በትግራይ አንድ ሺህ 700 የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ወደ መደበኛ ሥራቸው ተመልሰዋል

አዲስ አበባ፡- በትግራይ ክልል አንድ ሺህ 700 የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ወደመደበኛ ሥራቸው እንዲመለሱ መደረጉን የክልሉ ጤና ቢሮ ገለጸ፡፡

በጤና ቢሮው የጤና ኤክስቴንሽንና ጤና ማስተዋወቅ ቡድን አስተባባሪ አቶ ሚካኤሌ ሐጎስ እንዳስታወቁት፤ ከሰሜኑ ጦርነት በኋላ የጤና ኤክስቴንሽን ሥራውን የሚያራምዱ ባለሙያዎች ወደ ቀድሞ የሥራ ቦታቸው እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡

ከግጭቱ በፊት በክልሉ ሁለት ሺህ 500 የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች እንደነበሩ አስታውሰው፤ አሁን ላይ አንድ ሺህ ሰባት መቶ ባለሙያዎች ወደአገልግሎት እንዲመለሱ መደረጉን ጠቁመዋል።

ወደሥራቸው የተመለሱ በርካታ ባለሙያዎች የስነ-ልቦና አቅማቸውን የሚያሳድግና ቀድሞ ወደነበሩበት የሥራ መንፈስ መመለስ የሚያስችል ስልጠና ተሰጥቷል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

እንደ አቶ ሚካኤሌ ገለጻ፤ ከስድስት ወራት በፊት ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በክልሉ የተጓተቱ የተለያዩ የጤና የኤክስቴንሽን ፕሮግራሞችን ለማስጀመር የሚያስችል የአሰልጣኞች ስልጠና ተሰጥቷል፡፡

ስልጠናው ለጤና ኤክስቴንሽን ባሙያዎች ተሰጥቶ ማህበረሰቡም እንዲያውቀው ተደርጓል ያሉት አስተባባሪው፤ ወደ ሥራ ለመግባት በዝግጅት ምዕራፍ ላይ እንገኛለን ሲሉ ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ ሚካኤሌ ገለጻ፤ የግብአትና ለፕሮግራሞቹ መንቀሳቀሻ የሚሆን በጀት እጥረት፣ ከስር የሚወጡ መረጃዎች አለመጠናከርና ሌሎች ክፍተቶች ስራወን ወደተፈለገው ደረጃ ለማድረስ ተግዳሮት የሆኑ ነገሮች ናቸው፡፡

የግብአት አቅርቦት ሲመቻች የተለያዩ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራሞችን በቅርቡ ወደሥራ ለማስገባት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።

ክፍተቶቹ ከተሟሉ የጤና ኤክስቴንሽን ሥራውን ማሻሻል ይቻላል፤ ለዚህም ከጤና ቢሮ ትልቅ ጥረት የሚያስፈልግ በመሆኑ ከሚኒስቴሩ ጋር ይበልጥ ተቀራርቦ ለመሥራት የሚያስችል ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

በክልሉ ከሚገኙ የጤና ተቋማት መካከል በጦርነቱ ምክንያት 80 በመቶ የሚሆኑ የተለያዩ መጠን ያለው ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን አመላክተው፤ አፋጣኝ ድጋፍ በሚያስፈልግ ቦታዎች ባለሙያዎቹ ድጋፍ እየሰጡ ይገኛል ብለዋል፡፡

በትምህርት ቤቶችና ሰዎች በብዛት ወደሚሰባሰብባቸው አካባቢዎች በመሄድ የሕክምና አገልግሎት እየቀረበ መሆኑን የገለጹት አቶ ሚካኤሌ፤ በምግብ እጥረት ለተጎዱ ሕፃናት ልየታ የማድረግና ሕክምና የመስጠት ሥራ እየተሠራ መሆኑን አመላክተዋል።

በተጨማሪም ለወባ፣ ኮሌራና በሌሎች አፋጣኝ በሽታዎች ላይ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ በሽታዎቹን ለመግታት ባለመቻሉ ወደ መደበኛ የጤና አገልግሎት ሥራዎች ለመግባት ተጨማሪ አቅም ይጠይቃል ሲሉ አስረድተዋል።

አመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You