲያገኙ በማድረግ፣ የአካባቢው ማህበረሰብም የሥራ ዕድል እንዲፈጠርለት እና በዋነኛነት የማዕድን ሃብቱ እሴት ተጨምሮበት እንዲወጣ ቢያደርግ በውጭ ምንዛሪ ግኝቱም ሆነ በሥራ እድል ፈጠራው የበለጠ ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻል አስታውቀዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የተማረ የሰው ኃይል እየወጣ መሆኑን የጠቀሱት አስተባባሪው፤ ይህ የተማረ ዜጋ የሥራ እድል ከሚያገኝበት መንገድ አንዱ የማዕድን ዘርፍ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ በተለይም የጌጣ ጌጥ ሥራ ሰፊ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር አስታውቀዋል፡፡
ድርጅቱ ከቆፋሪዎች ጀምሮ ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን የጠቀሱት አስተባባሪው፤ በዋናነት እሴት በመጨመር የከበሩ ድንጋዮችን ቆርጠውና አስውበው ለገበያ እንዲያቀርቡ ስልጠና በመስጠት ይደግፋል። ለዚህም የመንግሥት ተቋማት ከድርጅቱ ጋር በጋራ የሚሠሩ ሲሆን ስልጠና በመስጠት የቴክኒክና ሙያ መምህራን ይሳተፋሉ፡፡ ስልጠና ያገኙትም መቁረጫ ማሽን ተጠቅመው የተለያዩ ጌጣ ጌጦችን ማምረት እንዲችሉ ድጋፍ ያደርጋል፤ ከድጋፉ አንዱና ዋነኛው መቁረጫ ማሽን እንዲኖራቸው ማድረግ ሲሆን ማሽኑን መግዛት እንዲችሉ ከፋይናንስ ተቋማት ጋር በጋራ ይሠራል፡፡
ድርጅቱ የማዕድን ሃብቱን ለኢትዮጵያውያን በማስተዋወቅ ረገድም ሰፊ ሥራ እየሠራ መሆኑን የጠቀሱት አስተባባሪው ከአማራ ክልል መገናኛ ብዙሃን ጋርም እንደሚሠራ አመልክተዋል፡፡ የተለያዩ ፕሮግራሞችን በመሥራት ማህበረሰቡ ስለማዕድን ሃብት ዕውቀትና ግንዛቤ እንዲኖረው እንዲሁም ምርቶቹ በየትኞቹ አካባቢዎች እንደሚገኙ ጭምር የሚያመላክት ሲሆን፤ ማዕድኑን አልምቶ መጠቀም የሚቻልና የማዕድን ሃብቱ ያለውን ጠቀሜታ በማስረዳት ሰፊ ሥራ ይሰራል። ለዚህም ኢንተርፕራይዞቹ በዋናነት ተሳታፊ ሲሆኑ፤ ይህም የማዕድን ሃብቱን ኢትዮጵያውያን በሰፊው እንዲያውቁትና የሀገር ውስጥ ገበያ እንዲፈጠር ያደርጋል ነው ያሉት፡፡
የማዕድን ሃብቱ በሀገር ውስጥ በስፋት ሲተዋወቅና ገበያው ሲፈጠር በርካታ ኢንተርፕራይዞች የከበሩ ድንጋዮችን እየቆረጡና እያስዋቡ መጠቀም ይችላሉ። ቱሪስቱም ሲመጣ ተቆርጦና ተውቦ የተዘጋጀውን በመግዛት ከፍተኛ ገቢ በሀገር ውስጥ እንዲገኝ ያደርጋል። ‹‹የማዕድን ሃብቱ እሴት ሳይጨመርበት በአብዛኛው ህንድ፣ ቻይና አሜሪካ ይላካል›› ያሉት አስተባባሪው፣ የከበሩ ድንጋዮች እሴት ሳይጨመርባቸው ከሀገር ሲወጡ የሚያስገኙት ገቢ አነስተኛ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ እሴት ጭመራ ላይ በስፋት መሠራት በዘርፉ ሰፊ የሥራ ዕድል መፈጠር፣ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሰኔ 23/2015