ኢትዮጵያውያን ውብ ድብልቅ ማንነት ያላቸው ሕዝቦች የሚኖሩባት ምድር ነች። እነዚህን ሕዝቦች ከቀሪው ዓለም የሚለያቸው በርካታ ባሕላዊ እሴቶች መያዛቸው፤ ከራስ ማንነት የሚቀዱ ብዝኃ እሴቶች ማካተታቸው ጭምር ነው። የኢትዮጵያን ምድር የረገጠና አስተውሎ ለመረዳት የሞከረ ሁሉ በሕዝቦች ኅብረት፣ አመጋገብ፣ አብሮ የመኖርና የመቻቻል፣ የቋንቋ፣ የአለባበስና የተለያዩ የኃዘን፣ የደስታ ሥርዓቶቻችን ሳይደመም አያልፍም።
ከሁሉ በላይ ግን እጅግ ማራኪና በሌላ አገር የማያገኛቸው አስደናቂ እሴቶች እንደሆኑ መረዳት ይችላል። የጎዳና ፌስቲቫሎች ጥምቀት፣ መስቀል፣ ጨምበላላ እና ሌሎችም ልዩ ልዩ ባሕላዊና ሃይማኖታዊ ሥርዓቶቻችን የተመለከተ የአገሪቱን ሕዝቦች ቁልጭ አድርጎ የሚያሳዩ መሆናቸውን ይገነዘባል። እነዚህን ሃብቶቻችን ማኅበረሰቡ ከበርካታ ሺ ዘመናት በላይ ሳይበረዙና ሳይጠፉ ጠብቆ ለአዲሱና መጪው ትውልድ ማስተላለፍ ችሏል።
የዝግጅት ክፍላችን በዛሬው አገርኛ ዓምድ ላይ በዓለም ቅርስነት ከተመዘገቡት መካከል አንዱ የሆነውን የኮንሶ ባሕላዊ እሴቶችን የተመለከተ ዳሰሳ ይዞ ቀርቧል። ኮንሶዎች በዘጠኝ የጎሳ ድምር ውጤት የተገነቡ፣ በሦስት ተፈጥሯዊ የመሬት አቀማመጥና ባሕላዊ አስተዳደራዊ ሥርዓት የታጠሩና (ቲንባ ካራታ ካታና፣ ከና ቁፋ እና ቱሮታ ቲቲባ) ተብሎ የጥንት ባሕላዊ አስተዳደራዊ ሥርዓት ባለቤት የሆነ ሕዝብ ነው።
በዚህ ውስጥም ኢትዮጵያዊ የሆኑ፣ በሌላ በየትኛውም የዓለም ክፍል የማናገኛቸው ድንቅ የተፈጥሮ አጠባበቅ ጥበብ፣ የደስታና የኃዘን ሥርዓቶች ይገኛሉ። እኛም የኮንሶ ባሕላዊ፣ ተፈጥሯዊ ሃብቶች በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡበትን ምክንያትና እሴቶቹን አጉልተው የሚያሳዩ ባሕላዊ ሃብቶቹን እንደሚከተለው እናቀርባለን። መረጃውን ያደረሱን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ ሠራዊት ዲባባ ናቸው።
ኮንሶ – ‹‹አፋ ኾንሶ››
የኮንሶ ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ታታሪና ሥራ ወዳድ ሕዝብ ያለበት አካባቢ እንደሆነ በርካቶች ይመሰክሩለታል። ይህ ታታሪነቱ ከጊዜ ጋር የመጣ ሳይሆን ከቀደሙት ጥንታዊ አባቶቹ የወረሰው ፀጋ መሆኑንም ይናገሩለታል። “ኮንሶዎች ሥራ ይወዳሉ” በሚል ቃል ሁሉም በአንድነት ይስማማል። ከባድ የሚባል ሥራ ለኮንሶ ማኅበረሰብ ሎሚ የመላጥ ያህል ቀላል ነው። ባሕላዊ ዕሴቶች ግንባታ ካልሆነ በቀር በማኅበረሰቡ በፆታ የተከፋፈለ የሥራ መደብ እምብዛም አይስተዋልም። ሴቶች ለኢኮኖሚያዊ ለውጥ ከወንዶች እኩል የመሥራት ባሕል በኮንሶ የተለመደ ነው።
እንደ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ ሠራዊት ዲባባ ገለፃ፤ የኮንሶ ብሔረሰብ “አፋ ኾንሶ” የሚሰኝ የቋንቋ ባለቤት ሲሆን ከምስራቃዊ ቆላማው ኩሸ ቋንቋ ቤተሰብ ይመደባል፡፡ የብሔረሰቡ ቋንቋ ኮንስኛ “አፋ ኾንሶ” ለአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የትምህርት መማሪያና በሥነ ጽሑፍ ዝግጅትና ቋንቋነት እያገለገለ የሚገኝ ነው፡፡
“በ2 ሺህ 22 ስኩዌር ኪሎ ሜትር በላይ የቆዳ ስፋት ያለው ኮንሶ ዞን የመሬቱ አቀማመጥ በአብዛኛው ወጣ ገባና ተራራማ ሲሆን አለትና ቋጥኝ ተፈጥሯዊ ሥነ አቀማመጡ ተፈጥሯዊ ፀጋው ናቸው” የሚሉት አቶ ሠራዊት፤ ከፍታውም ከባሕር ወለል በላይ ከ570 እስከ 2 ሺህ 100 ሜትር ከፍታ ላይ እንደሚገኝ ይገልፃሉ፡፡ የሕዝቡ ኢኮኖሚ መሠረቱ በጥምር ግብርና ላይ የተመሠረተ ሲሆን እንስሳት እርባታና ድለባ፣ የንብ ማነብ፣ ዕደ ጥበብ ሥራዎች፣ ማዕድን ክምችት፣ ንግድና የቱሪዝም ገቢ ኢኮኖሚውን የሚደግፉ ተግባራቶቹ ናቸው፡፡ በታሪክና ባሕል አንቱታን ያተረፈ ሕዝብ ከመሆኑም ባሻገር የኮንሶ ሕዝብ የራሱ ብቻ የሆኑ በርካታ የታሪክና የባሕል እሴቶችም አሉት። ከዚህ እንደሚከተሉት የሚቀርቡት ባሕላዊ ሃብቶች የኮንሶ ብቻ የሆኑ አገር በቀል ባሕላዊ ሃብቶች ናቸው።
ባሕላዊና ሃብቶች
የኮንሶ ማኅበረሰብ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) ከተመዘገበው ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ ታሪካዊ ቅርሶቹ ባሻገር አያሌ እሴቶች ያሉት ሕዝብ ነው። በስፍራው ሲገኙ ታይተው የማይጠገቡ፣ ተሰምተው የማይሰለቹ የሙዚቃና የጭፈራ ባለቤት ሲሆን ከራሱ ማንነት የሚቀዱ ባሕላዊ አልባሳት፣ የአመጋገብ ሥርዓት ባለቤት ነው። በኮንሶ እንኳን ደስታና ፌሽታ ኃዘንም ይደምቃል። ከእነዚህ ውብ እሴቶቹ ውስጥ ለዚህ ለዛሬው ርዕሰ ጉዳያችን ተገቢ ናቸው ያልናቸውን እንደሚከተለው እናቅርብ።
ሞትን በዘፈንና ጭፈራ የሚረታው ኮንሶ
ሞት በኮንሶ ይሸነፋል። ኃዘን ያለና የሚጠበቅ ቢሆንም የኮንሶ ማኅበረሰብ ለመላዕከ ሞት እጁን በቀላሉ የሚሰጥ አይደለም። በአካባቢው ማኅበረሰብ ጥሩ ስምና ዝናን ያተረፉ የጎሳ መሪዎች፣ ታዋቂ ሰዎች ከዚህ ምድር ልፋት እረፍትን ሲያገኙ ኮንሶዎች ሥርዓተ ቀብራቸውን አድምቀው ይሸኟቸዋል። የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ ሠራዊት ዲባባ ጉዳዩን ከዚህ እንደሚከተለው ያብራሩታል።
ኃላፊው እንደሚሉት የኮንሶ ማኅበረሰብ ሰው በሚሞትበት ሰዓት በዘፈን እና በጭፈራ በደስታ የሚሸኝበት ባሕል አለው። ይህም ባሕልም “ሺሌታ” ይባላል። የኮንሶ ብሔረሰብ ማኅበራዊ ትስስሩን ከሚያጠነክርባቸው እና ኢኮኖሚያዊ አቅሙን ከሚገልጥባቸው ባሕላዊ ክዋኔዎቹ መካከል “የለቅሶ ሥርዓት” ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል። ባሕላዊው የለቅሶ ሥርዓት የብሔረሰቡ ልዩ ልዩ ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ እሴቶች የሚታዩበት ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፉበት መንገድ ነው።
“የሞተ ሰው አስከሬን ወደ ሚቀበርበት በሚወሰድበት ጊዜ በዘፈን እና ጭፈራ ታጅቦ ይሸኛል” የሚሉት ኃላፊው፤ ከቀብር ሥነ ሥርዓቱም በኋላ ዘፈኑ እንደሚቀጥል ይናገራሉ። በዚህ የዘፈን ስንኞች ውስጥም ስለሞተው ሰው ደግነት፣ በሕይወት እያለ ስላከናወናቸው መልካም ሥራዎች በማንሳት እንደሚሞገስ ይገልፃሉ። የትውልድ ዘር ሐረጉም ተቆጥሮ በክብርና በሞገስ እንደሚዘከር ነው የሚያብራሩት።
“በዘፈን የሚሸኙ ሰዎችም፣ ‘የተመረቁ ሰዎች ናቸው” ተብሎ ይታመናል የሚሉት የኮሙኒኬሽን መምሪያ ኃላፊው፤ እነዚያም ዘፈኖች የተለያየ ግጥም እንዳላቸው ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ዘፈኑ የሚዘፈንበት ቆይታ የተለያየ መሆኑን ያብራራሉ። የኮንሶ ማኅበረሰብ ሕይወት ከእርሻ ጋር የተያያዘ በመሆኑ፣ እርሻ በሚታረስበት ወቅት የሞተ ሰው የቀብሩ ሥነ ሥርዓት ከተከናወነ በኋላ የዘፈን ሥርዓቱ አመቺ ነው ወደሚባሉት ወራት መስከረም ወይም ጥቅምት እንደሚተላለፍ ይገልፃሉ። አረም በሚታረምበት ወቅት ለሞተ ሰው ደግሞ የዘፈኑ ጊዜ ለጊዜው እንዲቆይ እንደሚደረግም ነው የሚያስረዱት።
ባሕላዊ የስፖርት ጨዋታዎች
ኮንሶ የባለ ብዙ ዕሴት ባለቤት ነው። ከእነዚህ ውስጥ በማኅበረሰቡ ልዩ ስፍራን የሚሰጣቸው ስፖርታዊ ጨዋታዎች አግራሞትን የሚጭሩ፣ የሚናፈቁና የሚወደዱ ባሕላዊ፣ ታሪካዊና ስፖርታዊ ጨዋታዎች በኮንሶ ብሔረሰብ ይገኛሉ። ከእነዚህ ዕሴቶች መካከል የሚከተሉት የኮንሶ ሃብቶችን ለመመልከት እንሞከር።
የሶታ ጨዋታ
“በወንዶች ወጣቶች ብቻ እና ታዳጊዎች ከአቻዎቻቸው ጋር በመግጠም ወኔያቸውን፣ ጥንካሬያቸውን የሚፎካከሩበት ምሽት ከ11 ሰዓት በኋላ የሚጫወቱት ባሕላዊ ስፖርትና ጨዋታ ሶታ ይባላል” የሚሉት አቶ ሠራዊት፤ ሶታ አሸናፊና ተሸናፊ ያለው በሁለት አቻዎች መካከል የሚገጥሙት ባሕላዊ የስፖርት አይነት መሆኑን ይናገራሉ። አሸናፊዎች በትውልድ ዘንድ አይረሴ አሻራ አኑረው የሚያልፉበት ተወዳጅ ጨዋታም መሆኑን ይገልፃሉ። ሶታ በወጣቶችና ታዳጊዎች መካከል የሚኖር ጥንት የነበረ ዛሬም ያለ ነገም የሚኖር የኮንሶ ብሔረሰብ ተወዳጅ ባሕላዊ ጨዋታና ስፖርት ነው፡፡
የኩራይላ ስፖርታዊ ጨዋታ
ሌላው በኮንሶ ማኅበረሰብ ተወዳጅ የሆነው ስፖርታዊ ጨዋታ “ኩራላይ” ይባላል። ተወዳጅ፣ ተናፋቂ፣ ወቅት ጠባቂና የኮንሶ ብሔረሰብ የሆነ ስፖርታዊ ጨዋታ ነው። ጨዋታው በኮንሶ ብሔረሰብ በበጋ ወቅት ወርሐ ጥር እስከ የካቲት መጨረሻ ብቻ የሚካሄድ አይነት ነው። በሁለት የተፈጥሮ ጎራ የተከፈለና እልህ አስጨራሽ ጨዋታው በ”ኩስታና ቃርታ” ወይንም በታናሽና ታላቅ መካከል የሚካሄድ ታላቅ ፉክክር ያለበት ወቅቱን የሚጠብቅ ስፖርታዊ ጨዋታ ነው። ”ኩራይላ” ለኮንሶ ማኅበረሰብ የብቻው ስፖርታዊና ባሕላዊ ዕሴት ሲሆን የጨዋታው ስያሜ ከማጫወቻው ኳስ መሰል ድቡልቡል ሉል አግኝቷል። የጨዋታው ሂደት ኳስ መሰሏን ድቡልቡል ሉል ወደ ሰማይ በመወርወር የሚጫወቱት ጨዋታ አይነት ሲሆን ሁለቱ ተጋጣሚዎች ታናሽና ታላቅ ቡድን በአየር ላይ ኳሷን ቀልቦ በመያዝ ነው። መሬት ብትወድቅ እንኳ በትግልና ጥበብ ያሸነፈ ኳሷን ይዞ እጁን ወደ ሰማይ ከፍ በማድረግ ”ኦርሶ! አና አላዋ ካሪቴ… ኦታይቴ፣ …” በሚል የጀብድነት ማብሰሪያ በእህቱ አሊያም በጎሳው አባል በመማል ኳሷን መያዙን ያረጋግጣል። የዚህን ጊዜ ነው በዙሪያው የከበበው ተመልካች የማን ቡድን ያዘ የሚል ማረጋገጫ የሚሰጡት።
እንደ ኮሙኒኬሽን ኃላፊው ገለፃ፤ በጨዋታው አሸናፊ ሊሆን የሚችለው ቡድን በተከታታይ አምስት ጊዜ ኳሷን የያዘ ቡድን ሲሆን፤ በመሐል ተቃራኒ ቡድን ኳሷን ከያዘ ውጤቱ ከዜሮ ይጀምራል። አንዱ ቡድን በተከታታይ አምስት ነጥብ ባስቆጠረ ጊዜ ደማቅ፣ ሞራላዊና ድል ማብሰሪያ ጭፈራና ቀረርቶ ደጋፊን ጨምሮ ይጫወቱታል። ሴቶች ለጎሳቸው አባል እና ለታናሽና ታላቅ ወንድሞቻቸው ደማቅ ሞራል የሚለገሱ ሲሆን ለአሸናፊና ኳሷን በተደጋጋሚ ይዞ የውጤት ጣሪያ አምስት ነጥብ ከደረሰ ለቡድኑ ከአንገቷ ማጌጫ ጨሌዋን አውልቃ ለአንደኛው አሸናፊ አንገቱ ላይ ታደርጋለች።
ታኬካ (ታሻ)
የኮሙኒኬሽን ኃላፊው አቶ ሠራዊት ካደረሱን መረጃዎች ውስጥ የሆነውና ሌላኛው ስፖርታዊ ጨዋታ ታኬካ (ታሻ) ተብሎ ይታወቃል። ይህም በኮንሶ ለአባቶች እና ጎልማሶች በአመዛኙ የሚጫወቱት ባሕላዊ ጨዋታ ሲሆን፤ ፈለገ ሂሳብ ያለው እንደሆነ ገልፀውልናል። ጨዋታው ማስተዋልን የሚጠይቅ፣ (በሞራ) ባሕላዊ መሰብሰቢያ አደባባይ ብቻ የሚገኝ የኮንሶ ብሔረሰብ ባሕላዊ ጨዋታ ነው፡፡ ታኬካ በማስተዋልና ጥበብ የሚጫወቱት ጨዋታ ሲሆን፤ ጨዋታውን ከአባቶችና ጎልማሶች አልፎ አልፎም ወጣቶች ይጫወቱታል። ይህ ባሕላዊ ስፖርት አይነት ”በዘመናዊ አጠራሩ ገበጣ” ሲሆን በኮንሶ ማኅበረሰብ ባለ 6፣ ባለ 12 ታሻ የሚል ሂሳባዊ ቀመር ያለው ነው።
እንደ መውጫ
የኮንሶ ማኅበረሰብ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) የተመዘገበው ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ ታሪካዊ ቅርሶቹ የሚዘክር በዓል በየዓመቱ ሰኔ 23 ቀን ያከብራል። በአገሪቱና በዞኑ በቅርቡ በተከሰተ የፀጥታ ችግር ምክንያት ለአራት ተከታታይ ዓመታት ሳይከበር ቆይቷል። የኮንሶ ዞን አስተዳደር ዘንድሮ ይህን ዓመታዊ በዓል እንደሚያከብር አስታውቋል። ይህንን ጉዳይ አስመልክተው ይፋዊ ቃል የሰጡት የኮንሶ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ገበየሁ እንዳሉት፤ የኮንሶ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ቅርሶች በዓለም ደረጃ ታዋቂ ነው። ታታሪው የኮንሶ ሕዝብ በዓለም እንዲሁም በሀገር አቀፍ ደረጃ የቅርስ አካል በሆነው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ፣ የእርከን ሥራ እንዲሁም የተፈጥሮ የኮንሶ መልክዓ ምድር አቀማመጡ በሰው የሠራሽ የካብ ጥበብ ዓለም የመሰከረለት ቅርስ ላለፉት አራት ዓመታት ሳይከበር የቆየው የኮንሶ መልክዓምድር ጥበቃና ባሕል ዩኔስኮ በዓል ቀን ከቀናት በኋላ ለማክበር ዝግጅቶች ተጠናቀዋል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ሰኔ 16/2015