የዛሬው የአዲስ ዘመን ድሮ አምዳችን ከ30 አመታት በፊት የተከወኑ አገራዊ የፖለቲካ ጉዳዮችን በብዛት ይዳስሳል። የደርግ መንግስት ወድቆ የኢህዴግ መንግስት ዙፋኑን ሲረከብ በአገር ደረጃ የተካሄደ የእርቀ ሰላም ጉባኤን አስመልክቶ የወጡ ዘገባዎች ምን ይመስሉ ነበር…? በጊዜው የአገሪቱ የውስጥ የፀረ-ሰላም ኃይል ከተባለው ኦነግ ጋር በተያያዘ ለፕሬዚዳንቱ መለስ ዜናዊ ከጋዜጠኞች የቀረበ ጥያቄ እንዲሁም መግለጫም ነበር። ያንን ሥርዓት አንደግመውም ይላሉ ፕሬዚዳንቱ …ከዚሁ ጋር በተያያዘ ኦነግ በወቅቱ ዋና ጸሃፊው የነበሩትን ሌንጮ ለታን አባሯል። በሌላ በኩል ደግሞ የሲውዲን ዜጋን የዘረፉት ግለሰቦች ይፈለጋሉ፤ እነዚህና ሌሎችም ጉዳዮች ተካተዋል።
“ያንን ሥርዓት በምንም አይነት መልኩ ተመልሶ እንዳይመጣ ሰብረነዋል”
-የፕሬዝዳንት መለስ ጋዜጣዊ መግለጫ
…….
ጥያቄ-”የእርቅና የሰላም ጉባኤ የተባለውን ምክንያት በማድረግ ኦነግ የሚካሄደውን ጦርነት ለ7 ቀን እንዲቆም ትዕዛዝ አስተላልፌአለሁ የሚል ዜና አሰረጭቷል። ይሄ ምን ለማለት ተፈልጎ ነው? የእርቅና የሰላም ጉባኤ የሕገ መንግስቱን ማርቀቅና የምርጫውን ሂደት ሊያደናቅፈው ወይም ፈጽሞ እንዳይካሄድ ሊያደናቅፈው ይችላል?
………….
መልስ- መልካም ኦነግ ጦርነቱን ለ7 ቀን አቁሜአለሁ የተባለው እኔ እስከማውቀው ድረስ ለ7 ቀን ብቻ ሳይሆን ለረዥም ጊዜ እንዳቆመ ነው። (አዲስ ዘመን ታህሳስ 17 ቀን 1986ዓ.ም)
የሰላምና እርቅ የተባለ ጉባኤ ተከፈተ
በመሀላችን ያለው ሰፊ የአመለካከት ልዩነትን ከተጨባጭ ስምምነት እያደረስን የሚል ስጋት ያንዣበበበትና የጉባኤው ቅንጅት አለመኖር የታየበት የዕርቀ ሰላሙ ጉባኤ አጀንዳውን ቢያፀድቅም በቅደም ተከተሉ ላይ ከስምምነት አልደረሰም።
ጉባኤው ዶ/ር በየነ ጴጥሮስን በሰብሳቢነት፣ ዶ/ር ታየ ወልደ ሰማያትን ደግሞ በፀሐፊነት የመረጠ ሲሆን እንዲሁም አስራ አምስት አባላትን ለጉባኤው ሪፖርተርነት ከልዩ ልዩ ድርጅቶች ከግል ፕሬስ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከስራ ከተወገዱ መምህራን እንዲሁም ከዩኒቨርሲቲ ከተባረሩ ተማሪዎች ኮሚቴ ተመርጠዋል ። (አዲስ ዘመን ታህሳስ 17 ቀን 1986ዓ.ም)
ኦነግ ሌንጮ ለታን አባረረ
-አቶ ሌንጮ ለታ እጃቸውን ሰጡ
(ኢ.ዜ.አ)- የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ምክትል ዋና ጸሃፊ የነበሩትን አቶ ሌንጮ ለታን ከትናንት ታህሳስ 14/1986ዓ/ም ጀምሮ ከግንባሩ ኃላፊነታቸው ያስወገዳቸው መሆኑን ትናንት አስታወቀ፡፡
የአቶ ገላሳ ዲልቦ የኦነግ ዋና ጸሐፊ ፊርማ እንዲሁም የግንባሩን ማህተም የያዘው መገለጫ እንዳመለከተው ከአሁን ወዲያ ሌንጮ ለታ ግንባሩን የማይወክሉና በኦነግ ስም ምንም አይነት መግለጫም ሆነ ተግባር ሊያከናውኑ እንደማይችሉ ሕዝቡም ሆነ የግንባሩ ደጋፊዎችና ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ እንዲያውቁልኝ ሲል ገልጿል፡፡
………….
ይሄው የግንባሩ ማዕከላዊ ኮሚቴ መግለጫ እንዳመለከተው በአቶ ኢብሳ ጉተማ መታሰር ሳቢያ ኦነግ የሰላምና የእርቅ ጉባኤ ላይ ሳይሳተፍ መቅረቱን ገልጿል፡፡
የኦነግ አመራር አባል ተያዙ
(ኢ.ዜ.አ)- አቶ ኢብሳ ጉተማ የኦነግ የአመራር አባል በድርጅታቸው በኩል ጦርነት እንዲካሄድ አሳውጀው ጉዳት እንዲደርስ ካደረጉ በኋላ አዲስ አበባ ገብተው በመገኘታቸው በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የፖሊስ ሠራዊት ማዕከላዊ ቢሮ አስታወቀ። (አዲስ ዘመን ኅዳር 13 ቀን 1986ዓ.ም)
የአሜሪካ መንግስት ስለ ኢትዮጵያ የአቋም ለውጥ አለማድረጉን ገለጸ
የዩናይትድ ስቴትስ መንግስት ሰላምና እርቅ ስለተባለው ኮንፈረንስ ያለውን አቋም አዛብቶ ለማቅረብ የተለያዩ የግል መጽሔቶችና ጋዜጦች የተቀነባበረ ዘመቻ በማድረግ ላይ ናቸው።
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ሚስተር ማርክ ባስ ሰሞኑን የሰጡትን ጋዜጣዊ መግለጫ የዘገቡት በርካታ የግል ጋዜጦችና መፅሄቶች አሜሪካ በኢትዮጵያ የሽግግር መንግስት ላይ ያላትን የእምነትና የድጋፍ ፖሊሲ የቀየረች አስመስለው ቢያቀርቡም በአሜሪካ በኩል አንዳችም የአቋም ለውጥ አለመኖሩን በዚያው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አምባሳደሩ በተደጋጋሚ አረጋግጠዋል።
…………
ሀቁ ይህ ሆኖ ሳለ ሙዳይ የተባለው ሳምንታዊ የግል ጋዜጣ በታኅሳስ 3 እትሙ ላይ እንደዘገበው የአሜሪካ መንግስት የታኅሳስ ዘጠኙን የሰላም እና የእርቅ ጉባኤ እንደ ታላቅ ቁምነገር በመመልከት የአቋም ለውጥ አሳይቷል ከሚል የሌለ ድምዳሜ ደርሷል። (አዲስ ዘመን ታኅሳስ 23 ቀን 1986ዓ.ም)
በቄለም አውራጃ የዱር አራዊት አዝመራ አጠፉ
በወለጋ ክፍለ ሀገር በቄለም አውራጃ የዱር አራዊት ገበሬዎች የዘሩት አዝመራ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሱት ገበሬዎች ለአብዮቱ በዓል አዲስ አበባ መጥተው በሰነበቱበት ወቅት መሆኑን የቄለም ወረዳ ገበሬ ማህበራት ተወካዮች ገለጡ።
በቄለም ወረዳ በየዱሩ የሚኖሩ የዱር አራዊት ዝንጀሮ፣ ጦጣ፣ ከርከሮ፣ ጎሽ፣ አሳማና የአንበሳ መንጋ በሌሊት ከየደኑ እየወጡ የገበሬዎቹን አዝመራ ከመብላታቸውም በላይ በቤት እንስሳትና በሰውም ጉዳት ማድረሳቸውን የአውራጃው የገበሬ ማህበር ሊቀመንበር አቶ አሸብር ኩምሳ ገልጠዋል። (አዲስ ዘመን መስከረም 14 ቀን 1969ዓ.ም)
የሲውዲን ዜጋን የዘረፉት ይፈለጋሉ
(ኢ.ዜ.አ)- አዲስ አበባ ላይ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በወረዳ 13 የቀይ መስቀል ተወካይ የሲውዲን ዜጋ ላይ የዘረፋ ወንጀል ፈጽመው በክትትል ከተያዙት ሌላ ለጊዜው ሀይሌ ግዛው የተባለ የቀድሞ አየር ወለድ ባልደረባና አስናቀ ተስፋዬ ከሚባለው ተባባሪው ጋር የተሰወሩ መሆናቸውን የክልል 11 ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
በሲውዲናዊው ዜጋ ላይ በተፈጸመው ዘረፋ ከተካፈሉት መካከል የተወሰኑት ከዘረፏቸው ንብረቶች ጋር በፖሊስ ክትትል የተያዙ መሆኑን ኮሚሽኑ አስታውቋል።
( አዲስ ዘመን ሰኔ 13 ቀን 1986 ዓ.ም)
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ሰኔ 13/2015