የ«ካርማ» ቀጥተኛ ፍቺ፣ ከቶ የማይዛነፍ፣ የድርጊትና የውጤት ግንኙነት ነው። ድርጊቱ ሰላማዊ ከሆነ ውጤቱም ሰላማዊ፤ ድርጊቱ ጦርነት ከሆነ ውጤቱም ያንኑ ጦርነትና እልቂት ይሆናል ማለት ነው። የእኛን ባህላዊ አገላለፅ መሠረት አድርገን ስንመለከተው ደግሞ «የእጅህን ታገኛለህ» እንደ ማለት ይሆናል። በካርማ እሳቤ ከእባብ የእርግብ እንቁላልን መጠበቅ አይታሰብም።
«ካርማ» የሚለው ቃል እና አስተምህሮቱ በአሁኑ ጊዜ በአብዛኛዎቹ ዘመናዊ ሥነጽሑፋዊ ሥራዎች ውስጥ የሚገኝ ነው። በዓለም ሥነጽሑፍ ሥራዎች ውስጥም ጽንሰ ሀሳቡ ሁነኛ ስፍራን በመያዝ ሁነኛ ሚናውን እየተጫወተ ይገኛል። ለዚህ ማሳያ Law of Karma, How Karma Works?, HOW PEOPLE TREAT YOU IS THEIR KARMA; HOW YOU REACT IS YOURS እና ሌሎች በርካቶችን መጥቀስ ይቻላል።
ቀጥለን የምንጠቅሰው ምንጫችን እንደሚለው ከሆነ «በሥነምህዳራዊ ሁኔታ ‘ካርማ’ ማለት ‘ድርጊት’ ወይም ‘ማድረግ’ ማለት ነው።» በመሆኑም፣ በምዕራ ባውያን ዘንድ ሁሉ ከለመድነው ዘይቤአዊ እና ሃይማኖታዊ ትርጉም ጋር ሁልጊዜ ስሙ በመሆን ጥቅም ላይ እንዲውል አስችሎታል።
ጉዳዩን በአግባቡ በማስተናገድ ተነባቢነትን ያገኘው ድረ-ገፅ (https://am.warbletoncouncil.org/karma) እንደሚለው «በእስያ የተወለደው የካርማ ጽንሰ-ሀሳብ» ብያኔው እንደ ሂንዱይዝም ወይም ቡዲዝም ባሉ የተለያዩ ምሥራቃዊ ሃይማኖቶች እና ፍልስፍናዎች «ሁሉን አቀፍ ኃይል ነው።»
በዚህ ፍልስፍናዊ አተያይ መሠረት አንድ ሰው አንድን ሰው ቢጎዳ በሆነ አጋጣሚ እሱ እራሱም የሆነ፣ የሌላ ሰው ሰለባ ከመሆን አያመልጥም፤ ወይም፣ አይድንም። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ፣ ከላይ እንደጠቀስነው «የእጅህን ታገኛለህ»፤ ወይም ድምፃዊው «የእጄን ነው ያገኘሁት» እንዳለው ይሆናል ማለት ነው።
ምንም እንኳን በጥንታውያን (1000–700 bce) የሕንድ ጽሑፋዊ ሰነዶች ውስጥ እንደ አንድ መስዋእት የሚደረግለት ባህላዊ የእምነት ተግባር ተደርጎ ይታይ የነበረ ቢሆንም፣ የራሱና ጥብቅ የሆነ መርህ (principle/Theory/Law of karma) ያሉት ካርማ፣ በተለይ በሕንድ ምድር ሚናው የማይተካ፣ ወሰኑ ከዚህ በመለስ የማይባል፤ በተግባር የሚገለፅ፤ በእነሱ ማንነት መገለጫ በሆነው ሳንስክሪት (Sanskrit) ቋንቋ በሚገባ የተብራራ፤ መርሁም ሳቢያና ውጤት (cause and effect)ን መሠረት ያደረገ ጽንሰ-ሀሳብ ነው። «መልካም አስተሳሰብና መልካም ተግባር ለመልካም ካርማ» የሚል እሳቤን በሚያራምዱ ወገኖች ዘንድ ሳቢያ (መንስኤ) እና ውጤት (ሁለቱ) የማይነጣጠሉ፣ ጫፋቸው (መነሻቸው) ተለይቶ የማይታወቅ፣ (ኡደት ያላቸው) በኡደት የሚንቀሳቀሱ (karmic cycle) ጉዳዮች ናቸው።
በዚህ ሁኔታ፣ ጽንሰ-ሀሳቡን ወደ አገራችን እናምጣው ካልን «የአፈፎ ልጅ ጠለፎ» (የሌባ ልጅ ከአባቱ በእጥፍ ሌባ የመሆን ዕድሉን የሚነግረን)፤ «ይወለድና ጫማው ሰፋፊ / ሆኖ ይቀራል ጎመን ቀራፊ» (ዘፈን)፤ «ሥራው ያውጣው»፣ «የሥራህን ይስጥህ» (ርግማንም ቢሆንም)፣ «ይበለኝ / የ’ጄን ነው ያገኘሁት» (ጥበቡ ወርቅዬ) እና ሌሎችንም የምናገኝ ይሆናል።
ከዚህ የምንገነዘበው ካርማን ባናውቀውም፤ እንደ ቡዲዝምም ሆነ ሂንዱዪዝም «ጉዳዬ» ብለን ባንይዘውም እንኳን እየኖርነው ነውና ለካርማ (ከራማ??) አዲስ አይደለንም ማለት ነው። ካስፈለገ «ያባቴ ከራማ ስብርብር ያርግህ» የሚለውንም እዚሁ ላይ ማከል ይቻላል። «የታዬ ከራማ» ሲባል ማለት የተፈለገው ምን እንደሆነም ጠበቅ አድርጎ በመያዝ ስለ ጉዳዩ ለማወቅ መጣር ክፋት የለውም።
ከዚሁ ሳንርቅ ጋሽ ጥላሁን (ስሙ ራሱ ጥላ ሁን)፡-
የጎዳሽ ይጎዳ ብድር ይድረሰው፤
የጠላሽ ይጠላ ተፈጥሮ ትውቀሰው . . .
ማለቱን ስናስታውስ ጋሽ ጥሌ በራሱ መንገድ «ካርማ»ን እየነገረን፤ «የእጁን ይስጠው» እያለን ነበርና አሁንም «የጎዳሽ ይጎዳ . . . የጠላሽ ይጠላ . . . » በማለት ካርማን በዜማ ውስጥ ደግመን እናንጎራጉረዋለን።
ዓይነቶቹ
«ያለፈው . . . አልፏልና / ዳግም ላይመለስ ሆኗልና» የሚለው የጥላሁን ገሠሠ ዜማ የማይመለከተው «ካርማ» ዓይነቶቹ ሦስት (prarabdha፣ sanchita፣ እና kriyamana ወይም agami) መሆናቸውን እዚሁ ጽሑፍ ውስጥ ከጠቀስናቸው ምንጮች ያገኘነው መረጃ ይነግረናል።
ሦስቱም «ካርማ» እንደ መሆናቸው መጠን «አንድ» ይምሰሉ እንጂ፣ ከማንነታቸው ጀምሮ ልዩነት አላቸው። ለምሳሌ ያህልም፡-
Prarabdha karma (ጎልቶ የሚታየው ካርማ ድርጊቱ በሚከናወንበት ጊዜ፤ ለምሳሌ፣ ለአንድ ሰው በሚዋሽበት ጊዜ ነርቮች ንግግሩን ባልተስተካከለ መንገድ ያመጣሉ፤ እናም ነርቮች እና እፍረቱ ይታያል።) is experienced through the present body and is only a part of sanchita karma (በአእምሯችን ውስጥ የቀሩ ትዝታዎች እና የወደፊቱ ድርጊታችን ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ።
ለምሳሌ፣ አንድን ሰው ባለማነጋገር የሚመጣውን ኀዘን እና በሚቀጥለው ጊዜ በፍቅር ስንዋደድ ምን እንደሚሰማን ከመናገር ወደ ኋላ አለማለት።) which is the sum of one’s past karmas, whereas agami karma (በአሁኑ ጊዜ አንድ እርምጃ ወደ ፊት ላይ የሚኖረው ውጤት፤ ለምሳሌ፣ ለብዙ ሳምንታት ከመጠን በላይ መብላት በሚቀጥሉት በርካታ ወራቶች ወደ ጤና ማጣት ይመራዋል።) is the result of current decisions and actions.“ የሚለውን ማሳየት ይቻላል።
«የእርስዎ ካርማ የእራስዎ ተግባር ነው»
በድጋሚ «ካርማ ማለት ምን ማለት ነው?» ነው ተብሎ የተጠየቀ ሰው የእኛን ተረትና ምሳሌ ተጠቅሞ «የዘሩትን ማጨድ» ቢል ትክክል ይሆናል።
«ደባ ራሱን፣
ስለት ዱግሱን።» የሚለውም ያውና ያው ነው።
ዳስ የተባሉ ጸሐፊ ለንባብ እንዳበቁት እያንዳንዱ ሰው ለእሱ ወይም ለድርጊቶቹ እና ለሀሳቦቹ ተጠያቂው እራሱ እንጂ ሌላ ማንም አይደለም። ስለዚህ የእያንዳንዱ ሰው ካርማ በሙሉ የእሱ፣ የራሱ ወይም የእሷ፣ የራሷ ነው። አስመሳይ ክስተቶች የካርማ ተግባርን እንደ ሞት ያዩታል። ነገር ግን ይህ ከእውነታው እጅግ የራቀ ነው። ምክንያቱም አንድ ግለሰብ የራሱን ትምህርት በማስተካከል የወደፊት እሳቤውን ይቀርፃልና።
[. . .] ጥሩ ካርማን ለማግኘት በዱህዕ ወይም ትክክል በሆነው ሕይወት መኖር አስፈላጊ ነው። (am.eferrit.com)
ካርማን በተመለከተ በሕንድ ያለው አተያይ የላይኛው («ሳቢያ» እና «ውጤት» ያልነው)ን መሠረት ያደረገ ሲሆን፤ በምሳሌነትም በኢንሳይክሎፔዲያ ብሪታኒካ ላይ የሰፈረውን፣ የሩፐርት ጋት (Rupert Gethin)ን፣ «የግለሰቡ የዛሬ ፍላጎት፣ ሆን ብሎ የሚያደርገው ሥራና ተግባር የነገው እሱነቱ ላይ የራሱን ተፅእኖ ያሳድራል» የሚለውን አስተያየት መጥቀስ ይቻላል።
ከስረመሠረቱ ሲፈተሽ ካርማ ማለት ተግባር ማለት ሲሆን፣ ለዚህ ማረጋገጫ ይሆነን ዘንድ አብዝቶ ከሚጠቀሰው፣ ከሩፐርት አስተያየት ወሳኝ የሆነውን እንደወረደ እንውሰድና «የእርስዎ ካርማ የእራስዎ ተግባር ነው» የሚለውን እናረጋግጥ ዘንድ እንመልከተው።
እንደ እኝሁ ምሁር አመለካከት ካርማ ማለት፣ እንደ አእምሯዊ ተግባር ወይም መሻት የሚቆጠር ነው፤ የአእምሯዊ ሕይወታችን ገፅታ ነው። አንድ ሰው ከመሥራቱ በፊት ያቅዳል፣ ያስበዋል፤ ከዛም በአካሉ፣ በንግግሩ እና አእምሮው ወደ ተግባር ይቀይረዋል። ተመራማሪው ለካርማ የሰጡት ብያኔና ሰብአዊ ስፍራ ይሄንን ያህል የዘለቀ፣ የጠለቀና የረቀቀ ነው።
«መጥፎ አስተሳሰብና መጥፎ ተግባራት ለመጥፎ ካርማ ይዳርጋሉ» (የጥላሁንን «የጎዳሽ ይጎዳ . . . » ልብ ይሏል) በሚለው አስተሳሰብ አራማጆች ዘንድ በብያኔው ላይ ልዩነት ያለ ሲሆን፣ በከፊሎች ካርማ እና እንደ ገና መወለድ (karma and rebirth) የተለያዩ መሆናቸው ሲታመንበት፤ በከፊሎቹ ዘንድ ደግሞ ሁለቱም አንድ፣ ያውና እኩል መሠረታዊ (ኢሴንሻል) መሆናቸው መታመኑ ነው።
ከእነዚህ በርቀት በሚለዩት ዘንድ ደግሞ በሁለቱ መካከል ምንም ዓይነት ግንኙነት የለም። «ይገናኛሉ» ባዮቹ ለማደናገር ካልሆነ በስተቀር የሚያቀርቡት ምንም ዓይነት መረጃ የላቸውም ባዮች የመኖራቸው ጉዳይ ነው።
ቡድሂስቶች፣ በመዝገበ ቃላት «እያንዳንዳቸው ተከታታይነት ባለው የአኗኗር ሁኔታቸው ውስጥ የሚወሰነው የእሱ ድርጊት ነው» የሚል ብያኔ የተሰጠውን ካርማ ሲበይኑ «ካርማ ማለት በግለሰቡ አእምሯዊ ወይም አካላዊ ተግባር መካከል ያለ ግንኙነትና እሱን ተከትሎ የሚመጣው ውጤት (ኢፌክት) ማለት ነው» ይላሉ።
የቃሉ ስሜታዊ ተፅእኖ በከፍተኛ ደረጃ ጠንካራ የሆነው «ካርማ» ሰጥቶ መቀበል፤ አፀፋውን ማግኘት (action and reaction) ነው – የእኛው ድምፃዊ «የእጄን ነው ያገኘሁት» እንዳለው፤ ሁሉ ማንኛውም ሰው «የእጁን ነው የሚያገኘው»። መልካም ላደረገ መልካም ይደረግለታል። በተቃራኒውም ከሆነ እንደዛው። ባይሆን ኖሮ፣ ከላይ እንዳልነው «የሥራህን ይስጥህ»፤ «የእጅህን አይንሳህ»፤ «በምድር የሰራኸውን በሰማይ ታገኘዋለህ»፤ ድምፃዊቷም «የፍቅር አምላክ የእጅህን ይስጥህ» እንዳለችው እና የመሳሰሉት አባባልና አገላለፆች እንኳን ከትውልድ ትውልድ ሊተላለፉ ቀርቶ ባልተወለዱ ብቻ ሳይሆን ጭራሹን ባልተፀነሱም ነበር።
ምንም እንኳን፣ «ካርማ ለብዙዎች ግራ የሚያጋባ ርዕስ ነው፣ ምክንያቱም ጽንሰ-ሀሳቡ ራሱ ቡዲዝም፣ ሂንዱይዝም፣ ጃይኒዝም፣ ታኦይዝም፣ ሺንቶይዝም እና ሌሎችንም ጨምሮ ከብዙ ወጎች የመነጨ ስለሆነ» የሚሉ ጸሐፍትና ተመራማሪዎች ቢኖሩም፣ ስለ ካርማ ሲነሳ ወይም ሲወሳ «የእርስዎ ካርማ የእራስዎ ተግባር ነው። ውጤቱም እንደዛው።»፤ «መንስኤ እና ውጤት ነው» የሚለው ከእጅ ሊወጣ፣ ሊያመልጥ የሚገባው ሀሳብ አይደለም። እያንዳንዱ ሰው ለእሱ ወይም ለድርጊቶቹ እና ለሀሳቦቹ ተጠያቂ መሆኑም ሆነ ካርማን ለማግኘት ትክክል በሆነው ሕይወት መኖር አስፈላጊ መሆኑን እና የመሳሰሉትን አጥብቆ መያዝ ያስፈልጋል።
ማሪያ ሆዜ ሮልዳን የተባሉና በካርማ ጉዳይ ጠልቀው የሄዱ ተመራማሪ እንዳሰፈሩት «አንድ ሰው መጥፎ ነገር ካደረገ ‘መጥፎ ሰው’ በእሱ ላይ ይሆናል ብሎ ያስባል። ለምሳሌ፣ በትራፊክ ፍሰት ሂደት ውስጥ አንድ ሰው ሌሎች በፍጥነት እንዳይሄዱ ካገደ፣ ካርማ ለእሱ ይመልሰዋል እና ተመሳሳይ ነገር ይከሰታል – ከዚህ በፊት ስላደረገው ለእርሱ»፤ «. . . ምንም እንኳን ይህ በሌሎች፣ የተለያዩ ምክንያቶች እውነት ሊሆን ቢችልም፣ ካርማ በቡዲስት ግንዛቤ ውስጥ እንዴት እንደሚሠራ አይደለም።
ከካርማ ጋር በተያያዘ «ጥሩ» እና «መጥፎ» የሚለውን ሀሳብ ወደ ጎን ትተን በምትኩ እንደ ልምምድ ልንጠቀምበት ብንችል ጥሩ ነው። «ካርማን እንደ ልምምድ ለመጠቀም የመጀመሪያው እርምጃ ለእርስዎ ምን ማለት እንደሆነ መመርመር» እና ምንነቱን በአግባቡ መረዳት ነው። አዎ፣ ይህ ከሁሉም ቀዳሚ መሆን አለበት።
ጸሐፊው ይቀጥላሉ፤
የውሸት ምሳሌን በተሻለ ለመረዳት በመጀመሪያ፣ ሐቀኝነት የጎደለውን አስተሳሰብ የሚንከባከብ አእምሮን ማዳበር ነው። ስትዋሽ ለወደፊቱ መዋሸት ቀላል ሊሆን ይችላል። ለሌላ ሰው ሲዋሹ እርስዎም ግልጽ እና ሐቀኛ ያልሆነ ግንኙነትን እያደረጉ ነው። በመጨረሻም ከራስዎ እና ከህሊናዎ ጋር መተኛት አለብዎት። የጥፋተኝነት ስሜት፣ ጥላቻ ወይም ሌላ ዓይነት ሥቃይ መቋቋም ይችላሉ። እንዲሁም ሊወጡ የሚችሉ ተጨማሪ ተጨባጭ ውጤቶች አሉ። ምናልባት ውሸቶቹን መጠገን ወይም ተጨማሪ ውሸቶችን መሸፈን ሊኖርብዎ ይችላል፤ ይህም ላለመገኘቱ ጭንቀት ይፈጥራሉ።
ማሪያ ሆዜ እንደሚነግሩን ካርማ አንፃራዊ እንጂ በመልካም እና በክፉ መካከል ብቻ የተለየ አይደለም። አንድ ነገር ሲያደርጉ ወይም አንድ ነገር ሲናገሩ ሁልጊዜ 100 በ100 ጥሩ፣ ወይም መጥፎ ላይሆን ይችላል። አንዳንድ ጊዜ መጀመሪያ «ጥሩ ናቸው» ብለን የምናስባቸውን ነገሮች እናደርጋለን፤ ግን በኋላ እንደዚያ እንዳልነበሩ ተገንዝበን ከባድ ስሜቶች እንድንሰማ ያደርገናል።
በዚህች ጽሑፍ ውስጥ እስካሁን ያነሳናቸው ፍሬ ነገሮች ሁሉ፣ ከሞላ ጎደል በዚህች፣ በማሪያ ሆዜ ሮልዳን አስተሳሰብ ውስጥ ተሸጉጠው የሚገኙ ይመስለናልና ጸሐፊውን እያመሰገንን ወደ ማጠቃለያችን እንሂድ።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ቴዎድሮስ ገብሬ “The Genius Loci of Addis Ababa /የአዲሳባ አድባር” በሚል ርእስ ባቀረበው የጥናቱ አጠቃሎ (Abstract)፤
በማደሪያውና በኀዳሪው መካከል የሚፈጠረው፣ ሥፍራን ሰብአዊና ኅሊናዊ የሚያደርገው ስንኝት በላቲን “genius loci” ተብሎ ይጠራል። እኛ ደግሞ «አድባር» ብለን ልንሰይመው እንችላለን። አድባር የሚለው መጠሪያ የሚወለደው ከግዕዙ «ደብር» ሲሆን፤ «ደብር» «ወሰን፣ ድንበር፣ መዲና፣ ከተማ፣ ታላቅ አገር» እንደ ማለት ነው። «አድባር»፣ አንድም ከ«ደብር» ጋር የሚተካከል አቻ አካላዊ ህልውና፤ አንድም፣ እንደ አለኝታ፣ እንደ ጠባቂ ባለ ቅጥ ኅሊናዊ፣ መንፈሳዊና ነፍሳዊ ኑባሬ አለው። [. . .] አዲስ አበባ–የኢትዮጵያ ደቂቅ አምሳል (microcosm)– ከልዩ ልዩ ኢትዮጵያዊ ባህሎች የወረሰቻቸው፣ አልምዳና ገርታ «ከተሜ» ያደረገቻቸው በደረጃ የሚለያዩ የሥፍራ መንፈሶች አሏት። ለምሳሌ፣ አዋይ የቤት ጠባቂ መንፈስ ናት፤ ቆሌና ከራማ የመንደር አለኝታ መናፍስት ናቸው።
«አድባር» የሚለው መጠሪያ ዝምድናው ከወሰን፣ ከድንበር፣ ከመዲና፣ ከከተማና ከአገር ጋር በመሆኑ ሁሉንም ይጠቀልላል። «የአዲሳባ አድባር» በስሜት፣ በሐሳብና በፍቺ ሥግው ናት። አድባር በተፈጥሮና በሰው መካከል ሚዛን የመትከል፤ በግለሰብ እና በማኅበረሰብ መካከል ኅብር የመፍጠር ዐቢይ ሚና አላት። በአንዳች ሰብአዊ ግፊት ይህንን ሚና መወጣት ያቃታትና የሸሸች ዕለት እንደ ኀዘኗ፣ እንደ ድንጋጤዋ፣ እንደ ቁጣዋ መጠን በሰውና በተፈጥሮ፣ በሰውና በማኅበሩ፣ በሰው እና በገዛ ራሱ ኅሊናና ልቡና መካከል ያለው ሁለንታዊ ትስስር ይላላል። ሲብስ ትስስሩ ተበጥሶ ሚዛን ይዛባል፤ ኅብር ይበጠበጣል። ሲከፋ መአት ይወርዳል፤ ቀውስ ይነግሳል።
እንዲህ በማለትና አስረጂዎችን በማቅረብ ያሰፈረው ሀሳብ መሠረታዊ ሲሆን፣ ሙሉ ጥናቱን ወደ ፊት አግኝተን እንመረምረዋለን ብለን ተስፋ በማድረግ፣ እንደ እነዚህ ዓይነት የጥናትና ምርምር ሥራዎች የሚበዙበትን፤ እንደ ልብም ወደ አደባባይ ወጥተው የሕዝብ የሚሆኑበትን ጊዜ በናፍቆት በመጠበቅም ነው።
ይህ ጸሐፊ «እንደ እውነቱ ከሆነ ካርማን በትክክል የሚገልጽ አቻ ቃል የለም።» ከሚሉት ወገን ነው። በመሆኑም ካርማ ሁሌም ይጠናል፤ ሁሌም ይጻፍበታል፤ ሁሌም ያወያያል . . . ያነጋግራል . . . እንጂ እዚህ ጋ «በቃ» ተብሎ የሚቆም ጉዳይ አይደለም። በዚሁ መሠረት፣ እኛም እዚሁ ላይ አቁመን ምናልባት የኛኑ «ከራማ» ሊገልጡ፤ ሊገላልጡና ሊያሳዩን (ልክ እንደ ላይኛው ቴዎድሮስ) የተዘጋጁ ካሉ እነሱን ወደ መጠበቅ እናመራለን።
ቸር እንሰንብት!!!
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 17/2015