ከጠዋቱ 1:30 አካባቢ ይሆናል። ከሰርቪስ ወርጄ በፈጣን እርምጃ ወደ ቢሮ ልገባ እየገሰገስኩ ነበር። ከኋላየ ‹‹እህት›› የሚል ድምፅ ሰማሁ፣ ጥሪው እኔን የሚመለከት ስላልመሰለኝ ወደኋላ ሳልዞር መራመዴን ቀጠልኩኝ። ሁለተኛ ሲጠራኝ ግን እሱም ከኔ እኩል እየተራመደ ከጎኔ ሆኖ ነበር። ደግሞ እህት ሲለኝ እኔም አቤት ምን ነበር? አልኩት ፈጣን እርምጃየን ሳልገታ።
‹‹አንዴ ስሚኝማ እባክሽን የሆነ ነገር ላስቸግርሽ›› አለኝ። እኔም ለአፍታ እርምጃየን ዝግ እድርጌ ርቀቴን ጠብቄ በመቆም በድጋሚ ምን ነበር? አልኩት። በእጁ ስልክ ይዟል፣ ጠቅ ጠቅ እያልን የምንጠራት ዓይነት ስልክ፣ ‹‹እባክሽን የስራ ውድድር ነበረኝና ወደ ሲኤምሲ ሄጄ መፈተን አለብኝ እዛ በግማሽ ሰዓት መግባት ይኖርብኛል ካልሆነ በቃ ፈተናው ያመልጠኛል›› እያለ ብዙ ዝርዝር ነገር ያወራ ጀመር።
ይንተባተባል መረጋጋት አይታይበትም። የስራ ፈተና ልፈተን ነው ሲለኝ (ለወራትም ቢሆን እኔም ስራ አጥ ነበርኩኝና) በመሃል ሃሳቡን አቋርጬ ታዲያ እኔ ምን ልርዳህ አልኩት የምችለውን ልረዳው በማሰብ፡፡ ልክ ቦርሳየ ውስጥ እጄን ስሰድ አርባ ብር የሚሆን ዝርዝር አገኘሁና ይህ ሲኤምሲ ያደርሰሃል? ብየ ሰጠሁት። መናገር አላቆመም እስካሁን እያወራ ነው፣ አሁንም ይቅበዘበዛል፣ እኔም እንዳይረፍድበት ውድድሩ እንዳያመልጠው ይሆናል እንዲህ የሚሆነው ብየ ልረዳው ፈለግኩኝ።
‹‹ይበቃኛል፣ በጣም ነው የማመሰግንሽ፣ እውነት ጥሩ ሰው ነሽ፣ እግዚአብሔር ይስጥልኝ›› ሌላም ሌላም አለ። እኔም ምንም አይደል መልካም እድል ብየ ትቼው ልሄድ ስሰናዳ ‹‹ ጥሩ ሰው ስለሆንሽ ላመሰግንሽም ካለፍኩኝ ደውየ መልካም ዜና እንድነግርሽ፣ አሁን ስለቸኮልሽ ምንም አልልሽም፣ ስልክሽን አትሰጪኝም? አለኝ፡፡
እኔም እሺ ብየ ከኋላየ ትቼው ወደ ፊት እየተራመድኩ 09 21……. ብየ ነገርኩት፣ ግን በጣም ፈጥኜ ስለነበር ቁጥሮቹን የጠራኋችው ይይዘዋል ብየ አስቤ አልነበረም፡፡ እሱ ግን ካሰብኩት በላይ ፈጣን ነበርና ይዞታል። በቅፅበት ደወለ፣ ስልኬ ቦርሳየ ውስጥ ሆኖ ይነዝረኛል። ተገረምኩ ስልኬን ከቦርሳየ አውጥቼ አላየሁም። ቢሮየ ገብቼ አረፍ እንዳልኩ የተደወለውን ስልክ ሳየው እድሜ ለቴክኖሎጂ የደወለልን ሰው ማን እንደሆነ ከኛ ቀድሞ የሚነግረንን (true caller) አበበ ለማ (ስሙ የተቀየረ) ብሎ አመጣልኝ። እኔም በውስጤ መልካም እድል ይሁንልህ አበበ ብየ ስልኬን መልሼ በማስቀመጥ ወደ ስራ ገባሁ።
ወደ ከሰዓት አካባቢ የማላውቀው ስልክ ይደወላል፣ አሁንም እድሜ ለtrue caller ስሙን ማን ቢለው ጥሩ ነው?! “ጉዳይ ገዳይ” በሰዓቱ ምንም አልገባኝም ነበር፣ አንስቼም አላወራሁትም፣ አበበ ይሆናል ብየ እርግጠኛ ስላልነበርኩኝ በዝምታ አለፍኩት። ምን አይነት ስም ነው? ብየ ራሴን በመጠየቅ ዝም አልኩኝ፡፡
ብዙ ግዜ አዲስ ስልክ አላነሳም። ማታ ወደ 12:30 አካባቢ ቤት ገብቼ አገር አማን ብየ ገና አረፍ ሳልል እንደገና ሌላ አዲስ ስልክ ተደወለ። የአሁኑ ግን እንቆቅልሹን በደምብ የሚፈታልኝ ስም ነበር የመጣው “ሌባው” ይላል። ደነገጥኩኝ፣ አነሳሁና አቤት አልኩኝ። ‹‹እንደምን ዋልሽ›› ይላል ደዋዩ፣ የማውቀው ድምፅ ነው። ጥዋት 1:30 ሰምቼዋለሁ። እግዚአብሔር ይመስገን እንደምን ዋልክ፣ ‹‹የጥዋቱ ልጅ ነኝ›› አለ፣ አሁንም እንደ ጥዋቱ ንግግሩ ፋታ አይሰጥም። አወኩህ አልኩት። ‹‹ላመሰግንሽ ነው፣ ፈተናውን እኮ አለፍኩ፣ እድሜ ላንቺ…›› ምናምን እያለ ቀባጠረ፡፡
እንኳን ደስ ያለህ ደስ ይላል አልኩት። ‹‹ጥዋትም ቀንም ደውየ ነበር አታነሺም›› ሲለኝ፣ ጥሩ ማረጋገጫ ነው አልኩኝ በውስጤ፡፡ እና በቃ ደስ ብሎኛል ስላለፍክ አንተም እንኳን ደስ ያለህ ግን ደግመህ እንዳትደውል አልኩት። ‹‹እንዴ ምነው እኔማ ለዚ ጥሩነትሽ እራት ልጋብዝሽ ነበር እኮ የፈለኩት›› አለ። እራት? አልኩኝ አሁንም በውስጤ።
አይ ይቅርብኝ አመሰግናለሁ ስለው ለመቆጣት ቃጣው፣ ‹‹አሁን እኮ ብር አለኝ ችግር የለውም፣ የሆነ ጓደኛየ ከውጭ መጥቶ ብዙ ብር ሰጠኝ›› ሲለኝ… ደግሞ የማንን የፈረደበት ኪስ አጥበህ ይሆን? አልኩኝ በውስጤ። በቃ አልፈልግም አልኩህ አይደል እንዴ፣ ለምንድነው የምታስገድደኝ? ብየ ኮስተር አልኩ፡፡ እሱ ግን በቀላሉ የሚፋታ አልሆነም፡፡ ይሄኔ እርሙን ያውጣ ብየ “ማነህ ጉዳይ ገዳይ በቃ አልፈልግም አልኩህ እኮ” ስለው ይበልጥ ተንተባተበ ‹‹ማን ነው ጉዳይ ገዳይ ይባላል ያለሽ›› ሲል በንዴት መጦፉ ያስታውቅ ነበር፡፡
ማንም አልነገረኝም ግን እርግጠኛ ነኝ ብዙ ሰው በዚ ስምህ ያውቀሃል አልኩት። እቅዱን ገና ሳይጀመር ስለከሸፈበት ለእኔ የማይሰማ ነገር ከራሱ ጋር አጉተምትሞ ስልኩን ዘጋሁት። እኔም ፈጣሪየን ከዚህ ስለጠበቀኝ እያመሰገንኩ ለመረጋጋት ሞከርኩኝ።
እራት ሊጋብዘኝ ነው ወይስ የያዝኩትን በሙሉ ነጥቆ ራሱን እና መሰሎቹን ሊጋብዝ? እኔም ለታክሲ እንኳን ሳይቀረኝ ባዶ እጄን ይዤ ቤቴ እንድመለስ?።
ይህን ገጠመኜን ላወጋችሁ የተነሳሁት ካለምክንያት አይደለም፡፡ በአሁኑ ወቅት በከተማችን አዲስ አበባ ልክ እንደ ጉዳይ ገዳይ ብዙ በሌብነት የተሰማሩ ሰዎች እንዳሉ የማይካድ እውነታ ነው።
ሰዎች ከወር ደመወዛቸው ቆጥበው በዚህ ሳምንት ውጪ አውጥተን ሻይ ቡና ማለት ይቅርብን ብለው የገዙትን ስልክ፣ ሰዓት፣ ጌጣጌጥ እና የመሳሰሉት ነገሮችን ነጥቀው እዚህ ግባ በማይባል ዋጋ የሚሸጡ በርክተዋል፡፡ የዘመኑን ሌቦች በምንም መለየት አይቻልም። ማንም በማይጠረጥረው መንገድ ለፍቶ ጥሮ ግሮ የተለወጠ የስራ ሰው መስለው ነው ለሌብነት የሚሰማሩት፡፡
ሌብነት ብዙዎችን ያማረረና ብዙ ነገር ሊያሳጣ የሚችል ፀያፍ ተግባር ነው። ከትንሽ እስከ ትልቅ ደረጃ የሚፈፀም የሌብነት ተግባር ማህበረሰብ ውስጥ መተማመንን እስከማጥፋት የደረሰ አደጋ አለው፡፡ የእውነት ተቸግሮ እርዳታ የሚሻን ሰው ጭምር በጥርጣሬ አይን እንዲታይ ያደርጋል፡፡
ሌቦች ብራችንን ወይም ስልካችንን ብቻ አይደለም እየሰረቁብን ያሉት፣ ሰብአዊነታችንን ጭምር ነው፡፡ በትክክል እርዳታ ለሚፈልጉ ወገኖቻችን እንዳንራራ አድርገዉናል። እርዳታ ስንጠየቅ ኸረ ማንን ልትበላ በፍፁም አላደርገውም ብለን መንገድ ቀይረን እንድንሄድ አድርገውናልና።
በሪሁ ኣረጋ
አዲስ ዘመን ሰኔ 17/2015