በኢትዮጵያ እግርኳስ ታሪክ ስማቸው በጉልህ ከሰፈረ ስኬታማ አሰልጣኞች መካከል የሚጠቀስ ነው። የተወለደው በአዲስ አበባ ልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አካባቢ ነው። የተጫዋችነት ህይወቱን የጀመረውም በሰፈሩ በሚገኘው መስከረም ኮከብ በተባለው ቡድን ውስጥ ነበር::
የክለብ ህይወቱንም በዳርማር፣ ጥጥ ማህበር፣ ሙገር ሲሚንቶ፣ ህንጻ ኮንስትራክሽን፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና በኋላም በደርግ ክለቦች አደረጃጀት በትግል ፍሬ በመጫወት አሳልፏል። አሁንም ድረስ ‹‹ጎራዴው›› የሚል ቅጽል ስም ያተረፈለት ጠንካራ ተከላካይ በመሆኑ ነበር። ለጥጥ ማህበር በሚጫወትበት ወቅት የሐረርጌ ምርጥ፣ በቅዱስ ጊዮርጊስ እያለ ደግሞ ለሸዋ ምርጥ እና ለመኢሰማ ተጫውቷል። በረጅም ጊዜ የብሄራዊ ቡድን ቆይታውም በ10ኛው እና 11ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ የመጀመርያ ተሰላፊ ነበር።
አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ ‹‹ጎራዴው›› በተጫወተባቸው ክለቦች በሙሉ አስገራሚና አስደማሚ ድሎችን በማስመዝገብ ኮኮብ ተጫዋች ሊሆን ችሏል:: ከ50 ዓመታት በላይ በእግር ኳስ ተጫዋችነትና አሰልጣኝነት ቆይታውም በርካታ ክብሮችና ስኬቶችን መቀዳጀት፣ ዋንጫዎችንም ማንሳት ችሏል:: አሰልጣኞችንና እግር ኳስ ተጫዋቾችን በማፍራት ረገድም ‹‹አንቱ›› የተባለ፤ ከውጪ አገር ዋንጫን ማምጣት እንደሚቻልም ቀድሞ ያሰየ የበርካታ ታሪኮችና ገድሎች ባለቤት ነው:: ባስመዘገባቸው ዘመን አይሽሬ ታሪኮችም የአገር ባለውለታ መሆን ችሏል::
ከውጤታማ የእግር ኳስ ተጫዋችነት ቆይታ በኋላ በ1970ዎቹ በተጀመረው የአሰልጣኝነት ዘመኑ በርካታ ክለቦችን አሰልጥኗል። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ህንጻ ኮንስትራክሽ፣ መከላከያ፣ ኤሌክትሪክ፣ መድን፣ ደደቢት፣…ክለቦች ከብዙ ጥቂቱ ናቸው።
አሰልጣኝነቱን የጀመረው በትግል ፍሬ እግር ኳስ ክለብ ሲሆን፤ በአሰልጣኝነትና በተጫዋችነት ቻምፒዮን ማድረግ ችሏል:: ከትግል ፍሬ በመቀጠል ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በርካታ የድል ዓመታትን አሳልፏል:: ክለቡን ከሁለተኛው ሊግ ወደ ዋናው ሊግ በማሳደግም ጉልህ ሚናን ተጫውቷል:: ቅዱስ ጊዮርጊስ በታሪክ የመጀመሪያውን የፕሪሚየር ሊግ፣ የጥሎ ማለፍ እና የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን በአስራት ኃይሌ አሳክቷል።
በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ደረጃ በተጫዋችነት፣ በጊዚያዊ አሰልጣኝነት እና በዋና አሰልጣኝነት በመስራትም ውጤታማነቱን አስመስክሯል:: ብሄራዊ ቡድኑን በተከታታይ ሶስት ጊዜያት በጊዜያዊ አሰልጣኝነት በመያዝ የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ አድርጓል:: አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ ‹‹ጎራዴው›› በዋልያዎቹ በረዳት አሰልጣኝነት ቆይቶ እአአ በ2002ቱ የሴካፋ ዋንጫ ውጤት በማጣቱና በስፖርት ቤተሰቡ ቁጣን በመፍጠሩ ጀርመናዊው የወቅቱ የብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ጆቼን ፊጌን መሰናበትን ተከትሎ ቡድኑን በጊዚያዊ አሰልጣኝነት ቢይዝም ከቆይታ በኋላ ተለያየ::
በድጋሚ ብሄራዊ ቡድኑን ቢይዝም ለ2004ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ሳያልፍ በመቅረቱ ከስራው ሊሰናበት ቻለ:: በሱ ምትክም አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ቢተካም አሁንም ብሄራዊ ቡድኑ ውጤታማ ሳይሆን ቀርቷል:: አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ እአአ በ2004 በወርሃ ታህሳስ በምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ዋንጫ (CECAFA) መጀመር ጥቂት ሳምንታት በፊት በድጋሚ የዋልያዎቹ ዋና አሰልጣኝ በመሆን ተሾመ:: የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ዋንጫን ለመጀመሪያ ጊዜ ማሳካት የቻለ ብቸኛ አሰልጣኝ በመሆን በኢትዮጵያ እግር ኳስ አሻራውን አሳርፏል። ይሁንና ከውድድሩ መጠናቀቅ በኋላ ከብሄራዊ ቡድኑ በገዛ ፍቃዱ ለቀቀ:: በወቅቱም ‹‹ከእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ የሚመጣውን ብሄራዊ ቡድኑን አሰልጥን የሚል ኮንትራት ጥያቄ አልቀበልም›› በማለት አስተያየት ሰጥቷል::
በነዚህ ዓመታት በእግርኳስ ቆይታው፣ በውጤታማነቱ፣ በቆራጥነቱ እና ጠንካራ ሰራተኝነቱ በበርካቶች ዘንድ ይወደሳል። በቅርብ ዓመታት ደግሞ የቴክኒክ ዳይሬክተር በመሆን ሰርቷል።
ታታሪው አሰልጣኝ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ እጅግ የደመቀ የጀግንነት፣ የድልና የጽናት ተምሳሌትም ነው:: አሁን ግን ከኖረለትና ብዙ ውለታ ከዋለለት ስፖርት በተለያዩ ምክንያቶች ርቆ ይገኛል:: ለአገር ከሰጠው የማይተካ ሚና አንጻር የተሰጠው ክብር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም:: አሰልጣኙ ከሚወደው ስራው ከመራቁም በላይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጤንነቱ ታውኳል:: የኢትዮጵያ ቅርስ የሆነው አሰልጣኝና የበዙ እውቀቶች ማህደር ጤንነት መታወክ ብዙ ኢትዮጵያውያንን አስደንግጧል::
‹‹በእጅ ያለ ወርቅ›› እንደሚባለው አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ ተገቢውን ህክምና በቶሎ ማግኘት የማይችል ከሆነ፣ ህይወቱን እስከማጣት ሊደርስ እንደሚችልም ተነግሯል:: ህክምናው በአገር ውስጥ መስጠት የማይቻል በመሆኑ ውጭ አገር ሄዶ መታከም ስላለበት እንዲሁም ለህክምና የሚያስፈልገው ገንዘብ ከቤተሰብ አቅም በላይ ስለሆነ የእርዳታ ጥሪም ቀርቧል::
የአሰልጣኝ አስራት ኃይሌን ህይወት ለመታደግና ለህክምና የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለማሰባሰብ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ስራ ገብቷል:: ከተለያዩ የሙያ ዘርፎች የተወጣጣና በኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው የሚመራው ኮሚቴ የገቢ ማሰባሰብ ስራውን በይፋ መጀመሩን ግንቦት 9/2015 ዓ.ም በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል:: ለአንጋፋው አሰልጣኝ የሚደረገውን ድጋፍ የተሳለጠ እንዲሆን በኮሚቴው ስም በተከፈቱት ሁለት የባንክ ቁጥሮች ብቻ ገቢ እንዲደረግም ጥሪ ቀርቧል:: ይኸውም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1000544405617 እና በንብ ባንክ 7000043195037 ነው:: ኮሚቴው በስሙ ከተከፈቱት የሂሳብ ቁጥሮች ውጭ የሚሰበሰብ ገንዘብ እንዳይኖርም ማሳሰቢያ ሰጥቷል::
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ግንቦት 13/2015