የተጠራንበት ሰዓት እየደረሰ ቢሆንም እስካሁን አልጨረሰችም። ፀጉሯን ስትሰራ፣ ስትለባብስ ከዚያም ስትኳኳል ሰዓቱ ነጉዶ የሙሽሮች መምጫ ደርሷል። መርፈዱን ላሳውቃት ከበር ቆሜ «ኧረ ውጪ» ማለት ከጀመርኩ ደቂቃዎች ተቆጥረዋል። ልጅት ግን የምትጨርስ አልሆነችም፤ አንዱን ለብሳ ጨረሰች ስል «ይሄስ አላማረብኝም» እያለች ሌላውን ታነሳለች። በዚህኛውም ልቧ አይረካም «… ይህ አይሆንም» በሚል ሌላ ፍለጋ ትጀምራለች። ቆሜ መጠበቁ ስላደከመኝ ከአንድ ጥግ ተቀመጥኩ፤ እየቆየች «ጨርሻለሁ …» ትለኛለች። ጥቂትም ሳትቆይ መልሳ «አላማረብኝም» ትላለች፤ በእኔ ዓይን ግን ሁሉም የሚያምርባት ቅንብብ ያለች ቆንጆ ናት። እርሷ ውስጥ ልጅነቴን እመለከታለሁ፣ ለዛ እና ወዘናዬን ወደ እርሷ ያጋባሁ ይመስለኛል። ሰዎች «ቁርጥ አንቺን የመሰለች…» ይሉኛል፤ እኔም ከአባቷ ስሙን ብቻ ከመጋራት በቀር፤ ሁለመናዋ የእኔ ወጣትነት እንዳለበት ነው የሚታየኝ። አሁን አንጋፋነቴ ማርፈዴን አስታወሰኝ እንጂ፤ እኔም በእርሷ እድሜ የሚያሳስበኝ ማማሬ ብቻ ነበር።
ቁንጅት ብሎ መታየቱን፣ የሰዎችን ቀልብ መሳቡን፣ ከእኩዮች ጋር የስርቆሽ መተያየቱን፣ መጠቃቀስና መጎነታተሉን፣ መግደርደርና መሽኮርመሙን … ከየትኛውም ጉዳይ በላይ ቦታ የምሰጣቸው ነገሮች ነበሩ። ዕድሜ እያሳሳቀ እንደ ደራሽ ይዞኝ ሳይፈተለክ በፊት፤ ለእኔ የጊዜ ትርጉሙ ከውበት ጋር የተያያዘ ነበር። ከቤት ለመውጣት የሚፈጅብኝ ጊዜም አንድ ሰው ጉዳዩን የሚያጠናቅቅበት ነው። እናቴ ከአንድ ቦታ ይዛኝ ለመሄድ ስታስብ ማርፈዴ ስለማይቀር ቀድማ ታስነሳኝ እንደነበር አስታውሳለሁ። እኔም ደርሶብኛልና የዛሬዋ የልጄ መዘግየት ምክንያቱ አልጠፋኝም፤ ያው በትልልቅ ሰርግ መሃል ትንንሽ ሰርግ አይጠፋም የሚለውን ብሂል ተከትሎ መሆኑ አይቀርም። በየአጋጣሚው እንዲህ መሆኑበእድሜዋ የሚጠበቅ ነው።
ታሪክ ራሱን ይደግማል ይባል የለ፤ እኔም ወደ ትዳር ከመግባቴ በፊት የሆንኩት ትዝ አለኝ። የተዋደደ ሁሉ አብሮ ባይኖር እንኳ ጊዜያዊ ስሜቱ ግን አንዳች ደስታን ይሰጣል። እንዲህ እንደዛሬው እድሜ ቀዝቀዝ ማለት ሲጀምርም ለልባችን ሙቀት መፍጠሩ አይቀሬ ነው። ነገሩ የሆነው እኩያዬ የሆነች አንዲት ዘመዴ መዳሯን ተከትሎ ነው። ሰፈራችን ከሙሽሪት መንደር ብዙም ያልራቀ በመሆኑ፤ ወዲህም ሥራ ለማገዝ፣ ሰርጉን ለማድመቅ፣ ሙሽሪትን እንሶስላ ለመቀባትም፣… መመላለሴ አልቀረም። አመሻሹ ላይም እኛ ሴቶቹ ተሰባስበን «… ሙሽርዬ አይበልሽ ከፋ ሁሉም ያገባል በየወረፋ» እያልን እንጨፍራለን። ከእኛ አንጻር ደግሞ ሰብሰብ ብለው «ሃይሎጋ» ከሚሉት ጎረምሶች አንዱ በዓይን ጎብኘት ሲያደርገኝ ይታወቀኛል። አሁን ከትዝታዬ ማህደር በቀር ወዴት እንዳለ የማላውቀው ወጣት፤ ደማም በመሆኑ ሰርቆ ሲያየኝ ከመከፋት ይልቅ ደስታ ተሰምቶኝም ነበር።
የሙሽሪት ጎረቤት በመሆኑም ሲወጣ እና ሲገባ ቃል ሳናወጣ በዓይን መነጋገሩ እና መጠቃቀሱን ቀጠልን። ታዲያ በሰርጉ ቀን ኃፍረታችን ለቆን ለራሳችን ጥንስስ እንነሳ ይሆናል በሚል ዝግጅቴንየጀመርኩት ከቀናት በፊት ነበር። የምሰራው ሹሩባ፣ የምዋብበት አምባር፣ የምደምቅበት ኩል፣ የምለብሰው ሸማ፣ የምቀባው ሽቶ፣ … ሁሉ ሃሳብ ሆኖብኝ ቆየ። እንዳይደርስ የለም በዕለቱ፤ አሁን ልጄ እንደምታደርገው ሁሉ እናቴን «ጨርሻለሁ…» እያልኩ ሳስጠብቃት ቆይቼ «ያምርብኛል» ባልኩት ራሴን አሰማምሬ ወጣሁ። እናቴ በማርፈዴ እየተቆጣችኝ መንገዳችንን ቀጠልን።
እንደ ዛሬው ድንጋይ ያልተነጠፈበት መንገድ በበልግ ዝናብ መሬቱ የረሰረሰ በመሆኑ ጸዓዳው ልብሴ እንዳይቆሽሽ በጥንቃቄ ነበር የምጓዘው። ግን ምን ዋጋ አለው፤ ከሰርጉ ቤት ለመድረስ ጥቂት ሲቀረን አንድ መኪና፤ መሬቱ ላይ የታቆረውን ውሃ እንደጸበል አጠመቀን። እንዲያ ያለ እንከን የተዘጋጀሁበት ልብስ፣ ያደመቀኝ ጸጉሬ፣ የተኳኳለው ገጼ፣ … ሁሉ በጭቃማው ውሃ ተሸፈነ። ጥፋት አድራሹ መኪናም አለፍ ብሎን ከቆመ በኋላ የሾፌሩ በር ተከፈተ፤ እናቴም ለቁጣ ወገቧን ይዛ አንገቷን ትሰብቅ ጀመር። ለካስ እንዲያ አምሬ እንዲያየኝ ስኳኳልለት የቆየሁት ወጣት፤ ሾፌር ኖሮ ከመኪናው ሲወርድ አንድ ሆነ።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28/2011
ብርሃን ፈይሳ