አዋጅና ሕግ፣ ደንብና መመሪያ ሲወጣ ያለአንዳች ሰበብና ምክንያት አይደለም።ጉዳዩ ትኩረት ተሰጥቶት በአስፈላጊነቱ ታምኖበት እንጂ ። ይህ በድንጋጌ ሰፍሮ አግባብ ባለው መመሪያ የሚዘጋጅ ህግ ደግሞ በአግባቡ ተፈጻሚ ይሆን ዘንድ የግድ ይላል፡፡
እንደ እኔ ዕምነት ለተፈጻሚነቱ ተግባራዊነት የሚመለከታቸው አካላት ብቻ ተጠያቂ አይሆኑም። በእነሱ ላይ የሚጣለው ግዴታ እንዳለ ሆኖ ከፍተኛውን ድርሻ መወጣት ያለባቸው ሕግ አውጪዎቹ አካላት ሊሆኑ ይገባል፡፡ አንዳንዴ በአንዳንድ ስፍራዎች ሕግ ተጥሶ በምትኩ ሕገወጥነት ሲንሰራፋ እናስተውላለን። እንዲህ በሆነ ጊዜ አብዛኛው ተያይቶ ከመተዛዘብ ባለፈ ስለምን ብሎ የሚጠይቅ አይሆንም። አንዳንዴ አግባብ ያልሆኑ ተግባራት ሲደጋገሙ በሰዎች እይታ ውስጥ ይለመዳሉ።ይህ ድግግሞሽ የሚያሳድረው ተጽዕኖም ድርጊቱ ሁሌም ‹‹ትክክል ነው›› ተብሎ እንዲታሰብ ጭምር ያደርጋል፡፡
ከተማችን አዲስ አበባን በለውጥ ምዕራፍ ካሻገሯት እሴቶች መካከል ታላላቅ የሚባሉ ሆቴሎች ይጠቀሰሉ ። እነዚህ ሆቴሎች ለከተማችን ከሚሰጡት ድምቀትና እውቅና ባለፈ ከአህጉራዊ ጉባኤዎች መካሄድ ጋር የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ በእጅጉ ላቅ ያለ ነው፡፡ ሆቴሎቹ በውድድር አልፈው ተመራጭ እንዲሆኑ የሚስችላቸው በዘርፉ የተቀመጠውን መስፈርት በአግባቡ ማሟላታቸው እንደሆነ ግልጽ ነው።ይህ ሳይሆን ቀርቶ አንዳች አጉድለው ቢገኙ ግን የተቀመጠው ሕግ እንደተጣሰ ተቆጥሮ ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅምና ደረጃ የሚያጡበት እውነታ ይኖራል፡፡
ወደከተማችን ሌላኛው ገጽታ እንመለስ ።አሁንም ከሆቴሎችና አገልግሎታቸው ትዝብት አንወጣም ።በከተማችን ሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎች ስር ተጠልለው የተለያዩ ግልጋሎት ከሚሰጡት መካከል በየሰፈሩ የምናገኛቸው አነስተኛ የምግብና መጠጥ ቤቶች ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ ስፍራዎች ባብዛኛው የብዙኃኑን የኪስ አቅም ያገናዘቡ በመሆናቸው ዕለት ከዕለት በደንበኞቻቸው ተጨናንቀው ይውላሉ። ሆቴሎቹ ከበዙ ደንበኞቻቸው ባሻገር ንግዱን ሲመሩላቸው በሚውሉ አስተናጋጆችም ጭምር የተወጠሩ ናቸው።
በግልጽ እንደሚስተዋለው የአብዛኞቹ ምግብ ቤቶች ትኩረት ንግዳቸውን በማቀላጠፍ ላይ ብቻ የቆመ ነው በርካቶቹ አገልግሎት እንሰጥባቸዋለን የሚሉባቸው ሳሎኖች ምግብ ከሚያበስሉባቸው ኩሽናዎች የራቁ አይደሉም። ይህ ብቻ አይደለም ። የመጸዳጃ ቤቶቻቸው ክፉ ሽታም ከምግቡ መዓዛ ቀድሞ ለእንግዶች አፍንጫ ለመድረስ የፈጠነ ነው። የቤቶቹ መስተንግዶ ባብዛኛው በአንድ ስፍራ ላይ መሆኑ በመጣበብና መጨናነቅ ስራው እንዲካሄድ ያስገድዳል ።
በአንዳንዶቹ ቤት ምግብ የሚያዘጋጁባቸው ዕቃዎች ጭምር ንጽህናቸው በእጅጉ የተጓደለ መሆኑን መታዘብ ይቻላል።ለውሃ ተብለው የሚዘጋጁ ማቅረቢያዎችና ብርጭቆዎቻቸው ንጽህናም በወጉ የተጠበቀ አይደለም። ብዙዎቹ በግልጽ በሚስተዋልባቸው ጉድለቶች ላይ አስተያየት ተቀብለው ለመታረም ዝግጁዎች አለመሆናቸውም ችግሮቹ በነበሩበት እንዲቀጥሉ በር ከፍቷል፡፡
የምግብ ቤቶቹ ደንበኞች ባብዛኛው ከሌሎች በተሻለ የዋጋ ቅናሽን ፈልገው የሚመጡ ናቸው።እንዲህ መሆኑ ደግሞ በግልጽ የሚስተዋለውን ጉድለት አጢነው መፍተሄ እንዳይፈልጉለት ሰበብ ሆኗል፡፡ የምግብ ቤቶቹን ነገር ማንሳት ከጀመርን በነዚህ ስፍራዎች የሚቀጠሩ ሰራተኞችን ጉዳይም ዝም ማለት አይቻለንም። ተቀጣሪ አስተናጋጆች በሆቴሎቹ ከመቀጠራቸው በፊት የጤና ምርመራ ማካሄድ እንደሚኖርባቸው በሕግ ተደንግጓል ፡፡
ይህን ምርመራ በኃላፊነት ወስዶ የሠራተኞችን የጤና ሁኔታ የማረጋገጥ ድርሻ ደግሞ በቀጣሪዎቹ ባለሆቴሎች ላይ የተጣለ ግዴታ ነው።ይህ ይሆን ዘንድም በዘርፉ ላይ የተጣለው ሕግ በግልጽ ያስገድዳል።ወደ ተግባራዊ እውነታው ስናልፍ ግን ቀጣሪ ባለምግብ ቤቶች የራሳቸውን ግዴታ ለሠራተኞቹ ብቻ አሳልፈው ሲሰጡ ይስተዋላል፡፡
የጤና ምርመራው ግዴታ የተጣለባቸው ተቀጣሪዎች በቂ መረጃና ግንዛቤ ስለማይኖራቸው በራሳቸው ወጪ ተመርምረው የጋራ ኃላፊነቱን በግላቸው ግዴታ ይወጡታል፡፡ ቀጣሪዎቹ ለጤና ምርመራው የሚያወጡት ክፍያ ከፍተኛ የሚባል አይደለም። ክፍያውን አጠናቀው ግዴታቸውን ቢወጡ ወጪው ኪሳቸውን አይጎዳም፣ በጀታቸውን አይጋፋም።ይሁን እንጂ በርካቶቹ የእነሱን ግዴታ በተቀጣሪዎቹ ጫንቃ ላይ በመጣል ኃላፊነትን ሲሸሹት ይስተዋላል።
ይህን የሚያደርጉት ምንአልባትም ስለጤና ምርመራው ግንዛቤው ካላቸው መካከል ጥቂቶቹ ብቻ ይሆናሉ።ከነሱ በባሰ ምርመራው ላይ ቁብ የማይሰጣቸው በርካቶች ደግሞ የተጣለባቸውን ኃላፊነት አውቆ በመተው ፣ አልያም ስለሕጉ ‹‹አናውቅም›› በሚል ሰበብ ከትከሻቸው ያወርዳሉ።ይህ አይነቱ ምክንያት ቀጣሪዎች ለጤና ምርመራው ትኩረት እንዳይሰጡና ከነጭራሹም ግዴታቸውን እንዳይሞክሩት ማሳበቢያ ይሆናል፡፡
በጣም የሚገርመው ነገር ይህ አይነቱ ውል አልባነት በሚካሄድበት የሥራ አካባቢ የሚመለከተው ሕጋዊ ተቆጣጣሪ አካል በወጉ ኃላፊነቱን ያለመወጣቱ እውነት ነው ፡፡ እንዲህ አይነቱ ግልጽ የሆነ ማሳያም በሕግ የተቀመጡ ደንብና መመሪያዎች በአግባቡ እንዳይተገበሩ መሰናክል ይሆናል።በተመሳሳይ በሙያው ዘርፍ ለሚሰማሩ ሌሎች አካላት በጎ ያልሆነ ምልክትን ይጠቁማል።በነበረው አግባብ ያልሆነ መስመር መቀጠሉም አሰራሩ ትከክል ነው ተብሎ እንዲታመን የሚኖረው ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው።
በጽሁፌ መግቢያ ላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት በሥራ ላይ ለሚያጋጥሙ የሕግ ጥሰቶች የሚመለከታቸው አካላት ብቻ ተጠያቂዎች ሊሆኑ አይገባም። የጉዳዩን ባለቤት ጨምሮ ‹‹ያገባኛል፣ ይመለከተኛል›› የሚል ታዛቢ ሳይቀር ከኃላፊነቱ ድርሻ ይካፈላል፡፡ አንዳንዴ ግን የሕግ አስፈጻሚው ግዴለሽነት በግልጽ ሲስተዋል ከማሳዘን አልፎ ያበሳጫል።ችግሮች ስር ከመስደዳቸው በፊት ተገቢ እርምጃዎች ያለመውሰድም ኃላፊነትን ከመዘንጋት ባለፈ በድርጊቱ እንደመተባበር ይቆጠራል፡፡
ቸልተኝነት ሁሌም ዋጋ ማስከፈሉ አይቀሬ ነው።በወቅቱ የማይፈጸም ሕጋዊነትም ከሕገወጥነት ተነጥሎ አይታይም።ሕግን በአግባቡ ለማስፈጸም ደግሞ የሁሉም አካላት ዓይኖች በእኩል ሊቃኙ ይገባል።እንዲህ ካልሆነ አንዱ በሌላው ሲያሳብብ ጀንበር ትጠልቃለች፣ ሀገር በገሀድ ትጎዳለች፡፡
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 19 ቀን 2015 ዓ.ም