
አዲስ አበባ፡- በመማር ማስተማር ሂደቱ በሥነምግባር የታነፁ ተማሪዎችን ለማፍራት ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የተዘጋጀ ስምንተኛ ከተማ አቀፍ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራ ጥናትና ምርምር ጉባዔ ተካሂዷል።
በጉባዔው መክፈቻ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ እንደገለጹት፤ በሥነምግባር የጎለበተና ሃሳብን በሃሳብ የሚሞግት ትውልድ በመፍጠር ረገድም መምህሩ ተማሪው፣ ወላጅ የትምህርት አመራሩና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ይበልጥ መስራት አለባቸው።
በሥነ-ምግባር የያነጸ ትውልድ ለአገርም ለእራሱም የሚጠቅም ስራ ማከናወን ይችላል ያሉት አቶ ዘላለም፤ አስፈላጊውን ቁጥጥርና ክትትል በማድረግ የተማሪዎች ሥነምግባር እንዲሻሻል መስራት የሁሉም ዜጋ ሃላፊነት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ትውልዱ በዕውቀቱና በክህሎቱ የዳበረ እነዲሆን የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የተናገሩት ኃላፊው፤ ተማሪዎች የመማር ማስተማር ሂደቱን በማያውክ ሁኔታ ትምህርታቸውን ተከታትለው ለማጠናቀቅ የሚያስችል ዝግጁነት ሊኖራቸው እንደሚገባ ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶስተኛ ዲግሪ የታሪክ ተማሪው ዮሀንስ ተስፋዬ ባቀረቡት የጥናት ጽሁፍ፤ ተማሪ ተኮር የማስተማር ሥነ ዘዴን መከተል ተማሪዎች ሃሳባቸውን በነጻነት እንዲያቀርቡ ከማስቻሉም ባሻገር ምክንያታዊ የሆነ የውይይት ባህልን እንዲያዳብሩ እንደሚረዳ አመላክተዋል።
ወላጆች ለተማሪዎች አነስተኛ ክትትል ማድረጋቸው፣ ትምህርት ቤቱ ያወጣውን ሕግ በመተግበር ረገድ ክፍተት መኖሩ፣ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የተማሪዎች መተዳደሪያ ደንብ ከወቅቱ ጋር የተገናዘበ አለመሆኑ፣ ተማሪዎች ኩረጃ ላይ ማተኮራቸው የተማሪዎችን የሥነምግባር ሁኔታውን እንዳበላሸው ጠቁመዋል።
ለመፍትሄው የተማሪዎችን ሥነምግባር ለማሻሻል የትምህርት አመራሩ ቅጣት ላይ ብቻ አለማተኮር፣ መምህራንና ወላጆች ከተማሪዎች ጋር በበቂ ሁኔታ መወያየትና የትምህርት ቤት ግብዓቶችን ማሻሻል፣ እንደሚገባቸው አስረድተዋል።
በመድረኩ የተማሪዎችን ሥነምግባር ለማሻሻል የሚረዱ ምክረሃሳቦች የቀረቡ ሲሆን፤ ተማሪዎችም ለትምህርት ቤታቸው ሕግና ደንብ ተገዢ እንዲሆኑ ይበልጥ መስራት እንደሚገባ ተገልጿል።
በኃይሉ አበራ
አዲስ ዘመን ሰኔ 3/2015