በዚያን ጊዜ … እንደዛሬው መገናኛ ብዙሃን ባልተስፋፋበትና መረጃ እንደልብ በማይዛቅበት ዘመን የጋዜጠኝነት ሙያ እንዲያድግ ፈር ቀዳጅ ከሆኑና የበኩላቸውን አሻራ ጥለው ካለፉ አንጋፋ ባለሙያዎች አንዱ ነው። በዚህም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን መስኮት ላይ ቀርቦ በዜና አቅራቢነት ለመጀመሪያ ጊዜ በቴሌቪዥን መስኮት የታየ ታሪካዊ ሰው ለመሆን የበቃው ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ ተዋናይ፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ሳሙኤል ፈረንጅ ነው።
ጋዜጠኛ ሳሙኤል ፈረንጅ ከአባታቸው ከቀኝ አዝማች ፈረንጅና ከእናታቸው አበበች ገመዳ በ1929 ዓ.ም ወለጋ ጠቅላይ ግዛት፣ ነቀምት ከተማ ተወለዱ። የ1ኛ እና የ2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በደምቢ ዶሎና በአዲስ አበባ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ተከታትለው ጨርሰዋል። ከዛም የከፍተኛ ትምህርታቸውን በጅማ እርሻ ኮሌጅ ተከታትለዋል። በኮሌጁ የከፍተኛ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ በነበረበት ወቅት የጋዜጠኝነት ተሰጥኦና ፍቅሩ ስለነበራቸው ትምህርት ቤቱ በሚያሰራጨው የሬዲዮ ፕሮግራም ላይ ያገለግሉ ነበር።
እርሳቸውም በነበራቸው የጋዜጠኝነት ሙያዊ ብቃት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አገልግሎት ሳይጀመር የአፍሪካ አንድነት ስብሰባ ሪፖርትን በቢቢሲ ረዳት መረጃ አቅራቢነት ተቀጥረው በዓለም አቀፍ ደረጃ ይዘግቡ ነበር። በቢቢሲ ረዳት መረጃ አቅራቢነት ተቀጥረው የሬዲዮ ጋዜጠኝነት ልምድ ከመቅሰማቸው በተጨማሪ እንግሊዝ አገር ከሚገኘው የታምሰን ብሮድ ካስቲንግ ኮሌጅ በቴሌቪዥን ጋዜጠኝነት እና አስተዳደር ትምህርትና ሥልጠና ወስደዋል።
በዚህም የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከተቋቋመ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በአገሪቱ በቴሌቪዥን መስኮት ላይ ቀርበው በዜና አቅራቢነት ለመጀመሪያ ጊዜ የታዩ ታሪካዊ ሰው ከመሆናቸው ባለፈ በነበራቸው የጋዜጠኝነት ሙያዊ ብቃትና ችሎታ በአፄ ኃይለሥላሴ ተመርጠው በአዋጅ የቀድሞው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ድርጅት ዋና ዳይሬክተር በመሆን አገልግለዋል።
ሁለገብ ባለሙያ የነበሩት ጋዜጠኛ ሳሙኤል ከጋዜጠኝነት ሙያ ባሻገር “አጽም በየገጹ” በተሰኘው የሎሬት ፀጋየ ገ/መድህን ቲያትር ላይ የጄኔራል መንግሥቱ ንዋይን ገፀ ባሕሪ ተላብሰው በብቃት ተውነዋል። ከዚህ ባሻገር የጥፋት መንትዮች እና መሰንበት ደጉ የተሰኙ መጽሐፎችን ለንባብ አብቅተዋል። “መሰንበት ደጉ” በሚለው የግጥም ስብስብ/መድብል መጽሐፋቸው አርስት ያደረጉትን እና የመጽሐፉ ሽፋን ላይ ያስቀመጡትን ግጥም እንደሚከተለው ላካፍላችሁ ወደድሁ።
መነጽር ይገዛል፣
ሞኝ የጨዋ ልጅ፣
ሁሉን የሚያሳየው፣
መሰንበት ነው እንጂ! ብለው ገጥመዋል።
ጋዜጠኛ ሳሙኤል በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት በጋዜጠኝነትና በሥራ አስኪያጅነት ለረጅም ዓመታት አገራቸውን እና ሕዝባቸውን ከማገልገላቸው ባሻገር በንጉሱና በደርግ ዘመነ መንግሥት በማስታወቂያ ሚኒስቴር፣ በፍትህ ሚኒስቴር፣ በእርሻ ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ በመሬት ይዞታ ወዘተ. በመሳሰሉ የመንግሥት ተቋማት በከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ተመድበው አገልግለዋል።
በኋላም የንጉሱ ሥርዓት አክትሞ የደርግ መንግሥት ሲመጣ እንደአብዛኛዎቹ ጋዜጠኞች “የዘውድ መንግሥቱ የሃሳብ አራማጆችና ደጋፊዎች” ነበራችሁ ተብለው ከሚወዱት ከጋዜጠኝነት ሙያ ከተገለሉና የጥቃት ኢላማ ከተደረጉ ዕውቅ ጋዜጠኞች አንዱ ነበሩ። እንዲሁም እሳቸው በወቅቱ ይስተዋል የነበረውን የጭቆና ሥርዓት “በግልጽ ይተቹና የነበረውን የመልካም አስተዳደር ችግር ይናገሩ” ስለነበር የቁም እስረኛ ተደርገው ነበር። በዚህም በሕይወት የመኖር ዋስትናቸው ጥያቄ ምልክት ውስጥ በመግባቱ አገራቸውን ጥለው እስከለተ ሕይወት ፍጻሚያቸው በስደት ለመኖር ተገደዋል።
ጋዜጠኛ ሳሙኤል አገሩን በስደት ለቆ ከወጣ በኋላ በጀርመን፣ በጣሊያን እንዲሁም ሕይወቱ እስካለፈበት ድረስ በካናዳ ቶሮንቶ ለረጅም አመታት ኖሯል። ይሁን እንጂ የወገኑና የአገሩን ፍቅር በልቡ ይዞ የተሰደደው ጋዜጠኛ ሳሙኤል በስደት በኖረባቸው አገራት ለኢትዮጵያዊያን ወገኖቹ አለኝታ ከመሆን ባሻገር ለጥቁር ሕዝቦች የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ነበር። ለአብነት በጀርመን በስደት ይኖር በነበረበት ወቅት በ1980ዎቹ የጀርመን መንግሥትና ባለስልጣናት “ጥቁሮች ናቸው የኤች አይ ቪ ቫይረስን ያመጡብን” የሚል የተዛባ ሃሳብ በመገናኛ ብዙሃን ያራምዱና ያሰራጩ ነበር። ጀርመንኛና ሌሎች የአውሮፓ ቋንቋዎችን አቀላጥፎ ይናገር የነበረው ትንታጉ ጋዜጠኛ ይህንን ሰብዓዊ ክብርን የሚነካ ንግግር የጀርመን ባለስልጣናት ሲናገሩ በመስማቱ፤ በአንድ ታዋቂ የጀርመን ጋዜጣ ላይ “እናንት የጀርመን ባለስልጣናት ጥቁሮች የኤች አይ ቪ ቫይረስ አመጡብን። ስለዚህ ይመርመሩ ብላቹህ የኤች አይ ቪ ቫይረስ ብትወጉን በምን እናውቃለን” የሚል በጣም ከፍተኛ ትችት ጽፎና ሃሳባቸውንም አውግዞ ነበር። በዚህም በጀርመን ባለስልጣናትና መንግሥት ጥርስ ውስጥ በመግባቱ ወደ ጣሊያን አገር ለመሰደድ ተገዷል።
ወደ ጣሊያን ባቀናበት ወቅት ደግሞ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ቤት አልባ ሆነው ኑሯቸውን ይገፉ የነበረው ጎዳና ላይ ነበር። ያኔ በጣሊያን አገር የወገኖቹን መራብ፣ መታረዝ፣ መራቆት… አይቶ እንዳላየ ማለፍ ስላልቻለ በወቅቱ ከነበሩት ፖፕ ሁለተኛ ጋር ቀርቦ “ኢትዮጵያን ከሚያህል ታላቅ አገር የመጡ ሰዎች እርስዎ ባሉበት ቦታ እንዲህ ጎዳና ላይ ወድቀው እያዩ እንዴት ዝም ይላሉ” ብሎ በጉልበቱ ተንበርክኮ መፍትሄ ማድረግ አለብዎት ብሎ ይማጸናቸዋል። ፖፕ ሁለተኛም “መፍትሄ አድርጋለሁ ከተንበረከክበት ተነስ” ሲሉት “ቃል እገባለሁ (promise) ካላሉ አልነሳም” ብሎ እግራቸው ላይ በግንባሩ ይደፋል። እርሳቸውም “ቃል እገባለሁ” ብለው ሁለት እጁን ይዘው እግራቸው ላይ ከወደቀበት አነሱት። ከዛም በገቡት ቃል መሰረት ተዘግተው የነበሩ በርካታ የንግድ ቤቶች ተከፍተው ለኢትዮጵያዊያኖች ማደሪያ እንዲሆን ተደረገ። ጋዜጠኛው ያኔ በጣሊያን አገር ጎዳና ላይ ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያዊያን መጠለያና ምግብ እንዲያገኙ ከማድረጋቸው ባሻገር የኢትዮጵያዊያን ማህበረሰብ ማህበር በሮም አቋቁመው የስደተኞች ሰብዓዊ መብት እንዲጠበቅ አድርገዋል።
በመጨረሻም ወደ ካናዳ ቶሮንቶ አቅንቶ ሌላ የስደት ኑሮ የመሰረተው ጋዜጠኛ ሳሙኤል ፈረንጅ፤ በስደት በሄደበት አገር ሁሉ ከኢትዮጵያዊያን ጎን በመቆም ወገኖቹን መርዳት ዋነኛ መርሁ ስለነበር ለካናዳ ፍርድ ቤቶች በተለይ አማርኛና ኦሮምኛ እያስተረጎመ ወገናቸውን ይረዱ ነበር። እንዲሁም በካናዳ ቶሮንቶ ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እንግሊዝኛ፣ ጀርመንኛ. ወዘተ የመሳሰሉ ቋንቋዎችን በነጻ ከማስተማር ባለፈ የተለያዩ ቲያትሮችን እየጻፉ ያቀርቡ ነበር።
በዚህም በሕይወት ዘመናቸው በሠሩት ሥራ ከተለያዩ 17 አገራት የክብር ኒሻን ሜዳሊያ አግኝተዋል። ለዋቢነት ለአገራቸው ላበረከቱት አስተዋጽኦ በኢትዮጵያ የመኮንን ደረጃ የክብር ኮከብ ኒሻን ሽልማት አግኝተዋል። በተመሳሳይ ከካናዳ መንግሥት የክብር ኮከብ የመኮንንነት ደረጃ ኒሻን ተሸልመዋል። ከጣሊያንና ከኦክላህማ አገራት የክብር ዜግነት አግኝተዋል። እንዲሁም ለእንግሊዟ ልዕልት ዲያና የጻፈው ግጥም አሸናፊ በመሆኑ፣ ከአሜሪካ ብሔራዊ የገጣሚያን ቤተመጽሐፍት ትልቁ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
በአጠቃላይ ጋዜጠኛ ሳሙኤል ፈረንጅ በኢትዮጵያዊነቱ የሚኮራ አገር ወዳድ ነበር። ይህንንም በሕይወት ዘመኑ እያለ በተግባር አስመስክሯል። ለኢትዮጵያ አገሩ የነበረው ራዕይም አገሩ በአንድነቷ ጸንታ የበለጸገች፣ ሕዝቦቿ በሰላም ተከባብረው የሚኖሩባተ አገር እንድትሆን ነበር። ለአገሩም በዓለም አደባባይ በጣም ብዙ ተሟግቷል። ከደርግ ዘመነ መንግሥት መውደቅ በኋላ የሰላም እና የእርቅ ጉባኤ በአዲስ አበባ እንዲደረግ የፖለቲካ ድርጅቶች ፓሪስ ላይ ወስነው በነበረ ወቀት ኢህአዴግ በዛ ድርድር ውስጥ አልሳተፍም ብሎ ነበር። በዚያን ጊዜ ያሉ ልዩነቶች በድርድር ተፈትተው በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ጋዜጠኛው ከልብ ፍላጎት ስለነበረው፤ የካናዳ መንግሥት የኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ተጽዕኖ እንዲያደርግ በመወትወት ኢህአዴግ በእርቁ እንዲሳተፍ ከፍተኛ ግፊት ያደርጉ ከነበሩ ሰዎች ውስጥ አንዱ ነበሩ። ከዚህ ባሻገር ኢህአዴግ ሥልጣን ከመቆጣጠሩ በፊት የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች (ኢሐፓ፣ መኢሶን) ሌሎቹም ያኔ ተከፋፍለው በቀይና ነጭ ሽብር አገሪቱን ሲንጧት በነበረበት ጊዜ ልዩነታቸውን ወደጎን ብለው እንዲተባበሩ ሲሠሩ ከነበሩ ሰዎች መካከል አንዱና ግንባር ቀደሙ ነበሩ።
የኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ሁልጊዜም በንቃት በመሳተፍ ሕዝቡ በሰላም፣ በብልጽግና የሚኖርባት አገር እንድትሆን የበኩሉን ሚና ሲወጣም ነበር። ኢትዮጵያን የሚያሳንስ የፖለቲካ አካሄድን አጥብቆ የሚጠየፍ ስለነበር፤ ኢህአዴግ ይዞ ብቅ ያለውን ፖለቲካን ሲቃወም ኖሯል፡፡ ኢትዮጵያን የሚያሳንሱ የፖለቲካ ድርጅቶችንም አጥብቀው ይቃወሙና ያወግዙም ነበር። በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ምንም የማያወላውል አቋም ስለነበራቸው፤ የወጡበት ብሔር ተወላጅ የሆኑ የዘር ፖለቲካ አቀንቃኞች ዘንድ ጭምር ማንነታቸውን እስከመካድና እስከመወገዝ ድረስ ይደርስባቸው ነበር።
በአገሪቱ የጋዜጠኝነት ሙያ ፈር ቀዳጅ ባለወርቃማው አንደበት፤ በሄደበት ሁሉ ከወገኑ አልፎ ለጥቁር ሕዝብ ዋስ ጠበቃ የሆነው ጋዜጠኛ ሳሙኤል ፈረንጅ በመጨረሻም ለካናዳ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የ1960ዎቹን ሙዚቃዎች አስመልክቶ የዶክመንታሪ ፊልም በመሥራት ላይ እያለ የጤና ችግር ይገጥመዋል። ቶሮንቶ በሚገኝ አንድ ሆስፒታል ሲረዳ ቆይቶ ባደረበት ህመም በተወለዱ በ81 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ጋዜጠኛ ሳሙኤል ፈረንጅ የስምንት ልጆች (አንድ ሴትና ሰባት ወንድ ልጆች) አባት፣ የስምንት ልጆች አያት እና የአንዲት ልጅ ቅድመ አያት ነበሩ። የጋዜጠኛ ሳሙኤል የቀብር ሥነ-ሥርዓት ኅዳር 23 ቀን 2010 ዓ.ም በቶሮንቶ ካናዳ ተፈጽሟል።
በጋዜጠኛ ሳሙኤል ፈረንጅ የተጻፈ “ይቅር በለኝ ዓባይ” የተሰኘውን ከግል ሕይወቱ ጋር የተያያዘውን አጭር ግጥም እንደሚከተለው ላካፍላቹህ ወደድሁ፤
ለካስ አንተም እንደኔው ተከፍተህ፣
ከአገር መውጣትህ ነው ሸፍተህ፣
አንሠራ አናሠራ ስላሉህ ነው፣
አገርህን ጥለህ የኮበለልከው፣
መቀበሪያ አፈርህን ያዘልከው፣
ምንኛ ይመሳሰላል ታሪካችን፣
በዛው ተሰደን መቅረታችን! በሚል ጋዜጠኛው ስንኞችን ደርድሮ ነበር። ታሪክ ተቀይሮ ዓባይ በቤቱ መቀበሪያ አፈሩን ይዞ ሲያድር፣ የሰው አገር ሲሳይ መሆኑ ቀርቶ ለአገሩ ሲሳይ መሆን ሲጀምር፤ አገርና ወገኑ ቀና እንዲሉ እድሜ ዘመኑን ሙሉ የደከመው ጋዜጠኛ ሳሙኤል ግን በዛው በስደት አፈር ለብሶ መቅረቱ ለኛ ውለታ ለዋለልን የኢትዮጵያ ሕዝብ የእግር እሳት ነው።
ጋዜጠኛ ሳሙኤል ፈረንጅ፤
ሰለሞን በየነ
አዲስ ዘመን ሰኔ 14/2015