አዲስ አበባ፡- አንዳንድ ሚዲያዎች ከለውጡ በኋላ የተገኘውን ነጻነት በአግባቡ እየተጠቀሙበት አለመሆኑ ተገለጸ።
የዓለም የፕሬስ ቀን ‹‹ሚዲያ ለዴሞክራሲ ፤ ጋዜጠኝነትና ምርጫ በዘመነ የመረጃ ብክለት›› በሚል መሪ ቃል በብሮድካስት ባለስልጣንና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በእሸቱ ጮሌ አዳራሽ በውይይት ተከብሯል።
በመድረኩ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት ለረጅም ጊዜ በሀገር ውስጥና በውጪ ሚዲያዎች በጋዜጠኝነት የሰሩት፤ በአሁኑ ወቅት በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ በማገልገል ላይ የሚገኙት አቶ ማዕረጉ በዛብህ እንደተናገሩት በለውጥ ማግስት ሁሌም ብሩህ የሚዲያ ነጻነት ቢኖርም በአግባቡ መጠቀም ይገባል።
አጼ ኃይለስለሴ ወርደው ደርግ ስልጣን ሲይዝ ለተወሰነ ጊዜ ነጻነት ሰጥቶ ነበር። ብዙ ሰው ይጽፍ ነበር። በኋላ ግን ነጸነቱ ሊጠፋ ችሏል። በተመሳሳይ ሁኔታ ኢህአዴግ ስልጣን የያዘበት ወቅት አንጻራዊ የሚዲያ ነጻነት ነበር። ትንሽ ቆይቶ የሚዲያ ነጻነት ሊታፈን ችሏል ብለዋል። አሁንም ለውጡን ተከትሎ ነጻነት አለ ያሉት አቶ ማዕረጉ አሁን ያለውን ነጻነት ተከትሎ በሚዲያዎች ብሄርን ከብሄር የሚያጋጩ ተግባራት ሲፈጸሙ ይታያል ብለዋል።
‹‹ሚዲያዎች ነጻነታቸውን ያለ አግባቡ ሲጠቀሙ ነጻነታቸውን እያጡ ይሄዳሉ›› ያሉት አቶ ማዕረጉ አሁን ያለውን አንጻራዊ ነጻነት ያለ አግባብ በመጠቀም በተለይም በማህበራዊ ሚዲያዎች እየተከናወኑ ያሉ አሉታዊ ተግባራት የሚዲያ ነጻነት ላይ ጥቁር ጠባሳ የሚያሳርፍ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ለረጅም ጊዜ በተለያዩ ሚዲያዎች በባለሙያነትና በአመራርነት ያገለገሉትና የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽንስ ማዕከል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አማረ አረጋዊ እንደሚሉት፤ አሁን ሥራ ላይ ያለው ህገ መንግስት ፕሬስ ነጻነቱን ጠብቆ እንዲሰራ የሚያስችል ድንጋጌዎችን ቢያካትትም በተግባር የፕሬስ ነጻነት ችግር ውስጥ ይገኛል። መንግሥት፣ የሚዲያ ተቋማትና ባለሙያዎች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማትና ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚዲያ ነጻነት ችግር ላይ እንዲወድቅ የራሳቸውን አበርክተዋል።
ይህ ወቅት ከምንጊዜውም በላይ ሚዲያዎች አስተዋጽኦዋቸውን ማበርከት ያለባቸው ወቅት ነው ያሉት አቶ አማረ፤ አሁን ሚዲያውን ወደ መስመር ለማስገባት የሚደረጉ ጥረቶችን አጠናክሮ በመቀጠል ወደ መስመር ማስገባት ይገባል ብለዋል።
የብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ በበኩላቸው፤ አንዳንድ ሚዲያዎች ያለውን ነጻነት ተጠቅመው ከድንበራቸው ውጪ ሲወጡ ይታያል። ባለስልጣኑ ግን ሚዲያዎቹ ላይ እርምጃ በመውሰድ ሳይሆን በውይይት መፈታት እንዳለበት ያምናል ብለዋል። በመሆኑም ከሚዲያዎች ጋር የሚደረጉ ውይይቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ።
እንደ ዶክተር ጌታቸው ማብራሪያ፤ የሚዲያውን ችግር ለመቅረፍ ሀገራዊ የሚዲያ ፖሊሲ እየወጣ ነው። አሁን ሥራ ላይ ያሉ ህጎችንም ከፖሊሲው ጋር የተጣጣሙ እንዲሆኑ የክለሳ ሥራ እየተሰራ ነው ብለው የሚዲያ ሞኒተሪንግ ቴክኖሎጂ ከፈረንሳይ ሀገር ገብቶ በቅርቡ ሥራ ይጀምራል። የሚዲያ ባለሙያዎችን አቅም ለማሳደግ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ስልጠና እንዲያገኙም ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 24/2011
በመላኩ ኤሮሴ