ኢትዮጵያን ለ7 ዓመታት በፕሬዚዳንትነት ያገለገሉት የቀድሞው ርዕሰ ብሔር ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ በ75 ዓመታቸው ህይወታቸው ማለፉ ተሰምቷል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ዶክተር መረራ ጉዲና ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ከእሳቸው ጋር መቀራረብ የጀመሩት የገዥው ፓርቲ አባልነታቸውን አቁመው ወደ ሕዝብ ትግል ከተቀላቀሉ በኋላ ነው።
ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ሁለት ሦስት ነገሮች ላይ በበጎነት መታወስ የሚገባቸው ናቸው። የመጀመሪያው በዚያን ጊዜ ገዥውን ፓርቲ በተለይ የወቅቱን ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ‹‹የምትሰራው ሥራ መንግስቱ ኃይለማርያምን መሰልከኝ ›› ብለው ተናግረው ስብሰባ ረግጠው መውጣታቸው በዚያን ወቅት የተፈፀመ የተለየ ድፍረት ነው። ይህን አከናውነው መውጣት መቻላቸው ሊያስመሰግናቸው ይገባል። ባላመኑበት ነገር ‹‹አላምንም›› ብለው በዚያን ዘመን መናገር ከባድ ነው። አሁን ቢሆን እንኳን ብዙ ሰው ይናገራል። በዚያን ጊዜ ወቅቱ አስቸጋሪ ነበር። እንደዚያ መናገር መቻል በእውነቱ ቀላል አይደለም።
ሁለተኛ ደግሞ በዚያ ፖለቲካ ውስጥ እንደገቡት እንደሌሎች ካድሬዎች ለትርፍ አይመስልም። ለምሳሌ ሌሎች ካቢኔዎች የቀበሌ ተመራጮች ሳይቀር መኪና፣ ቤትና ንብረት ሲያፈሩ ‹ ‹የአገር መሪ ነኝ›› የሚል ሰው አንድ ቤት፣ አንድ መኪና እንኳን ሳይዝ መውጣቱ ንጽህናቸውን የሚያሳይ ነው ።
እኔ እስከማውቀው የቤት መስሪያ ቦታ እንኳን አልነበራቸውም። ቤት አልነበራቸውም፣መኪና አልነበራቸውም። ‹‹የተቃዋሚ ፓርቲ ቋንቋ መናገር ጀመርክ ተብለው በመንግሥት የተ ሰጣቸውን መኪናም ጭምር ተቀምተዋል። ያንንም እያወቁ እዚያ ውስጥ መግባታቸው ያስመሰግናቸዋል።
ከዚያም በኋላ እንደተራ ሰውም ላገልግል ብለው በተወለዱበት አካባቢ ደምቢዶሎ ሄደው የነበረ ቢሆንም የፓርላማ አባል ሆነው ተመርጠው ለአምስት ዓመታት ያህል አገርን በንፅህና ማገልገል ችለዋል።
አምና ለፖለቲካ ፓርቲዎች አንድነት ለመስራት ሞክረዋል። በተለይ ከዚያ በኋላ መድረክ ተብሎ በተዋቀረው ቡድን በፓርቲዎች ጥምረት ለአንድ ዓመት ያህል ስንደራደር ከእኛ ጋር እየተመላለሱ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረጋቸው ታሪክ አይረሳውም።
በአጠቃላይ ፖለቲካ ውስጥ የገቡት ለትርፍና ለሆዳቸው ሳይሆን ለአገር አስተዋጽኦ ለማድረግ ነው። ያንን ለመፈፀም በማይችሉበት ደረጃ ላይ ሲደርሱ ባለው ሥርዓት (ሲስተም) ያንን ለቅቆ መውጣት መቻል ሌሎች የፖለቲካ ባለሥልጣናት ትምህርት ሊወስዱ ጥሩ ነው። በዚህ መንገድ ለሕዝብ መስራት ከተቻለ፣ ሕዝብን ማገልገል ፣ለሕዝብ መብት አስተዋጽኦ ማድረግ ከተቻለ ተመራጭ እንደሆነ ተናግረዋል።
ፖለቲካን ወደ ንግድ መለወጥ አይገባም። ካልሆነም ደግሞ ለቅቆ መውጣትም መለመድ አለበት። ሌሎቹ በማያምኑበት ሥርዓት ውስጥ ሆነው ልጆቼን ላሳድግበት ምናምን እያሉ መኖርን የሚመርጡ አሉ። እሳቸው ግን በራሳቸው ላይ ጨክነው የሚመጣውን ግፊትም ችለው ኖረዋል። ቤታቸው በላያቸው ላይ እስከ መታሸግ ሊደርስ ችሏል። ያንን ሁሉ ተቀብለው ለአገር አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችሉትን አድርገዋል።
‹‹ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል›› የሚባለውን አባባል ሊሰብሩ ሞክረዋል። ሌሎቹም ያንን ቢያደርጉ መልካም ነው። ፖለቲካ ለሆድ መሆን የለበትም። ለአገር ማገልገል ሲቻል መስራት ነው። ካልሆነ ደግሞ አልሆነም ብሎ በአደባባይ ለሕዝብ ተናግሮና ምርጫን ለሕዝብ ማሳወቅ መልካም ነው። እዚያው ዝም ብሎ እየተሽከረከሩ የሕዝብ መብት ሲረገጥ ፣ሕዝብ ሲዋረድ፣ሲታሰር፣ሲገደል ዝም ብሎ እያዩ ልጆቼን ላሳድግ፣ እንትንም ላድርግ እየተባለ በየቦታው እየተሞዳሞዱ መኖር ጥሩ አይደለም። ከዚያ ውጪም ሰው የሕዝብ አመኔታና ክብር አግኝቶ መኖር እንደሚችል በተወሰነ ደረጃ ለማሳየት ሞክረዋል። እኔ እነዚህን አስተዋጽኦዎች እንደበጎ ነገር አያቸዋለሁ ብለዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 24/2011