የቀቤና ብሔረሰብ ባሕሉን፣ቅርሱንና ታሪኩን ጠብቆ የሚያቆይበትና ለማስጎብኘትም ምቹ የሆነ የባሕል ማዕከል ለመገንባት ሲያደርግ የነበረው ጥረት ተሳክቷል፤ ማዕከሉ ግንባታው ተጠናቆ ለምረቃ በቅቷል። ለስኬት ያበቁት ደግሞ በሀገር ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎችና በዓለም ክፍሎች የሚኖሩ የብሔረሰቡ ተወላጆች ሲሆኑ፣ ተወላጆቹን በማስተባበርና ማዕከሉ ተገንብቶ ለምረቃ እንዲበቃ ደግሞ የቀቤና ልማት ማኅበር ትልቁን ድርሻ ተወጥቷል።
የባሕል ማዕከሉ ግንባታ የተከናወነው ከአዲስ አበባ 158 ኪሎ ሜትር ላይ በምትገኘው ወልቂጤ ከተማ መግቢያ ላይ ነው። ማዕከሉ በ2 ሺ472 ነጥብ 75 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ሲሆን፤ በውስጡም የተለያዩ ክፍሎችን አካቶ የያዘ ነው። ከመሬት በላይ ሁለት ወለል፤ ከመሬት በታች አንድ ወለል ያለው ይህ የባሕል ማዕከል እስከ አንድ ሺህ ሰዎችን መያዝ የሚችል የመሰብሰቢያ አዳራሽ፣ 100 ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል የቪ አይ ፒ መቀመጫ (ሰገነት)፣ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ሁለት መለስተኛ አዳራሾች፣ 6 ቢሮዎች፣ ምስልና ድምፅን በአንድ ላይ ለመቅረጽ የሚያስችል ክፍል ወይንም አውዲዮ ቪዡዋል እና የሳውንድ ሲስተም ክፍልም በውስጡ ይዟል። በ58 ካሬ ላይ ያረፈ መስጂድ፣ 4 መድረሳዎች፣ 2 እንግዳ መቀበያ ክፍሎች፣ የብሔረሰቡን ባሕላዊ ቁሳቁሶች ለእይታ ለማቅረብ የሚያስችል ሙዚየም፣ መፀዳጃ ቤቶችን ጨምሮ የትርጉም ቤት እና ሌሎች ክፍሎች ይገኙበታል።
የማዕከል ግንባታውን ለማከናወን የተደረጉ ጥረቶችን በተመለከተ የቀቤና ልማት ማኅበር የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ከማል ሡልጣን እንደገለጹት፤ የቀቤና የልማት ማኅበር በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ያሉ የብሔረሰቡ ተወላጆችን በማስተባበርና ከመንግሥትና ከሌሎችም የልማት ደጋፊዎች ጋር በመሆን የቀቤና ብሔረሰብ ባሕል፣ ታሪክ፣ ቋንቋና ሌሎችም እሴቶችን ጠብቆ ለማቆየትና ለትውልድ ለማሸጋገር በማሰብ የባሕል ማዕከሉን በመገንባት ለማስመረቅ ችሏል።
ማዕከሉ የቀቤና ብሔረሰብ በትናንትናዋ ኢትዮጵያ በሀገርና ሀገረ መንግሥት ግንባታ በቀቤና አባቶች ለተደረገው ትግልና ለትግሉ ትሩፋት ማስታወሻ እና ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የአሁኑ ትውልድ አሻራ መሆኑን በመጥቀስ፣ ከታሪክ ምንነት እና ከወደፊቱ ተስፋ አንጻር በጥልቀት ሲጤን የባሕል ማዕከሉ መመረቅ ለብሔረሰቡ ተወላጆች ከምረቃዎች ሁሉ የተለየ ምስጢራዊ ትርጉም ያለው እንደሆነም ያስረዳሉ።
የአንድ ማኅበረሰብ ሕልውና የሚጠበቀው በሰፈረበት መልክዓ ምድር፣ ባሕሉን፣ ቋንቋውን እና እምነቱን መሠረታዊ ይዞታውን ሳይለቅ በማቆየትና ዘመኑ በደረሰበት ቴክኖሎጂ በማበልጸግ ለትውልድ ማስተላለፍ ሲቻል ነው ያሉት የቦርድ ሊቀመንበሩ፤ በዘመነ ሉዓላዊነት ለትውልድ የሚተላለፈው ባሕል ከሌሎች ባሕሎች ጋር ያለው መስተጋብር እንዳለ ሆኖ የራሱ እሴቶች የሚቀጥሉበት ቋንቋም ሆነ ታሪኩ በሌሎች ተፅዕኖ ስር ሳይወድቅ ትውልድ የሚቀባበልበት ሥርዓት ሲኖር መሆኑንም አንስተዋል።
ይህንን በተረዱት ጥቂቶች ትግል የተጀመረውን የሕዝብ ጥረት በመደገፍ የቀቤና ልማት ማኅበር የወረዳውንና፣ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እንዲሁም በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚገኙ የብሔረሰቡ ምሑራን፣ ተወላጆች እና ሌሎችም የልማቱ ደጋፊዎችን በማስተባበር በባሕል፣ በታሪክ፣ በቋንቋ እንዲሁም በወረዳው ልማትን በማፋጠን የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከመንግሥት ጋር በመሆን የተለያዩ የልማት ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
ከነዚህ የልማት ተግባራት መካከል የቀቤና ባሕል ማዕከል ግንባታ አንዱ ነው ያሉት አቶ ከማል፤ ማዕከሉ የብሔረሰቡን የባሕል፣ የቋንቋ፣ የታሪክ እና የእምነት እሴቶችን በማሰባሰብ በአግባቡ ጠብቆ ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
እንደ አቶ ከማል ማብራሪያ፤ የልማት ማኅበሩ በቀጣይ ጊዜያትም የብሔረሰቡን ባህል፣ ቋንቋ፣ ታሪክ እና እምነት ከማሳደግ በተጨማሪ መንግሥት በማይደርስባቸው የልማት ተግባራት በተለይም በትምህርት፣ በጤና በውሃ፣ በግብርና፣ በአካባቢና ተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ እንዲሁም በራሱ የሚኮራና ለሀገር ጠቃሚ የሆነ ትውልድ ለመፍጠር የተለያዩ ተግባራትን ለማከናወን አቅዶ እየሠራ ይገኛል። በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ የብሔረሰቡ ተወላጆች ለዚህ ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።
የቀቤና ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘይኑ ሻቡዲን በበኩላቸው፤ የቀቤና ባሕል ታሪክ ቋንቋና ቅርስ ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ፣ ሕዝቡንና ደጋፊዎችን በማስተባበር የባሕል ማዕከሉን ማስገንባት መቻሉን ጠቁመዋል። ማዕከሉ ለቀቤና የበኩር ልጅ ነው ያሉት አስተዳዳሪው፤ የበኩር ልጅን ለምረቃ ለማብቃት ሕዝቡ ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፏል ብለዋል።
የበኩር ልጅ ለመውለድ ምጥ የሚያስቸግር መሆኑን ያስታወሱት አስተዳዳሪው፤ የቀቤና ሕዝብም የበኩር ተቋሙን ለማጠናቀቅ ብዙ ውጣ ውረዶችን ማሳለፉን ጠቁመው፤ ከዚህ በኋላ ሌሎች ተቋማትን ለመገንባት የሚያስችል አቅም መገንባቱን ጠቁመዋል። የሕዝቡን የመፈጸም እና የማስፈጸም አቅም ያሳየበት መሆኑንም አንስተዋል።
እንደ አቶ ዘይኑ ማብራሪያ፤ የማዕከሉ ፋይዳው ከፍ ያለ ነው። የባሕል ማዕከሉ የቀቤና ሕዝብ ቅርሶች የሚደራጅበት፣ የቀቤንሲና ቋንቋ ማበልጸጊያ እና በቋንቋው ዙሪያ ጥናትና ምርምር የሚደረግበት፣ እና መድረሳ ጨምሮ የያዘ ነው። በተጨማሪም የቀቤና ሽማግሌዎች (የኦገት) አባቶች የሕዝባቸውን ጉዳይ በቢሮ ውስጥ ተመካክረው እንዲፈቱ ምቹ ሁኔታ የፈጠረ ማዕከል ነው። ትላልቅ ሀገራዊ መድረኮችን ለማስተናገድ የሚችል ሀገራዊ፣ ክልላዊ እና ዞናዊ እንዲሁም መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት የሚያዘጋጁዋቸውን መድረኮች ለማስተናገድ ብቁ የሆኑ አዳራሾችን የያዘ ነው። በመሆኑም የባሕል ማዕከሉ የብሔረሰቡ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ፕሮጀክት ነው።
ማዕከሉ መንገድ ዳር እንደመሆኑ ከፈጣሪያቸው ለመገናኘት የሚፈልጉ እስልምና እምነት ተከታዮች እንዲጸልዩ የሚያስችል መስጂድ ጭምር እንዲኖረው መደረጉን ጠቁመዋል።
የጉራጌ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በበኩላቸው፤ የባሕል ማዕከሉ ለጉራጌ ዞን ብቻ ሳይሆን ለደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ሞዴል የሚሆን ነው ብለው፤ የባሕል ማዕከሉ ለዞኑ እና ለወልቂጤ ከተማ ተጨማሪ ውበት የሆነ ነው። ማዕከሉ በሕዝብ ትብብር ተዓምር መሥራት እንደሚቻል ያሳየ ነው በማለት የማዕከሉን ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎች ጠቁመዋል።
እንደ አቶ ላጫ ማብራሪያ፤ የባሕል ማዕከሉ ተገንብቶ መጠናቀቁ አከባቢውን የኮንፍረንስ ቱሪዝም ማዕከል ያደርጋል። የባሕል ማዕከሉ ገንብቶ ለማጠናቀቅ በርካታ ዓመታት ያስቆጠረ ቢሆንም እንኳ በኅብረተሰቡ ተሳትፎ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ጀምሮ ማጠናቀቅ እንደሚቻል ማሳያ ነው።
ባሕል የአንድ ሕዝብ ማንነት መገለጫ በመሆኑ ለዚህ ትኩረት ሰጥተው በመሥራት እውን ላደረጉ አካላት ክብር ይገባቸዋል ያሉት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ፤ የባሕል ማዕከሉ ግንባታ ቢጠናቀቅም ተጨማሪ ሥራዎች ያስፈልጉታል ብለዋል። በቀጣይነትም የባሕል ማዕከሉ የጥናትና ምርምር፣ የኮንፈረንስ ማዕከል እንዲሁም የመዝናኛ ማዕከል እንዲሆን የማዕከሉን ግቢ ውስጥ የማስዋብ ቀሪ ሥራዎችን በመሥራት ሁሉም ርብርብ ሊያደርግ እንደሚገባ ገልጸዋል።
በባሕል ማዕከሉ ምረቃ መርሐ ግብር ላይ የተገኙት የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋጤ ሰርሞሎ እንደተናገሩት፤ የቀቤና ብሔረሰብ ሕገ መንግሥቱና የፌዴራል ሥርዓቱ ካጎናጸፋቸው መብቶች ተጠቃሚ በመሆን ባሕሉን ቋንቋውን እና ታሪኩን ጠብቆ በማሳደግ ረገድ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል። ለዚህም የቀቤና ብሔረሰብ የባሕል ማዕከል አንዱ ማሳያ ነው።
ኢትዮጵያ በዩኔስኮ የተመዘገቡ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ባለቤት መሆኑዋን የጠቆሙት አፈ ጉባኤዋ፤ የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የኢኮኖሚያዊ፣ የማኅበራዊና የአስተዳደራዊ ሥነ ምግባር፣ የሥነ ልቦና ሁኔታዎች፣ የሥነ ቃልና ቋንቋ፣ የምግብ አዘገጃጀት፣ አመጋገብ፣ የቤት አሠራር፣ የአልባሳት፣ ጌጣ ጌጥና ሌሎች እሴቶች የባሕል አካል መሆናቸውን ጠቁመዋል። እነዚህን የባሕል እሴቶችን ጠብቆ ለማቆየት፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማሸጋገር፣ ለማስተዋወቅ፣ የሥራ እድል ለመፍጠር ባሕል ማዕከሎች ሚናቸው የጎላ ነው ያሉት አፈ ጉባኤዋ፤ ከዚህ ባሻገር በዚህ ዘርፍ የሚመራመሩ ተመራማሪዎች እና ለጸሐፊዎች እንደ ቋሚ የመረጃ ማዕከል ሆኖ የሚያገለግል ነው። በተጨማሪም የባሕል ማዕከሎች ሥራ እድል በመፍጠር ፤ በአግባቡ ከተያዙ ደግሞ የቱሪስት መዳረሻ የመሆን እድላቸው ሰፊ ነው።
የቀቤና ባሕል ማዕከል ከኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኝ በመሆኑ በአካባቢው ከሚገኙ ሌሎች የቱሪስት መስሕቦች ጋር ተዳምሮ የቱሪስት ቀልብ ለመሳብ እንደሚረዳ ገልጸዋል፤ ባሕል ማዕከሉ መገንባቱ የቀቤና ብሔረሰብ ሕገ መንግሥቱ ያጎናጸፈውን ባሕልን ታሪክን የመጠበቅ፣ የመንከባከብ እና ለቀጣይ ትውልድ የማስተላለፍ መብቱን እንዲጠቀም ይረዳል ብለዋል።
የወረዳው ሕዝብ ለባሕሉ ካለው መልካም አስተሳሰብና ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ ካለው ጽኑ ፍላጎት ሀገር ውስጥ እና በውጭ የሚኖሩ የብሔሩ ተወላጆች የሕዝቡን አቅም በልማት በማኅበሩ አማካኝነት በማስተባበር ያስመዘገቡት ስኬት የሚደነቅ መሆኑን አንስተው፤ የቀቤና ሕዝብ በልማት ማኅበሩ አማካኝነት ያስገነባው ማዕከሉ ለሌሎች በአርዓያነት የሚጠቀስ ነው ሲሉ አብራርተዋል።
በባሕል ማዕከሉ ምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ሀገራት የመጡ የብሔረሰቡ ተወላጆች፣ የፌደራል፣ የክልልና የዞን ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ ከአጎራባች ዞኖች የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የብሔረሰቡ ተወላጆችና ሌሎችም ተገኝተዋል። የባሕል ማዕከሉ ተገንብቶ ለምረቃ በመብቃቱ ደስተኛ መሆናቸውን የብሔረሰቡ ተወላጆች ተናግረዋል።
ከብሔረሰቡ ተወላጆች መካከል ሐጂ አባድር አክመል እንዳሉት የማዕከሉ ግንባታ እጅግ ዘግይቶም ቢሆን ተጠናቆ በማየታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ጠቁመዋል። የማዕከሉ ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኖ ማየታቸው እንደ ዳግም የመወለድን ያህል ያስደስታል ያሉት ሐጂ አባድር የማዕከሉ ፋይዳም ዘርፈ ብዙ ነው ብለዋል። በተለይም የሕዝቡን አንድነት በማጠናከር ረገድ ከፍ ያለ ፋይዳ እንደሚኖረው ጠቁመዋል።
በምረቃ ሥርዓቱ ላይ ከተገኙት እንግዶች መካከል ከሀዲያ ዞን አርቲስት ካሳሁን ለማ እና ከጉራጌ ዞን ማረቆ ወረዳ አርቲስት ነጋሳ ሲጃ ማዕከሉ ለምረቃ በመብቃቱ ደስተኛ መሆናቸውን ጠቁመዋል። ማዕከሉ ለቀቤና ወረዳ ብቻ ሳይሆን ለአጎራባች ሕዝቦች ያለው ፋይዳ ከፍ ያለ መሆኑን አንስተዋል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ሰኔ 4 ቀን 2015 ዓ.ም