ልጆች እንዴት ናችሁ? ትምህርት ጥሩ ነው? ትምህርት ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ነገን ጥሩ ለማድረግ ያስፈልጋልና በርትታችሁ እየተማራችሁ እንደሆነ አልጠራጠርም። ታዲያ መማር ብቻ ሳይሆን ጎበዝ ተማሪ ሆኖ ጥሩ ውጤት ማምጣትም ይኖርባችኋል። ሀገራችንንም ከዘመኑ ጋር እኩል እንድትሄድና በቴክኖሎጂ ካደጉ ሀገራት ተርታ እንድትሆን ለማድረግ ጠንክሮ መማር ያስፈልጋል።
በዓለም ላይ በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚውና በማህበራዊው ሕይወት እንዲሁም በሁሉም ዘርፍ አንዳንድ አገራት ኃያላን የሆኑት ጠንክረው በተማሩና ውጤታማ በሆኑ ዜጎቻቸው ነው። ኢትዮጵያ ሀገራችንም ነገ ተረካቢዋ እናንተ ናችሁና ከእናንተ ከተማሪዎች ብዙ ትጠብቃለች። ስለዚህ ነው ጠንክራችሁ መማር የሚያስፈልጋችሁ።
እስቲ ለዛሬ አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ? የአርበኞች የድል በዓልን ታከብራላችሁ? ወይም በየዓመቱ ሚያዝያ 27 ሲደርስ ምን ትዝ ይላችኋል? መቼም ምንም ትዝ አይለንም አትሉኝም አይደል ልጆች? አዎን! ሚያዝያ 27 በየዓመቱ የድል በዓል ይከበራል፤ የአርበኞች የድል በዓልና ቀንም ይባላል። ዘንድሮ ለስንተኛ ጊዜ እንደሚከበርስ ታውቃላችሁ እንዴ?
የድል በዓል ዘንድሮ ለ78ኛ ጊዜ ነው የሚከበረው ካላችሁ በትክክል አውቃችኋል። 1933ዓ.ም ሚያዝያ 27 ቀን ማለትም በዛሬዋ እለት ታላቅ የሆነ ድል የተቀዳጀንበት ቀን ነው። በየዓመቱ ከምናከብራቸው በዓላቶች አንዱ ነው። ታዲያ ይህን ድል ለማግኘት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ህፃናትም ሳይቀሩ የራሳቸውን ሥራ ሰርተው አልፈዋል። ድሉም ብዙ ዋጋ የተከፈለበት የሁላችንም ኢትዮጵያዊ ድል ነው።
ዘንድሮ የሚከበረው የኢትዮጵያ አርበኞች የድል በዓል የሚከበረው ከትምህርት ቀን ውጭ ሚያዝያ 27 እሁድ ስለሆነ መልካም አጋጣሚ ነው። እናንተም የእረፍት ቀናችሁ ስለሆነ ከጓደኞቻችሁ አልያም ከቤተሰቦቻችሁ ጋር በዓሉ ከሚከበርበት ቦታ አትጠፉም አይደል?
እስኪ የኢትዮጵያ የአርበኞች የድል በዓልን አስመልክቶ ያነጋገርኳቸውን ልጆች ላስተዋውቃችሁ በዛውም ከነገሩኝ ታሪክ ላካፍላችሁ። እነዚህ ታሪካቸውንም በደንብ ጠንቅቀው ያውቃሉ። እናንተም የእነርሱን ፈለግ በመከተልና በማንበብ ልክ እንደእነርሱ ስለ አርበኞች የድል በዓል ግንዛቤ ለመያዝ እንደምትሞክሩ አልጠራጠርም፡፡
ሚያዝያ 27 ስለሚከበረው የድል በዓል ቀድሜ ያነጋገርኩት ተማሪ ዘውዱ አዳሙ ይባላል። ዘውዱ የአራተኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን፣ የሚማረው ደግሞ በምኒልክ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው። በጣም ጎበዝ ተማሪ ነው፤ ታሪክም ስለሚያነብ ስለ ሀገራችን ታሪክ ጠንቅቆ ያውቃል። ትምህርት ሊዘጋ የዓመቱ መጨረሻ ላይ ስለሆን ለፈተና እየተዘጋጀ መሆኑን ነግሮኛል። ጥሩ ውጤት ለማምጣት ቀድሞ እያነበበ ነው። ፈተና ከመድረሱ በፊት የከበደውንም ከጓደኞቹ ጋር በመሆን እየተጠያየቀ ያነባል።
የኢትዮጵያ አርበኞች የድል በዓልን በተመለከተ ብዙ ሀሳቦችን አካፍሎኛል። የኢትዮጵያ የአርበኞች በዓል በየዓመቱ ሚያዝያ 27 የሚከበር መሆኑንና የሚከበርበት ምክንያትም ጣሊያን ዓድዋ ላይ ከተሸነፈ ከአርባ ዓመታት በኋላ ዳግም ዘመናዊ መሣሪያ ታጥቆና ብዙ ሺ ወታደር በማዘጋጀት ሀገራችንን በቀኝ ግዛት ስር ለማንበርከክ የመጣበት ጊዜ ነበር።
ታዲያ እናቶቻችን እና አባቶቻችን አሻፈረኝ በማለት በዱር በገደል ባላቸው መሣሪያ ሁሉ እየተዋጉ፤ እይፎከሩና እየሸለሉ ለአምስት ዓመት በመላው ሀገሪቱ ታግለው ድል ያደረጉበትን ቀን የምናስብበት የድል ቀናችን ነው። የዚህ ኢትዮጵያ አርበኞች መታሰቢያ ሐውልትም በአራት ኪሎ ይገኛል።
ተማሪ ዘውዱ «ይሄ የድል ቀን ቀላል እንዳይመስላችህ! ቀደምት ኢትዮጵያውያን ለአምስት ዓመታ በጫካ ብርዱንና ሙቀቱን ተቋቁመው ያገኙት ድል ነው» ብሎናል።
ይህን ድል ለማግኘት ብዙ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። ብዙዎች ቤታቸውና ንብረታቸውን ተቀምተውና ተቃጥሎባቸው ተሰደዋል። ነገር ግን እናትና አባት አርበኞች በትልቅ ወኔ ድል አድርገው የወራሪ ወታደርን ከሀገር ማስወጣት የቻሉበት ድል ነው።
ተማሪ ዘውዱ አዳሙ የኢትዮጵያ አርበኞች ድል ለማወቅ ብዙ ጥረት ያደርጋል። በትምህርት ቤታቸው የታሪክ መጻሕፍትን ያነባል። ከትምህርት ቤት ውጭ ደግሞ በሰፈር ወላጅ አባቱንና እናቱን፣ ታላላቆቹን ይጠይቃል። እንዲሁም በዓሉ በሚከበርበት እለት ደግሞ ከቤተሰቦቹ ጋር በመሆን በስፍራው በመገኘት ስለ ኢትዮጵያ የድል በዓል ጥሩ እውቀትን እንደሚጨብጥ ይናገራል። ታሪካችንን ጠንቅቀን የምናውቅ ከሆነ ጥሩ ሀገር ወዳድ ዜጋ እንሆናለንም ብሏል።
ከዘውዱ ቀጥሎ የኢትዮጵያ የአርበኞች የድል በዓልን አስመልክቶ ሀሳቡን ያካፈለን
ተማሪ እንዳለ ተረፈ ነው። እንዳለ ከዘውዱ ጋር በምኒልክ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የአራተኛ ክፍል ተማሪ ነው። እንዳለና ዘውዱ በአንድ ክፍል የሚማሩ ጥሩ ጓደኛሞች ናቸው። ወደፊትም አብረው በማንበብና በማጥናት ጥሩ ጓደኛ ሆነው እንደሚቀጥሉ ነግረውኛል።
እንዳለ እንደሚለው ደግሞ፤ የኢትዮጵያ አርበኞች ድል የሁላችንም የመላው የኢትዮጵያውያን ሕዝብ ድልና ብሔራዊ ኩራቻችን ነው። ይህ ትልቅ የኢትዮጵያ የአርበኞች ድል በዓል በሁሉም ሀገር በድምቀት መከበር እንዳለበትም ያምናል። በሌሎች ሀገር የነፃነት ቀናቸውን በድምቀት እንደሚያከብሩት ሁሉ እኛም ድላችንን በኩራት ልናከብረው ይገባል።
እንዲያውም ሁሉም ተማሪ በሰልፍ ወጥቶ በዓሉ ቢከበር ደስ እንደሚለውና ሚያዝያ 27 ሲደርስ በየዓመቱ አራት ኪሎ ወደሚገኘው የአርበኞች መታሰቢያ ሐውልት በመሄድ ማክበር ከጀመረ ሦስት ዓመት እንዳለፈ ነግሮኛል። ታዲያ ብቻውን መሰላችሁ የሚሄደው!? አይደለም፤ ጓደኞቹንም ይዞ በመሄድ በቦታው ያለውን ድባቡ በመመልከት እንደሚደሰቱ ገልጾልኛል።
እንዳለ ሲናገር «አርበኞቻችን እኛ በነፃነት እንድንኖር ሲሉ ተዋግተዋል። ሀገራችንን በነፃነት አቆይተውልናል። በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በዘር፣ በቀለምና በጎሳ ሳይለያዩ በጋር በብሔራዊ ስሜት በመነሳሳት ተዋግተው የውጭ ወራሪን ድል ማድረግ ችለዋል።»።እኛም አለ ተማሪ እንዳለ እንደ አያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን አገር ወዳድ በመሆን ለሀገራችን ውለታ ልንውልላት ይገባል ብሏል። ሁሉም በያለበትና በአቅሙ ድሉን በማክበር ጀግኖች እናቶችና አባቶቻችንን ሊያስታውስ ይገባል ብሏል።
እንዳለ ስለ ኢትዮጵያ አርበኞች ድል ብዙ መስማት ያስደስተዋል። ስለ ድሉ የሚያወሱ መጽሐፍትን ማንበብ ይወዳል። በንግግሩም ሁሉም ሰው ስለ ድል በዓል ማወቅ አለበት፤ ድሉን የማያውቁ ሰዎች ደግሞ ማንበብ አለባቸው ብሏል። መንግሥትም በዓሉ ሲደርስ ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ጊዜ በተለያየ መልኩ ሕብረተሰቡን ማስተማር አለበት ሲል ለታሪኩ ያለውን ተቆርቋሪነት ያሳያል።
አባቶቻችን ድል ባያደርጉ ኖሮ አሁን ያለንን ማንነት አንያዝም ነበር። እርሱ የአርበኞችን የመታሰቢያ ሀውልት በሚያይበት ጊዜ የኩራት መንፈስ ይሰማዋል። የአርበኞች ድል በዓል ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ታሪካችንን መጠበቅና ማቆየት አለብን የሚለው እንዳለ፤ አንድ በመሆን የአርበኞች በዓል ስናስብ ቀድሞ ትዝ የሚለን ቅኝ ግዛት ሳንገዛ ተዋግተን ድል ያደረግን ብቸኛ ጥቁር አፍሪካዊ መሆናችን ነው ይላል።
ልጆች! የዘውዱና የእንዳለ ሀሳብ በጣም ደስ የሚል ነው አይደለ? ሁለቱም ሀገራቸውን በጣም ይወዳሉ። ለታሪካቸውም ከፍተኛ የሆነ ፍቅርና አክብሮት አላቸው። የድል በዓሉ ሲከበር በቦታው በመሄድ ይታደማሉ። የሀገራቸው ታሪክም ስለሚያነቡ ጠንቅቀው ያውቃሉ። እናንተም እንደ እነርሱ መሆን አለባችሁ። እንዲሁም የሀገራችሁን ባህል ጠንቅቃችሁ እንድታውቁ የታሪክ መጻሕፍትን ማንበብ በእድሜ ከእናንተ የሚበልጡ፣ መምህሮቻችሁን መጠየቅ አለባችሁ።
ለእናንተም ብቻ ሳይሆን ጓደኞቻችሁ እንዲያነቡና ታሪካቸውን ጠንቅቀው እንዲያውቁ በጋራ በመሆን አንብቡ። ነገ ከእናንተ ብዙ ቁም ነገር ስለሚጠበቅ መበርታትና እራሳችሁን ለትልቅ ቁም ነገር ካሁኑ ማዘጋጀት ይኖርባችኋል። ታዲያ እራስን ለትልቅ ቁም ነገር ማዘጋጀት የሚጀምረው የሀገርን ታሪክ ከማወቅ ብሎም የቀደሙ እናቶችና አባቶቻችንን ሥራ በማክበርና እንደመማሪያ በመጠቀም ጭምር ነው። መልካም በዓል!
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 27 ቀን 2011 ዓ.ም
ሞገስ ፀጋዬ