አዳማ ገልማ አባ ገዳ አዳራሽ “ድሮም አንድ ነበር፤ አሁንም አንድነን” እያሉ የቢፍቱ ኦሮሚያ አባላት ጣዕመ ዜማ ያሰማሉ። ከኦሮሚያና ከኢት ዮጵያ ሱማሌ የመጡ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ከፍተኛ የሁለቱ ክልል ባለስልጣናትን የጣዕመ ዜማው እውነትነት ስሜታቸውን ተቆጣ ጠረው።
“ጊዜያዊ ችግሮች ያሻከረው ልባችንን በይቅርታ በማለፍ በትብብር ዓለም የሚደነቅባትን ኢትዮጵያን እንገነባለን” በፖለቲካ ሴራ በደረሰው ጉዳት ልባቸው ቢጎዳም በዜማው የተነገረው ሀቁ ሀቅ ነው፤ በዜማው ዳንኪራ ባይወርዱም ሀቅነቱን ኪሳቸውን ፈቶ ለዜመኞቹ በሰልፍ ወጥተው እየተቃቀፉ በመስጠት ሀቅነቱን አረጋገጡ። ያለፈውን አንድነታቸውን ለማጠንከር፣ የፖለቲካ ሴራ ያሻከረው ልባቸውን ለመፈወስ፣ የወደፊቱንም አንድነትና ዕድገትን አረጋገጡ። ሴራው ላይደገም፤ መለያየት ላይኖር የባህል፣ የቋንቋ፣ የደም አንድነታቸውን ለዘለዓለም ለማጽናት ቃል ገቡ።
በኦሮሞና ሱማሌ መካከል ጊዚያዊ ችግር፤ ሴራ መሆኑና የማይለያዩ መሆኑን የአዳማው የሱማሌና የኦሮሞ የሰላም ኮንፈረስ ተሳታፊዋ ዘምዘም አሌ ትናገራለች። ታሪክ ማረጋገጫ ነው። ዘምዘም 19 ዓመቷ ሲሆን 12 ወንድምና እህት አላት። ተወልዳ ያደገችው በጅግጅጋ ከተማ ነው። አባቷ ኦሮሞ ሲሆን እናቷ ሱማሌ ናቸው። በእነሱ ቤት የሱማሌኛም ሆነ የኦሮምኛ ቋንቋ መሳለመሳ ይተገበራል፤ ይነገራልም። እንደነዘምዘም አይነት በርካታ ቤተሰቦች በሁለቱ ብሄሮች መካከል ተጋምደው ይኖራሉ። ይህን መጋመድ ለዘለዓለም ይኖራል እንጂ ማንም አይፈታው ብላለች።
ሁለተኛው የሁለቱ ብሄሮች ገጽታ በወቅታዊ የፖለቲካ ሴራ የዜጎች መሞት፣ መቁሰልና መፍናቀል ሌላኛው የዜጎች ጊዜያዊ ችግር ነው። ለዚህም ችግር የነዘምዘም ቤተሰብ ምሳሌ ነው። በጅግጅጋ ከተማ በነበረው ግጭት ጥቃት እንደሚያደርስባቸው ሙሉ ቤተሰብ ተፈናቅለው አዳማ መምጣታቸውን ትናገራለች። ጊዚያዊ የፖለቲካ ሴራ ከህይወት እስከ መፈናቀል ጉዳት አድርሶብናል። ግን ጊዚያዊ ነው ቀድሞም አንድነን ወደፊትም አንድ እንሆናለን ብላለች።
ከቦረና የመጡት የአገር ሽማግሌ ካቴሎ ኦዶ፤ ሁለቱ ብሄሮች “የእኔ የአንተ” ሳይባባሉ በፍቅር ሲኖሩ ነበር። ሁለቱ በሁለቱ ባህልም በጋብቻ ሲተሳሰር ነው የኖረው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን “የአንተን ቦታ ወሰደብህ እያሉ” እርስ በእርስ እንድንጎዳዳ አድርገውናል ብለዋል። የህዝቡ ፍላጎት ሳይሆን ከኋላ ሆነው የሚያጎዳዱን ሰዎች ነበሩ የሚሉት ካቴሎ ችግሩ የህዝቦቹ አለመሆኑ ማሳያው አሁን ላይ ወደ ፍቅር በመመለስ አብረው እየኖሩ ነው ይላሉ።
የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሽመልስ አብዲሳ፤ የኦሮሞና የሱማሌ ክልል ህዝቦች ከአንድ የኩሽ ግንድ የወጣ፣ በአንድ ላይ ተጋምዶ በችግርና በደስታ ወቅት አብሮ የኖረ ህዝብ ነው። ባለፉት ስርዓት የነበሩትን ጭቆናዎች ለነፃነትና ለዕኩልነት አብሮ ታግሏል። ዛሬም እየታገለ ነው ብለዋል።
የሁለቱ ክልል ህዝቦች ግንኙነት፤ በአፈናቃዮች፣ በገዳዮችና በኮንትሮባንዲስቶች ሴራ ለዓመታትና ለወራት ቢደናቀፍም አይቀጥሉም። እነዚህ አካላት ሁሉም ይጠፋሉ። ምክንያቱም የህዝቦች ተጋምዶና አንድነት ከሴራም ከጦርነትም በላይ ነው። ሴረኞችን ለማጥፋትም ወንድማማችነትን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
በሁለቱ ህዝቦች መካከል ዛሬ ያለውን አንድነት ሲያዩ በርካቶች ይደሰታሉ። ጥቂቶች የቀራቸውን ዕድል ለመሞከር ይፍጨረጨራሉ። ይህን ለማክሸፍ መስራት አለብን። የተፈናቀሉ ወደ ቦታቸው መመለስ ይገባል። ከዚህ በኋላ መንገድ የሚዛጋ ጠላት በመሆኑ ሁሉም ተባብሮ ሊሰራ ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። በአጠቃላይ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በማህበራዊ ተባብሮ በመስራት የበለጸገች ኢትዮጵያና ምስራቅ አፍሪካን ለመፍጠር እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፊ መሀመድ ኡመር፤ በበኩላቸው በኦሮሞና በሱማሌ ክልሎች መካከል የወሰን ችግር አለመኖሩን አንስተው በሁለቱ ህዝቦች መካከል የፖለቲካ አሻጥር ተፈጥሮ ነበር ብለዋል። ‹‹የኦሮሚያ ክልል ትግል ሲያደርግ በምስራቅ የተከፈተበት ጦርነት ነው። ይህን ያደረገው የሱማሌ ክልል ህዝብ አለመሆኑን ኦሮሞዎችም ታውቃላችሁ። በሱማሌ ስም ስለተፈጸመ ተፈናቃዮችን ይቅርታ እንጠይቃለን›› ብለዋል።
የሁለቱ ክልል ህዝቦች በደም የተሳሰሩ መሆናቸውን ያነሱት አሁን ላይ ነፃነታቸውን በመቀዳጀታቸው በቀጣይ ያለማንም ማሳበብ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በማህበራዊ በጋራ መስራት አለብን። የተጀመረውም ግንኙነት እስከታች በማውረድ አንድነታችን ማጠናከር እንደሚገባም ተናግረዋል።
የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ ተግባራዊ በማድረግም የጋራ ልማትና ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ። የባህል ትስስሩን ማጠናከር። በፖለቲካ ሴራ የተፈጠሩ መዛባቶችን ማስተካከል ዋና ዋና ስራዎች መሆናቸውንም አስታውቀዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 24/2011
በአጎናፍር ገዛኸኝ