ምርጫ በየአምስት ዓመቱ ብቻ የሚመጣ አይደለም። ይልቁንም ለአፍታ እንኳን የማይለየን (ምናልባትም እኛ የማናስተውለው) የምንደምቅበት አሊያም የምንደበዝዝበት ዕጣችን ነው። በግፊቶችና እኛ በምንሰጣቸው ምላሾች መካከል ምን ጊዜም ቢሆን የመምረጥ እድል አለ። ነገር ግን ብዙዎቻችን በንዴት ጦፈን የምንሰጠውን መልስ የመምረጥ ዕድላችንን ለሚጋልበን ስሜት አሳልፈን እንሰጠዋለን። ይህም ለጉዳት ይዳርገናል። ታዲያ የምንጎዳው በደረሰብን ነገር ሳይሆን ለደረሰብን ነገር በምንሰጠው ምላሽ ነው።
ማንም የዘራውን ያጭዳል እንዲሉ ወደድንም ጠላንም የምርጫችንን ውጤት እናጣጥማለን። በምናደርገው ምርጫ በረከትን አሊያም መርገምትን እንጠራለን። ከአንድነት ይልቅ መለያየትን ከመረጥን መበታተን እጣችን ይሆናል። ከፍቅር ይልቅ ጥላቻን ከመረጥን የጭካኔን ፍሬ እንበላለን። ከመደጋገፍ ይልቅ መጠላለፍን ከመረጥን የውድቀትን ጽዋ እንጎነጫለን። እነዚህን መንገዶች መከተል አስተውሎትና ጥበብ አይጠይቅም። መገንባት እንጂ ማፍረስ አይከብድማ ! መልካም ማሰብና መናገር በራሱ ብቻውን በረከት ያመጣል።
ይህችን አባባሌን ግልጽ የምታደርግ ተረት እነሆ። አንድ ሞልቶ የተትረፈረፈለት ባለጸጋ ሰውና በቀን አንድ ጊዜ እንኳን ለመብላት የሚቸገር ድሃ በአንድ አካባቢ ይኖሩ ነበር። ታዲያ ሁለቱም መልከ መልካም ሚስቶች ነበሯቸው። የድሃው ሚስት እጅግ የተዋበ፣ ሞንዳላ ሰውነት ያላት፣ ወዟ የሚቀዳ ደመ ሙሉ ነበረች። የባለጸጋው ሚስት ግን ከስታና ገርጥታ ፃዕረ ሞት ትመስል ነበር። ባለጸጋው የድሃውን ሚስት እየተመለከተ ሲብሰለሰል ቆይቶ አንድ ዕለት “ምን እያበላሃት ነው እንዲህ ያማረባት” ሲል ይጠይቀዋል።
ድሃውም “የምላስ ስጋ” ሲል ይመልሳል። በዚህ ጊዜ ባለጸጋው “አሃ ለካ ሚስጥሩ ይህ ኖሯል” ይልና ሚስቱ በቋሚነት የምላስ ስጋ እንድትመገብ ያደርጋል። ነገር ግን ምንም አይነት ለውጥ ሳያይባት ይቀራል። በዚህ ጊዜ ይናደድና የድሃውን ሚስት ቀምቶት የሱን ከሲታ ሚስት ይልክለታል። የድሃው ሚስት ባለጸጋው ቤት ከገባች ጊዜ አንስቶ ሰውነቷ እየሸሻት እየከሳችና እየገረጣች ትሄዳለች።
የቀድሞዋ የባለጸጋው ሚስት ደግሞ እያማረባት ሰውነቷ እየሞላና ደም ግባቷ እያበራ ይሄዳል። በዚህ ጊዜ ባለጸጋው እንደገና ወደ ድሃው ይሄድና “ምን ጉድ ነው? ከዚህ ቀደም ምን እያበላሃት ነው ብዬ ብጠይቅህ የምላስ ስጋ ብለህ ሸመጠጥከኝ አሁን ግን እውነቱን እንድትነግረኝ እፈልጋለሁ” ይለዋል። ድሃውም “የምላስ ስጋ ያልኩህ እውነቴን ነው። ነገር ግን ሆድ የሚገባውን አይደለም። በቤታችን እንኳን ስጋ ልንበላ ጥራጥሬም በየቀኑ አናገኝም። የምላስ ስጋ የምመግባት በየቀኑ እያጫወትኳት፤ በቀልድ እያፍለቀለቅኳትና ጊዜዬን ሰጥቻት እያስደስትኳት ነው” አለው።
ሰላምና ፍቅር ከቁሳዊ ፍላጎቶች በላይ ለሰው ልጅ አእምሮ እርካታን፣ ለልብ ሀሴትን ይሰጣሉ። ደግ ደጉን በማሰብ፣ በመናገርና በማድረግ በረከታችንን መቁጠር ስንችል በጥላቻ ሰክረን የምንወላገድበት ምክንያት አይገባኝም።
ደራሲና ጋዜጠኛ ማሞ ውድነህ በአንድ ወቅት ስለፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም አንድ ገጠመኝ የተናገሩት ትዝ ይለኛል። በአፄ ኃይለ ስላሴ ዘመን ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ በድርቅ በመመታቷ በወቅቱ የነበረው ቲዎክራሲ ፓርላማ ምክንያቱ እንዲጠና ይጠይቃል።
በርከት ያሉ አባላት ያሉት ግብረ ኃይል ይቋቋምና ፕሮፌሰር መስፍን እየመሩት ወደስራ ይገባል። ከዛም ሁለት ዓመታት ከፈጀ ምርምር በኋላ ፕሮፌሰሩ የጥናቱን ውጤት ይዘው ፓርላማ ይቀርባሉ። “ዝናብ እንዲዘንብ የሚያደርጉት ተክሎች ናቸው እኛ ግን ተክሎችን እየጨፈጨፍን ብለው ንግግራቸውን ገና ከመጀመራቸው አንድ የምክር ቤት አባል በዚህ ዘመን አካሄድ እንደሚባለው በዚያ ዘመን ቋንቋ “ስለ ደንቡ … ስለ ደንቡ “ ብሎ ያቋርጣቸዋል።
የመናገር ዕድሉን ሲያገኝም “ዝናብ እንዲዘንብ የሚያደርገው ፈጣሪ ነው። ይህ ሰው ግን ተክሎች ናቸው እያለ ነው፤ መናፍቅ ስለሆነ ከፓርላማው ይባረርልኝ” አለ። የተቀሩት የፓርላማው አባላትም ፕሮፌሰሩ ይባረሩ በማለታቸው ሁለት ዓመት የፈጀው ጥናት ሁለት ደቂቃ እንኳን ሳይቀርብ ፕሮፌሰሩ ፓርላማውን ለቅቀው ወጡ። ይህ ጥናት ቀርቦ ተቀባይነት ቢያገኝ ምናልባትም ዛሬ ያለው ትውልድ የተራቆተ ሳይሆን በደን የተሸፈነ መሬት በረከቱ ይሆን ነበር። ያ ባለመሆኑ የወቅቱን ባለጊዜዎች ምርጫ ውጤት ማጣጣም ግድ ሆኗል።
የትላንት ምርጫዎቻችን ዛሬን የበረከት አሊያም የመርገምት ዘመን ያደርጉታል። ለምሳሌ በያዝነው ሳምንት የተከበረው የወዛደሮች ቀን በብዙ የዓለማችን አገራት የሚገኙ ሰራተኞች የሚፈጸምባቸውን ጉልበት ብዝበዛ በመቃወምና ምቹ የስራ አካባቢ እንዲፈጠርላቸው በመጠየቅ የተቃውሞ ሰልፍ በማድረግ አክብረውታል። ትላንት የነበሩ ሰዎቻቸው በብዙ የዓለም አገራት ዛሬ የሚነሳውን ጥያቄ የመለሱላቸው ጀርመንና ብሪታንያን በመሰሉ አገራት የሚገኙ ሰራተኞች ግን ዕለቱን በውዝዋዜና አዝናኝ በሆኑ የጎዳና ትርኢቶች አክብረውታል።
እኛም ዛሬ የምንመርጠው እያንዳንዱ ነገር ዛሬን፣ በይበልጥ ደግሞ ነገን በበረከት አሊያም በመርገምት መሙላቱ ጥርጥር የለውም። ስለዚህ “አስር ጊዜ ለካ አንድ ጊዜ ቁረጥ” እንዲሉ በግፊቶችና በምንሰጠው ምላሽ መካከል ባለው ቅጽበታዊ ጊዜ በሚገባ ተጠቅመን ምርጫችን ዛሬም ሆነ ነገ በረከት አምጪ እንዲሆን እንትጋ።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 25/2011
በየትናየት ፈሩ