‹ሪፖርተርስ ዊዘአውት ቦርደርስ› የተሰኘ ዓለም አቀፍ ተቋም በቅርቡ ባወጣው የ2019 የዓለም የፕሬስ ሪፖርት እንዳስታወቀው ኢትዮጵያ የፕሬስ ነፃነት ረገድ 40 ደረጃዎችን አሻሽላለች። ይህ በአገሪቱ ታሪክ ትልቅ መሻሻል ቢሆንም ከለውጡ ማግስት ያለው የፕሬስ ነጻነት ምን ይመስላል? በዘርፍ የመጣው ተጨባጭ ለውጥ ምንድነው? ያጋጠሙ ችግሮችስ ?
የአሃዱ ኤፍ.ኤም 94.3 ሬዲዮ ጋዜጠኛና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጥበቡ በለጠ ከለውጡ ማግሥት በኋላ በሚዲያው ዘርፍ ለውጥ ውስጥ ዋነኛው የፕሬስ ነጻነት ነው። ምክንያቱም ከለውጡ በፊት ባሉት ባለፉት 27 ዓመታት የአገሪቱ ፕሬስ እጅግ አስከፊ ገፅታ ውስጥ እንደ ነበር ያስታውሳሉ። ጋዜጠኞች በሚናገሩትና በጻፉት ሀሳብ ብቻ መታሰር የቅርብ ጊዜ ታሪክ ነው ይላሉ። ጋዜጠኞች ብቻ ሳይሆኑ በእነርሱ አማካኝነት አስተያየት የሚሰጡና ሃሳባቸውን የሚገልጹ ሰዎች ሳይቀሩ በተለያዩ መንገዶች ተፅዕኖ ሲደረግባቸው ቆይቷል ይላሉ።
እንደ ጋዜጠኛ ጥበቡ ገለፃ ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ሲ.ፒ.ጄ ከ1984 እስከ 1994 ዓ.ም ባሉት አሥር ዓመታት «አሥሩ የዓለማችን ፕሬስ ጠላቶች» በሚል በየዓመቱ በሚያወጣው የዓለም አገራት ውስጥ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚና በዋናነት ትጠቀስ ነበር ብለው ይህም የፕሬስ ነጻነቱ ምን ያህል ቅርቃር ውስጥ ገብቶ እንደነበር አመላካች ነው ሲሉ አመልክተዋል።
‹‹ባለፉት 27 ዓመታት ውስጥ ብዙ ህንጻዎችና መንገዶች ተሰርተዋል፤ ሆኖም አንድም ጋዜጣ ወይምመጽሄት ግን ሊያድግ አልቻለም፤ ምክንያቱም ዘርፉ እንዲያድግ ስላልተፈለገ ነው፤›› ሲሉ ጋዜጠኛ ጥበቡ ይወቅሳሉ። ከለውጡ በኋላ ግን ያ ሁሉ ታሪክ እየመሰለ ነው ብለው አሁን የመጣው ለውጥ በእጅጉ የሚደነቅ ነው ሲሉ ይናገራሉ።
ማንም ሰው የፈለገውን የመናገርና የመጻፍ ተፈጥሯዊ መብት እንዳለው የሚገልፁት ጋዜጠኛ ጥበቡ ባለፈው አንድ ዓመት በተናገረው ወይም በጻፈው ሀሳብ ምክንያት የተከሰሰ ወይም የታሰረ ጋዜጠኛ የለም። ይህም ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር ይሆናል ተብሎ የማይታሰብና ያልተገመተ ትልቅ ለውጥ ነው ሲሉም አስታውቀዋል።
ይሁን እንጂ እንደ ጋዜጠኛ ጥበቡ ማብራሪያ ለውጡ የሚደነቀው ከመጣው ነጻነት አኳያ ነው እንጂ የአገሪቱ ፕሬስ አሁንም በርካታ ፈተናዎች አሉበት። «መንግሥት በፈቀደው የፕሬስ ነጻነትን ተጠቅመው ከውጭ አገር ወደ ኢትዮጵያ ገብተው ሥራ የጀመሩና በአገር ውስጥም ያሉ አዳዲስ ሚዲያዎች የሙያውን ሥነ ምግባርና ዓለም አቀፋዊውን አደረጃጀት ትተው የፖለቲካ ዓላማ ይዘው ወደ ሥራ ገብተዋል» ሲሉ ይናገራሉ።
ከዚህም ባሻገር ‹‹ሚዲያዎች በዘር እየተደራጁ ነው፤ለዚህ የክልል ሚዲያዎች አብነት ናቸው። በመሆኑም በዘር ላይ የተመሰረተ ሚዲያ በአገርና በህዝብ ላይ ከፍተኛ አደጋ ስለሚያስከትል አፋጣኝ መፍትሔ ሊበጅለት ይገባል።›› ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል። በማህበራዊ ሚዲያ በኩልም መንግሥት አሰራሩን በግልጽ ለህዝብ የሚያደርስበትን መንገድ መከተል እንጂ ማህበራዊ ሚዲያውን እንደ ስጋት በመቁጠር አተካራ ውስጥ መግባት አይገባም፤በዚህ ጉዳይ ነጻነት መስጠቱ የበለጠ ተመራጭ መሆኑን ይመክራሉ።
በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እያገለገለ የሚገኘው ጋዜጠኛ ብሩክ በርሄ በበኩሉ በአንድ ዓመት የለውጥ ጊዜ ውስጥ የህትመት፣የኦን ላይንና ብሮድካስት ሚዲያዎች የተሻለ የፕሬስ ነጻነት ይታይባቸዋል ይላል። ከዚህ ቀደም በነበረው የፖለቲካ ሂደት ሁሉም ሚዲያዎች ከፍተኛ የሆነ ፖለቲካዊ ቁጥጥር ይደረግባቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። ለውጡን ተከትሎ ግን ሚዲያዎች ሙሉ በሙሉ ነጻ ናቸው ባይባልም በተሻለ ደረጃ ማንኛውንም ሃሳብ በነጻነት የሚያንሸራሽሩበት ሁኔታ መፈጠሩን ይገልፃል።
ባለፉት 27 ዓመታት «ልማታዊ» እና «ፀረ ሰላም»በሚል ሚዲያዎች ለሁለት ተከፍለው መቆየታቸውን የሚያስታውሱት ጋዜጠኛ ብሩክ ከለውጡ በኋላ ግን ክፍፍሉ ተወግዶ ሁሉም ሚዲያዎች በነጻነትና በእኩልነት እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን መታዘቡን ተናግሯል። እንደ ጋዜጠኛው ገለፃ አገሪቱ የነበረችበት ቅርቃር ዛሬም ድረስ ለሚስተዋለው ችግር ምክንያት የነበረው የነጻነት እጦት እንደሆነም በምክንያትነት አስቀምጧል።
አሁን ያለው የሚዲያ ነጻነት ለሚዲያዎች ብቻ ሳይሆን እንደ አገር ያሉ የዴሞክራሲ ችግሮችንም ለመፍታት ጉልህ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብሎ ይሁን እንጂ የተገኘውን ነጻነት በአግባቡ ያለመጠቀምና ከሥነ ምግባር ውጭ ሚዲያን ለፖለቲካና ለግል ፍላጎት ማስፈጸሚያ የመጠቀም የተጠናከረ ሁኔታ ነፃነቱን ወደ ነበሩበት አፈና ሊመልስ ስለሚችል በጊዜ ሊታረም የሚገባ ተግዳሮት መሆኑን ይጠቁማል።
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ገብረጊዮርጊስ አብርሃ በበኩላቸው፤ ከለውጡ በፊት ህገ መንግሥቱን ጨምሮ በመረጃ ነጻነትና በብሮድካስት አገልግሎት አዋጆች ስለ ፕሬስ ነጻነት የሚመለከቱ አንቀጾች የተቀመጡ ቢሆንም ነጻነቱ ግን በተግባር አልነበረም ሲሉ ተናግረዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ በሙያውም ሆነ በባለሙያው በአጠቃላይ ደግሞ በሚዲያ ተቋማቱ ዘንድ ሥራቸውን በፍርሀት ሲያከናውኑ ቆይተዋል። በመሆኑም ተቋማቱ የራሳቸውንም ሆነ የተቋማቸውን ሃሳብ በነጻነትና በልበ ሙሉነት ማቅረብ አለመቻላቸውን አስታውሰዋል።
‹‹ተቋማቱ መንግሥት ተጠያቂ መሆን በሚገባው ጉዳይ ተጠያቂ ያለማድረግ፣ ህዝብ ሊያውቃቸው የሚገቡ መረጃዎችን ያለማቅረብ ድክመቶች እያሉባቸው ተቋማቱ ችግራቸውን «መረጃ ስንጠይቅ መረጃ አናገኝም፣ አዎንታዊ ነገሮችን ብቻ እንድንዘግብ ተደርገናል ፤ በሙያችን ላይ ጣልቃ ገብነት አለ» የሚል ሽፋን እየሰጡ ተጉዘዋል ሲሉ ይወቅሳሉ።
‹‹ከለውጡ በኋላ ግን አዎንታዊ ጉዳዮችን ብቻ ሳይሆን መንግሥትን ተጠያቂ የሚያደርጉ ሥራዎች እየታዩ ነው፤ ሚዲያዎች አንጻራዊ የሆነ ነጻነት ይታይባቸዋል” በማለት ይጋራሉ። ይህም ለፕሬስ ነጻነት አዲስ ለውጥ ነው። ይሁን እንጂ የሚዲያዎች ገለልተኛ አለመሆን አሁንም ዘርፉ ያልተሻገረው ተግዳሮት መሆኑን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።
በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት መምህር የሆኑት ዶክተር አደም ጫኔ በበኩላቸው፤ ከፕሬስ ነጻነት ጋር ተያይዞ ባለፈው አንድ ዓመት የመጣውን ለውጥ «በኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት ላይ የተዘጋው በር ተከፍቷል፤ ታስሮ የነበረው ጋዜጠኝነት ተፈቷል» በማለት በአጭሩ ይገልጹታል።
ስለሆነም ካለፉት 27 ዓመታት በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር አሁን በኢትዮጵያ አንጻራዊ የፕሬስ ነጻነት አለ፤ በመንግሥት ሚዲያዎች የበላይነት ተይዞ የነበረው ዘርፉ ለግሎችም ክፍት እየሆነ መምጣቱ፤ በአሸባሪነት ተፈርጀው የቆዩና ተዘግተው የነበሩ የግል ፕሬሶች እንደገና ሥራ መጀመራቸው በማሳያነት በመጥቀስ የጋዜጠኛ ጥበቡና የጋዜጠኛ ብሩክን ሃሳብ ይጋራሉ።
በራሱ በመንግሥት ሚዲያዎች ሳይቀር አይነኬ የሚባሉ ጉዳዮች ማንሳትና መሞገት መጀመራቸው እንዲሁም መንግሥት የፈጸመውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶችና ወንጀሎች ማጋለጥ መቻሉ የፕሬስ ነጻነት ላይ ለውጥ ለመኖሩ ተጨማሪ ማሳያዎች ናቸው ሲሉ ዶክተር አደም ጫኔ ተናግረዋል።
«ፕሬሱ ላይ የመጣው ለውጥ ሙሉ ነው ማለት አይቻልም» የሚሉት ዶክተሩ፤ በተለይም ከለውጡ ማግስት ሙያዊ ጋዜጠኝነትን መተግበር ላይ ከፍተኛ ችግር እየታየ መሆኑን በማመላከት ጋዜጠኞቹ ያነሱትን ሃሳብ ያጠናክራሉ። በዚህም ሰዎች መለየት እስኪያቅታቸው ድረስ አክቲቪስትነትና ጋዜጠኝነት የተቀላቀሉበትና ሙያው ችግር አጋጥሟል ባይ ናቸው፤ይህ ሁኔታ ለፕሬስ ነጻነት ትልቅ አደጋ ነው።
በአጠቃላይ አስተያየት ሰጪዎቹ ሊሰራበት ይገባል ያሉዋቸውን ጉዳዮች አስቀምጠዋል። ለፕሬስ ነጻነት እንቅፋት የሆኑ ወይም ይሆናሉ ተብለው የታሰቡ ህጎች ሳይቀር የማሻሻል ሥራዎች ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። በዚህ ረገድ አገሪቱ አዲስ የብሔራዊ የሚዲያ ፖሊሲ ባለቤት እንድትሆን ትልቅ ግብዓት መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፤ መልዕክታቸው ነው። ይህም በአገሪቱ የፕሬስ ነጻነትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ የአጠቃላይ አገራዊ ሪፎርም አካል ተደርጎ ሊሰራ ይገባል።
ስለሆነም ጠንካራና ገለልተኛ የሚዲያ ተቋማትና የሚዲያ ካውንስል በማቋቋምና ለዚህ የሚያግዙ የህግ ማዕቀፎችን በማውጣት ሙያዊ ጋዜጠኝነትን በጠንካራ መሰረት ላይ መገንባት ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆን እንዳለበት መክረዋል። የተገኘው የፕሬስ ነጻነት ዘላቂነት እንዲኖረውም ለውጡ ባህል እስኪሆን ድረስ ቀጣይነት ያለው ሥራ መስራት ይገባል። ለዚህም ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 24/2011
በይበል ካሳ