የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት/ተ.መ.ድ/ በጥቅምት 1945 /እ.አ.አ./ የተመሰረተ የምድራችን ግዙፉ ሁሉን አቀፍ ድርጅት ነው፡፡ ተ.መ.ድ ዋና መቀመጫውን በዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ ኒዎርክ ሲቲ በማድረግ 193 አባል ሀገራትን አቅፎ ለ72 ዓመታት ያህል የተንቀሳቀሰ ድርጅት ነው፡፡
ተ.መ.ድ ስድስት ታላላቅ ክፍሎች ያሉት ሲሆን፤ ጠቅላላ ጉባኤ /General Assembly/፣ የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት/security council/፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ምክር ቤት/ economic and social council/፣ የባላደራ ምክር ቤት/ Trusteeship Council/ ፣ ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት /International Court of Justice/ እና ዋና ጽሕፈት ቤት /Secretariat/ ናቸው፡፡ እነዚህ ድርጅቶች እጅግ ቁልፍ የሆኑ የድርጅቱን ተግባራት የሚመሩ አካላት ናቸው፡፡ በተጨማሪም በጄኔቫ፣ በናይሮቢ እና በቬና አካባቢያዊ መቀመጫዎች አሉት፡፡ ድርጅቱ አረብኛ፣ ቻይኒኛ፣ እንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ራሺኛ እና ስፓኒሽኛ ቋንቋዎች የድርጅቱ ኦፊሴላዊ ሥራ የሚሠራባቸው ቋንቋዎች ናቸው፡፡
ተ.መ.ድ በ72 ዓመት ዕድሜ ውስጥ ያስመዘገ ባቸው ውጤቶች እንዳሉ ይታመናል፡፡ ሰብአዊ መብቶችን ከመከላከል ጀምሮ እስከ ኢኮኖሚ ልማት ድረስ ያከናወናቸው ተግባራት አሉ፡፡ በተፈጥሮ አደጋዎች እና በጦርነት ጊዜ ውስጥ ድጋፍ እና ክብካቤ መስጠት፣ የህክምና ድጋፍ ለሚፈልጉ ወገኖች አገልግሎቱን ማድረስ፤ ንጹህ የመጠጥ ውሃ፣ ምግብ፣ ማረፊያ እና ማገገሚያ ቦታዎች /መጠለያዎች/ ማቅረብ፤ በተለያዩ ፕሮግራሞቹ እና ስራ ክፍሎቹ የድህነት፣ የረሃብ እና በሽታዎች ቅነሳ እና የትምህርት ማስፋፋት ሥራዎች በተለይ በአዳጊ /በታዳጊ/ ሀገሮች ሲያከናውን ነበር፡፡
ይሁን እንጂ ተ.መ.ድ የድካሙን እና የዕድሜውን ያህል አሁን በአባል ሀገራቱ ዜጎች ያለው መታመን ምን ያህል ነው የሚለው አጠያያቂ እየሆነ ነው፡፡ ተ.መ.ድ ለዓለም አቀፍ ችግሮች መቃለል ይሠራል ተብሎ ቢታመንም፣ በየጊዜው የሚወለዱ አዳዲስ እና ያልተፈቱ ዘመን ተሻጋሪ ቀውሶች እየተባዙ መሄዳቸው እንዲሁም የተፈጥሮ አደጋዎች መበራከት የድርጅቱን ተግባር እና ኃላፊነት በጥርጣሬ እንዲታይ እያደረጉት ነው፡፡ በርካቶችም ተ.መ.ድ ተሐድሶ የሚፈልግ ድርጅት መሆኑን አበክረው አሳስበዋል፡፡
የተሐድሶ ጥሪ
ለመንግሥታቱ ድርጅት የወደፊት ህልውና የድርጅቱን ተሐድሶ እውን ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ሀገራት፣ ሌሎች አካባቢያዊ የሀገራት የትብብር መድረኮች፣ መሪዎች እና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁራን እያሳሰቡ ነው፡፡ የደቡብ አፍሪካው አዲሱ ፕሬዚዳንት ራማፎዛ በቅርቡ ለተ.መ.ድ ጉባኤ ባደረጉት ንግግር ‹‹የተመድ ቁልፍ ድርጅት የሆነው የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት አጠቃላይ ተሐድሶ ሊደረግበት ይገባል›› ብለዋል፡፡ የምክር ቤቱ ተለዋጭ አባል የሆነችው ደቡብ አፍሪካ ለአህጉሪቱ/አፍሪካ/ ቢያንስ ሁለት ቋሚ እና አምስት ተለዋጭ አባላት ሊኖሯት ይገባል የሚል አቋም ታራምዳለች፡፡
ብሪክስ /BRICS/ የሚባለው ደቡብ አፍሪካ፣ ቻይና፣ ህንድ፣ ራሺያ እና ብራዚልን ያቀፈው ስብስብ የሀገራቱ ሚኒስትሮች ባደረጉት ስብሰባ የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ተሐድሶ ያስፈልገዋል የሚለውን ደግፏል፡፡ ይኸው ስብስብ በቀጥታ አይጠይቅ እንጂ በስብስባቸው ያሉት ሦስቱ ሀገራት ብራዚል፣ ህንድ እና ደቡብ አፍሪካ የምክር ቤቱ ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ፡፡ ያንንም በመጠቀም እያደገ የመጣውን ጠባብ ሀገራዊ ብሔርተኝነት፣ ህዝበኝነት እና የንግድ ቀጣና ከለላ ዝንባሌዎችን በዓለም አቀፋዊ እንቅስቃሴ ሊመከቱ ይገባል ብለው ያስባሉ፡፡
የኖርዲክ ሀገራት መሪዎችም ከዓመት በፊት ጀምረው ተ.መ.ድ እንደ ስሙ ለዓለም አቀፋዊ ተግባራት ማእከላዊ የሆነ ሚናውን መወጣት የሚያስችለው ተሐድሶ ሊያደርግ እንደሚገባ ግፊት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡
የአሁኑ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው ተ.መ.ድ ተሐድሶ ማድረግ እንዳለበት ሲያሳስቡ ነበር፡፡ ትራምፕ ‹‹ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ተ.መ.ድ ያለውን እምቅ አቅም የመጠቀም ደረጃ ላይ ሊደርስ አልቻለም፤ ምክንያቱ ደግሞ ጎታች ቢሮክራሲና የአስተዳደር ብልሹነት አለበት፡፡ ይህ ሆኖ እያለ የተ.መ.ድ መደበኛ በጀት በ140 በመቶ ጨምሯል፡፡ ከ2000/እ.አ.አ./ ጀምሮ ሲታሰብ ደግሞ የሰው ኃይሉ ከእጥፍ በላይ ጨምሯል፡፡›› ብለው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በቅርቡ ባደረጉት የተ.መ.ድ ጉባኤ ንግግራቸው ደግሞ ለተ.መ.ድ እንቅስቃሴ ፈተና የሚፈጥር ንግግር አሰምተዋል፤ ‹‹የዓለም አቀፋዊነትን ርዕዮተ ዓለም እንናስወግዳለን፤ የአርበኝነት/ሀገር ፍቅር/ ዶክትሪን መቀበል አለብን›› ብለዋል፡፡ ትራምፕ ለተ.መ..ድ ዋጋ ባለመስጠት ‹‹አሜሪካ ትቅደም›› የሚል መርሃቸውን እያራመዱ ነው፡፡
አካባቢያዊ ድርጅቶች፣ጥምረቶች፣ሀገራት በተናጠል፣መሪዎች ከየራሳቸው ብሔራዊ እና ቡድናዊ ፍላጎት ተ.መ.ድ ተሐድሶ እንዲያደርግ ጥያቄ ማቅረባቸውን ቀጥለዋል፡፡
የእነዚህ አካላት ሁሉ ግፊት የወቅቱን የተ.መ.ድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዥን ድርጅታቸው ምላሽ መስጠት ግዴታ እንዳለበት አምነው እንዲንቀሳቀሱ አድርጓቸዋል፡፡ ጉቴሬዥ ድርጅታቸው በተሐድሶ ውስጥ እንደሚያልፍ እያሳወቁ ነው፡፡ የተለያዩ በተ.መ.ድ ያሉ ተዋንያንን አሠራር የማዘመን እቅድ አላቸው፡፡ የሚሌኒየሙን የልማት ግቦች ማሳካት እንዲችሉ፣ በየጊዜው እየተለወጠ በሚሄደው የዓለም ሁኔታ ውስጥ በተለይም የሰላም እና ጸጥታ አጀንዳውን በጥብቅ የመያዝ ፍላጎት አሳይተዋል፡፡
ተሐድሶን በተ.መ.ድ ውስጥ ማካሄድ ቀላል ባይሆንም በዚህ ወሳኝ እና አስፈላጊ ጥረት ተ.መ.ድ በዓለም ላይ ተጽእኖ እያሳደሩ ላሉ ጉዳዮች ፈጣን ግብረመልስ የሚሰጥ እና የምድራችንን ፈተናዎች የሚቋቋም ድርጅት ማድረግ ለነገ የሚባል አልሆነም፡፡ ሀገራት የሚሌኒየሙን የልማት ግቦች እንዲያሳኩ ከመርዳት ጎን ለጎን ግጭቶችን አስቀድሞ የመከላከል፣ ስጋቶችን የመቀነስ ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣም ይፈለጋል፡፡
ይሁን እንጂ በዚህ ደረጃ በነጻነት ተራምዶ የሚፈልገውን ለውጥ ለማምጣት ቁልፍ ችግር የሆነበት ጉዳይ አለ፤ ይህም በጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ባላቸው ሀገራት መካከል እያደር እየሰፋ የመጣው ሽኩቻ የድርጅቱን እርምጃ መገደቡ ነው፡፡
ተ.መ.ድ እና የኃያላኑ ፍጥጫ
የተ.መ.ድ ቻርተር በሰኔ 1945፤ 50 በሚሆኑት መስራች ሀገራት ሳንፍራንሲስኮ ላይ ከተመከረበት በኋላ በአራቱ ኃያላን ሀገራት ማለትም ብሪታኒያ፣ ሶቪየት ኅብረት፣ ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ እና ቻይና በወሰዱት መሪነት በአባል ሀገራቱ ተፈርሞ ስራ ላይ ውሏል፡፡ እንደ ኒዎርክ ታይምስ ዘገባ ግን ‹‹እኛ የተባበሩት ሀገራት ዜጎች… ›› ብሎ የሚጀምረው የተ.መ.ድ ቻርተር ዛሬ ላይ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ ድርጅቱ በቻርተሩ መሠረት የሚያስጠብቀው መላውን የተባበሩት 193 ሀገራት ዜጎችን ፍላጎት ሳይሆን የሃያላን መንግሥታትን ጠባብ ሀገራዊ ፍላጎት ነው፡፡
የተ.መ.ድ የመሪዎች ጉባኤ ወሳኝ ውሳኔዎች የሚተላለፉበት፣ ዓለምን ሊለውጥ የሚችል አቅጣጫ የሚያዝበት እንደሚሆን ለሚጠብቁ ለአባል ሀገራቱ ዜጎች እምብዛም ስሜት የሚፈጥር ድርጅት እየሆነ አይደለም፡፡ በአንድ ወቅት የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ የነበሩት ባንኪሙን ቃል አቀባይ የነበረው ስቴፋኔ ዱጃሪክ ‹‹የተ.መ.ድ ጠቅላላ ጉባኤ መክፈቻ ሁልጊዜም የዲፕሎማሲ የዓለም ዋንጫ፣ የዲፕሎማሲ ኦስካር ነው፡፡ ሳቢ የሆነ የፋሽን ሳምንትም ነው›› ብሎ ነበር፡፡ ይህን ስሜት የዓለም ህዝቦች እየተጋሩት ይመስላል፡፡ ለዚህ እንደ ምክንያት ከሚነሡት ጥቂቶቹን መጠቋቆም ይቻላል፡፡
ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት
በመርህ ደረጃ የበለጸገውም ይሁን ደሀው ሀገር በጉባኤው እኩል ድምፅ አላቸው፡፡ አንድ ሀገር አንድ ድምፅ አለው፡፡ ይሁን እንጂ እውነተኛው ሥልጣን ያለው ሌላጋ ነው፡፡ በየዓመቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ የመፍትሔ ሐሳቦች ይበሰራሉ፤ የተምሳሌታዊ ዲፕሎማሲ መድረክ ይሆናል፡፡ ኃያላኑ የሚፈልጓቸው አጀንዳዎች ትኩረት ያገኛሉ፤ በመድረኩም ይነግሳሉ፡፡
የተ.መ.ድ. የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት 15 አባላት አሉት፤ እነዚህ 15 አባላት ከፍተኛ የውሳኔ ድምጽ አላቸው፡፡ በኢራን ላይ እንደተደረገው ከፍተኛ የኢኮኖሚ ማዕቀብ፣ በሊቢያ ላይ እንደተደረገው ወታደራዊ ጣልቃ ገብነትን ዓይነት ውሳኔዎችን ለመወሰን የሚችሉ ናቸው፡፡
በተለይ ቋሚ አባላት የሚባሉት ሀገራት የራሳቸውን እና ሸሪኮቻቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲሉ ያላቸውን ድምፅን በድምፅ የመሻር ሥልጣን ይጠቀማሉ፡፡ ከ1990 ጀምሮ ሲታይ እንኳን አሜሪካ ያላትን ድምፅን በድምፅ የመሻር ሥልጣን 16 ጊዜ የተጠቀመች ሲሆን አብዛኛውን ለእስራኤል ፍልስጤም ግንኙነት ጉዳይ ነው፡፡ ራሺያ ደግሞ 17 ጊዜ የተጠቀመች ሲሆን፤ በአብዛኛው በሶሪያ ጉዳይ ነበር፡፡ ምንም እንኳን ድምፅን በድምፅ በመሻር ሥልጣን ምክንያት የዓለም አቀፍ ሰላም እና ጸጥታ የማይከበርበት ደረጃ ላይ ከተደረሰ የጠቅላላ ጉባኤው ውሳኔ ወሳኝ እንደሚሆን በቻርተሩ ቢቀመጥም በተጨባጭ ግን ሲኬድበት አይታይም፡፡
ሰላምን ከማስጠበቅ አንጻር ተ.መ.ድ የድርሻውን እንዳይወጣ በፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት አባል ሀገራት በተለይም በተደጋጋሚ ከሚታየው በምዕራቡ ዓለም እና በራሺያ መካከል በሚስተዋለው የአቋም መለያየት ምክንያት ያለው የውሳኔ አሰጣጥ ችግር ከፍተኛ ውስንነት አለበት፡፡ በተለይም ቋሚ መቀመጫ ያላቸው አባላት በጉዳዩ ላይ ድርሻ ካላቸው ችግሩን ለመፍታት ለምክር ቤቱ አዳጋች ሲሆንበት ይታያል፡፡ ይሄንን በቀላሉ ማየት የሚቻለው የሶሪያን ጉዳይ በመታዘብ ነው፡፡
ከቋሚ አባላቱ መካከል አሜሪካ ብሪታኒያ እና ፈረንሳይ የሚደግፏቸው ተቃዋሚዎች በራሺያ ከሚደገፈው የበሽር አላአሳድ መንግሥት ጋር የገቡበት ከስድስት ዓመታት ያላነሰ ጦርነት መቋጫ ሳያገኝ የቀረው የቀውሱ ተዋንያን ራሳቸው በመሆናቸው ነው፡፡ በሶሪያ ተደጋጋሚ የጦር ወንጀሎች መፈጸማቸው ቢነገርም ማስቆም ያልተቻለበት ምክንያት ግልጽ ነው፡፡ ተመሳሳይ ሁኔታዎችን በየመን እያስተዋልን ነው፡፡
በተመሳሳይ የቻይና ብርቱ ወዳጅ የሆነችው ሰሜን ኮሪያ የኒኩሌር ጦር መሳሪያ ሙከራዎችን በአደባባይ ስትፈጽም እና የተ.መ.ድ ክልከላ እንደምንም ስትቆጥር የቆየችው የኃያላኑ ድጋፍ በመኖሩ ነው፡፡
የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ ሚና
የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ ተግባር እና ኃላፊነቶችም በቻርተሩ ተድበስብሰው የተቀመጡ እንደሆኑ ይነሳል፡፡ ዋና ጸሐፊው ለየትኛውም ሀገር ምንም ዓይነት አድልዎ ወይም ማጎብደድ ማሳየት እንደሌለባቸው የታወቀ ቢሆንም ድርጅቱ ግን በኃያላኑ ሀገራት ድጎማ እና መልካም ፈቃድ ላይ ጥገኛ ሆኖ መሥራቱን ቀጥሏል፡፡ ጸሐፊው ሲመረጥም በአምስቱ ቋሚ መቀመጫ ባላቸው ሀገራት ምስጢራዊ የድምፅ አሰጣጥ መሠረት ለሁለት አምስት ዓመታት የሚመረጥም በመሆኑ ለእነዚህ ሀገራት ከማጎብደድ ለመውጣት የሚቸገር ነው፡፡
የዩናየትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ ወደር የለሽ ተጽእኖ
በጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ካላቸው ሀገራት መካከል ደግሞ በተለይ ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ በድርጅቱ ውስጥ ያላት ወደር የለሽ ተጽእኖ ሁሌም አነጋጋሪ ነው፡፡ ቻርለስ ቲ ኮል /Charles T. Call/ ፣ዴቪድ ክሮው /David Crow/ እና ጀምስ ሮን /James Ron/ የተባሉ የዓለም አቀፍ ጉዳይ ተመራማሪዎች ባጠኑት ጥናት እንዳስታወቁት፤ አሜሪካ ለድርጅቱ ከምትሰጠው ከፍተኛ አዎንታዊ አስተዋጽኦ የመነጨ አሉታዊ ተጽእኖ ታሳድራለች፡፡ ትራምፕ በዓለም አቀፉ ድርጅት ላይ ከፍተኛ ትችት የሚሰነዝሩ መሪ ሆነዋል፡፡ እርሳቸው ብቻ ሳይሆኑ ብዙዎቹ የአሜሪካን ሪፐብሊካን አሜሪካ ፍላጎቶቿን በተ.መ.ድ እና በዓለም የንግድ ድርጅት ጫና ውስጥ ማስገባት እንደሌለባት ያስባሉ፡፡ ይህ ማለትም ተ.መ.ድ እና የዓለም የንግድ ድርጅት አሜሪካ ጠላት አድርጋ በምታያቸው ሀገራት ጫና ሥር እንዳይወድቅ ስጋት አላቸው፡፡ የአሜሪካን ዜጎችም ብዙዎቹ ተ.መ.ድ የአሜሪካንን ተጽእኖ፣ፍላጎት ወይም ኃይል የሚቀናቀን አድርገው ማሰብ ጀምረዋል፡፡ ስለዚህ አሜሪካ ተ.መ.ድ እንዲታደስ የምትፈልግበት መንገድ ይሄንን ነባር ጥቅሟን ከሚጋፋ አዳዲስ ዝንባሌዎች እንዲርቅ ጫና በማድረግ ላይ የተመሠረተ ሆኖ ይታያል፡፡
ይሄንን ጫና ለማሳደር እንደ ጉልበት የሚጠቀሙት አሜሪካ የድርጅቱን እስከ 22 በመቶ በጀት የምትሸፍን መሆኑን እና ከፍተኛ የሆኑት የድርጅቱ የሥልጣን ቦታዎችን ጥቅሟን በሚያስከብሩ ባለሥልጣናት ለማስያዝ ረቂቅ የሆነውን የራሷን የመረጃ/ስለላ/ተቋማት መጠቀም የምትችል ሀገር መሆኗን ነው፡፡ ከዚህ ፍላጎቷ ለማፈንገጥ ተ.መ.ድ ነጻነቱን ለመጠቀም በሚጥርበት ጊዜ ሁሉ አሜሪካ ከተለያዩ የተ.መ.ድ ስምምነቶች ልትወጣ እንደምትችል በማስፈራራት ላይ ተጠምደዋል፡፡ የአሜሪካን መውጣት ለድርጅቱ ትልቅ ፈተና ይጋረጥበታል፤ በበጀት ቀውስ ይናጣል፤ የሕጋዊነት እጦት ቀውስ ውስጥ ይገባል የሚል እምነት ይዘው አሜሪካኖች እየሠሩ ነው፡፡
የሌሎች አባል ሀገራት ኩርፊያ
የአሜሪካን ወደር የለሽ ተጽእኖ ለሌሎች አባል ሀገራት ምቾት የሚሰጥ አልሆነም፡፡ አዳጊ ሀገሮችም በተ.መ.ድ ላይ ያላቸው እምነት ዝቅተኛ እንዲሆን እያደረገ ነው፡፡ አዳጊ ወይም ደካማ የሚባሉ ሀገራት እና የአሜሪካን ጠላት ተደርገው የሚታሰቡ ሀገራት ይሄንን የአሜሪካንን ጫና ለመቋቋም በተ.መ.ድ ውስጥ ያላቸውን የውሳኔ አቅም ማሳደግ ይፈልጋሉ፡፡ ይህ አዳጊ እና አሜሪካን ጠል ሀገራት አዝማሚያ በተለይም ከትራምፕ ወደ ሥልጣን መምጣት እና በተደጋጋሚ የሚያሰሙት የ‹‹አሜሪካን ትቅደም “America First” ›› መፈክር ስጋታቸውን ጨምሯል፡፡ ሌላው ቀርቶ አፍቃሪ አሜሪካን የሚባሉ ሀገራትም ወደ እነዚህ ጎራ የማዘንበል ሁኔታ ታይቶባቸዋል፡፡
በአጠቃላይ ሲታይም በደቡባዊ ንፍቀ ክብብ ያሉ ሰዎች ተ.መ.ድ እና አሜሪካ የጋራ አጀንዳ እንደሚያራምዱ ያምናሉ፡፡ ለአሜሪካ የሚሆነው በጎ ነገር ሁሉ ለተ.መ.ድ፣ ለተመድ የሆነው በጎ ነገር ሁሉ ለአሜሪካ እንደሆነ ያምናሉ፡፡
የዚህ በአሜሪካን እና በተ.መ.ድ መካከል ባለው ግንኙነት ስጋት እና ጥርጣሬ ያላቸው ወገኖች መነሻቸው ለአሜሪካን ባለስልጣናት ያላቸው አተያይ /ዝንባሌ/ በተ.መ.ድ ላይ ተጽእኖ ማሳደሩ ነው፡፡ ይህ በተቃራኒው መሆን ሲገባው የነገሮቹ መዛባት ከተ.መ.ድ ይልቅ አሜሪካን ትኩረት የምትስብ እና በዓለም መድረክ ተለይታ የምትታይ ሀገር አድርጓታል፡፡ ይህ ተሻግሮ ስጋት እና ጥርጣሬዎችን በአውሮፓ ህብረት እና በዓለም አቀፉ ገንዘብ ድርጅት ላይም ይሄዳል፡፡ ከዚያ አልፎ አካባቢያዊ በሆኑ ለተ.መ.ድ ተጠሪ በሆኑ ሰብአዊ መብት ድርጅቶችም ላይ እንዲሁ ጥርጣሬ አለ፡፡
ከዚያም አልፎ ተ.መ.ድ የአሜሪካ የጣልቃ ገብነት መሳሪያ እየሆነ ነው የሚል ሐሳብም አለ፡፡ ለምሳሌም በአፍጋኒስታን እና በኢራቅ ሽብርን ለማጥፋት በሚል የተሰማራው የተ.መ.ድ ሚና በደቡብ ንፍቀ ክብብ ባለው በአብዛኛው ማኅበረሰብ የቅኝ ግዛት ዘይቤ ያለበት ነው የሚል አስተሳሰብ ተይዞበታል፡፡ ስለዚህም በአሜሪካ እና በተ.መ.ድ ግንኙነት ላይ ያለውን ጥርጣሬ የሚያጎላው ነው፡፡
በርካታ ሀገራት ተ.መ.ድ እንዲያደርግ የሚፈልጉት ተሐድሶ ከዚህ ከአሜሪካን ብርቱ ተጽእኖ በሚያወጣው ደረጃ ነው፡፡ የአሜሪካን አክራሪ/ወግ አጥባቂ/ ፖለቲከኞች ዘንድ ያለውን ተ.መ.ድን የመተቸት ዝንባሌ ተቀባይነት እንዲያጣ ያደርገዋል፡፡ ተ.መ.ድ የአሜሪካንን ጥቅም እያስከበረ እንጂ እያዳከመ አይደለም የሚለው የገዘፈ አመለካከት ነው፡፡ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ትራምፕ በመስከረም 19 የድርጅቱ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ያሰሙት የሮሮ ንግግርም አሁንም ድርጅቱን ከጥርጣሬ ነጻ ሆኖ የሀገራቸውን ፍላጎት በማስጠበቅ እንዲቀጥል ሽፋን ለመስጠት ሕጋዊነቱን ለማጽናት የተሰነዘረ እንጂ የሌሎችን እምነት የሚቀይር አይደለም የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡
የተ.መ.ድ እና የአሜሪካን ውዝግብ መገለጫዎች
የኢራን የኒኩሌር ኃይል ስምምነት
እንደ Time መጽሄት ዘገባ ተ.መ.ድ ከአሜሪካ ጋር ከተፋጠጠባቸው ወሳኝ ጉዳዮች አንዱ የኢራን የኒኩሌር ስምምነት ነው፡፡ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ትራምፕ ‹‹ስምምነቱ ለአሜሪካ ስድብ ነው›› ሲሉ አቃለውታል፡፡ ኢራን ለአሜሪካ አስጊ ኃይል ነች፤ ኢራን ከኢኮኖሚ ማእቀብ ልትሻገር የምትችል ሀገር ልትሆን እንደምትችል ታስባለች፡፡ ኢራናውያን በመካከለኛው ምሥራቅ ካሉ ህዝቦች ሁሉ እጅግ በእውቀት በክህሎት የላቁ ናቸው፡፡ ኢራን የተጣለባት ማእቀብ ግን ይሄንን እምቅ አቅም በምትፈልገው ልክ ለልህቀት እንዳትጠቀም ጫና አድርጎባት ቆይቷል፡፡ ከ2012 እስከ 2014 ድረስ ብቻ እንኳን ማእቀቡ ከአጠቃላይ የምርት እድገቷ 4.5 በመቶ ያህሉን ቀንሶባታል፡፡ በስምምነቱ መሰረት ማዕቀቡ መነሳቱ ኢራንን ወደ ኒኩሌር ኃይል ልማት እንዳትመለስ የሚያደርጋት ቢሆንም ከኢኮኖሚው ጫና ግን ነጻ አውጥቷታል፡፡ አሜሪካ ስምምነቱን ባትቀበልም ተ.መ.ድ ግን ተጠብቆ እንዲቆይ እየወተወተ ነው፡፡ አሜሪካ ከስምምነቱ እንደወጣች ብታውጅም ሌሎች የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት አባላት እና የተ.መ.ድ ማኅበረሰብ እንደጸኑ ነው፡፡ ኢራንም በስምምነቱ የጸናች ሲሆን የአሜሪካን ሕግ አፍራሽ ሆኖ መቆጠርም እንደ ሌላ ትርፍ እየወሰደችው ነው፡፡ የተ.መ.ድ አቋም ግን ከአሜሪከ የሚያርፍበት ጫናና ትችት ግን የዋዛ አልሆነም፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይም
የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይም ተ.መ.ድን ከአሜሪካን ጋር እንካ ሰላንትያ ውስጥ ያስገባው አንዱ ጉዳይ ነው፡፡ አሜሪካ የ1990 ኪዮቶን ስምምነት ያደጉ ሀገራት የካርቦን ልቀት መጠናቸውን እንዲወስኑ የሚያደርግ ይዘት ያለበትን ስምምነት በማጣጣሏ ስምምነቱ ፍሬማ የመሆን ዕድሉን አዳክሟል፡፡
በስምምነቱ መሰረት ሀገራት የካርቦን ልቀት ምጣኔያቸውን እንዲያሻሽሉ የተቀመጡ ስምምነቶች በኃያላን ሀገራቱ መገፋታቸው ለተ.መ.ድ ራስ ምታት ሆኗል፡፡ አሜሪካ ከስምምነቱ እንደምትወጣ ማስታወቋ ለድርጅቱ መርዶ ነበር፡፡ በየጊዜው እየተመዘገበ የመጣው የዓለማችን ከፍተኛ የሙቀት መጠን በተከታታይ መመዝገቡ፣ ከፖርቶሪኮ እስከ ሴራሊዎን የደረሱ የተፈጥሮ አደጋዎች እና ውድመቶች ለችግሩ እንደ ማሳያ እያቀረቡ እንደ ማሳመኛ ሆነው በድርጅቱ መቅረብ እንዳለባቸው ይታመናል፡፡ አሜሪካ የያዘችውን አቋም ተቃውመው ሀገራት በስምምነቱ በጽናት ቆመው ለመጓዝ የያዙትን አቋም ሳይለውጡ ማስቀጠል የተ.መ.ድ ወሳኝ የቤት ሥራ ነው፡፡ ስለዚህ የዓለም ሙቀት የመጨመር ጉዳይ ለተ.መ.ድ ወሳኝ ተግዳሮት ነው፡፡ የትራምፕ ከፓሪሱ ስምምነት መውጣት ከ1880 ጀምሮ ሲታሰብ አሁን ላይ የዓለም ሙቀት መጠን በ1.7 ዲግሪ ፋራናይት የጨመረ ሲሆን በኃያላኑ ዝምታ ምክንያት ይህ ዕድገት እስከ 3.6 ዲግሪ ፋራናይት ከደረሰ ሊቀለበስ የማይችልበት ደረጃ ሊደርስ እንደሚችል ጠበብቶች ያስረዳሉ፡፡
የኮሪያ ልሳነ ምድር ውጥረት
ለኮሪያ ልሳነ ምድር ውጥረት የተቀመጠው መፍትሔ አስተማማኝ ደረጃ ላይ የደረሰ አይደለም፡፡ የአሜሪካው ትራምፕ እና ኪም ጆንግ ኡን በሲንጋፖር ከተገናኙ በኋላ ጉዳዩ የረገበ ቢመስልም በጉዳዩ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው ቻይና እና ደቡብ ኮሪያ ፍላጎት ምን ያህል ታርቆ ዘላቂ መፍትሔ መምጣት ይችላል የሚለው ብዙዎችን የሚያሳስብ እና ለተ.መ.ድ ከፍተኛ ፈተና የሆነ ጉዳይ ነው፡፡ ችግሩ ለተ.መ.ድ ፈታኝ የሚሆነው የእነዚህ ከጉዳዩ ጀርባ ያሉ ኃያላን ሀገራት ተቃራኒ /የሚጋጩ ፍላጎቶች የሚታረቁበትን ነጥብ መድረስ ነው፡፡ ተ.መ.ድ ለሀገራቱ ፍላጎት ዝቅተኛ የጋራ አካፋይ የሆነ ሃሳብ ማቅረብ እና ማስማማት ይችላል ወይ የሚለው ነው፡፡ ችግሩ ይህ የዝቅተኛ የጋራ አካፋይ የሆነ ሃሳብ መምጣት ወይም ማስማማት አለመቻሉ ነው፡፡
ተ.መ.ድ ያለበት የኃላፊነት ጫና
ተ.መ.ድ ለረጅም ጊዜያት በቆየው አገልግሎቱ ውስጥ ስኬታማ የሆነባቸው ጉዳዮች ያሉትን ያህል ከቁመናው በላይ የተሸከማቸው ጫናዎችም አሉበት፡፡ ይህ ሁኔታ ግን ድርጅቱን ሊያራምድ እንደማይችል የሚተቹ ወገኖች አሉ፡፡ በአንድ ወቅት የቀድሞው የተ.መ.ድ ዋና ጸሐፊ የነበሩት ዳግ ሃመርስጆልድ ‹‹ተ.መ.ድ የተፈጠረው ሰዎችን ወደ ገነት ሊወስድ/ሊመራ አይደለም፤ ሰዎችን ከሲኦል ሊያድን እንጂ›› ብለው ነበር፡፡ ቀለል ባለ መንገድ ሲቀመጥ ተ.መ.ድ የሚሻለው ዓለም ከችግሮች ጋር ተቋቁሞ እንዴት እንደሚዘለቅ መርዳት እንጂ ችግሮችን ማጥፋት አይደለም የሚል ዓይነት ነው፡፡ በእርግጥም ተ.መ.ድ በሚያደርገው ተሐድሶ ውስጥ ሊፈታቸው የሚችሉ እና የማይችሉ ችግሮች መኖራቸውን ለመለየት እንደሚገደድ ያመለክታል፡፡
ድርጅቱ በአሁን ጊዜ በዋናነት ከያዛቸው ተልእኮዎች አንዱ ተጋነው ታቅደዋል የሚባሉትን የሚሌኒየሙን የልማት ግቦች የማስፈጸም ተልእኮ ነው፡፡ እ.አ.አ በ2030 የተሳኩ እንዲሆኑ ለማድረግ ድርጅቱ በሩጫ ውስጥ ነው፡፡ አባል ሀገራቱን ግን የሚያረካ ሆኖ አልተገኘም፡፡ እነዚህ ግቦች ለዓለማችን ችግሮች ሁነኛ መፍትሔ ለማምጣት ወሳኝ ናቸው የሚባሉ ናቸው፡፡ በተለይ ቁልፍ የአለማችን ችግሮች የሚባሉትን የድህነት ቅነሳ፣ የአካባቢ ተፈጥሮአዊ ደህንነት ቀጣይነት፣ የአቃፊነት/ inclusiveness / ጉዳይ ልዩ ትኩረት የተሰጣቸው ናቸው፡፡ የህጻናት ሞት ቅነሳ፣ እና አደገኛ ፖሊዮን የመሰሉ በሽታዎችን ከአለማችን የማጥፋት ዘመቻዎች ርብርብ እየተደረገባቸው ያሉ ናቸው፡፡
በታዳጊ ሀገሮች 30 በመቶ የሚሆኑት ልጆች /እስከ 600 ሚሊዮን/ በቀን ከአንድ ዶላር ባነሰ ይኖራሉ፡፡ አስፈላጊ አገልግሎቶች እና ቁሶችን በጽኑ ማጣት ሰዎችን ሁሉ የሚጎዳ ነው፡፡ በልጆች ላይ ሲከሰት ደግሞ እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡ ከህልውና ስጋት፣ ትምህርት፣ የምግብ እና ጤና አቅርቦት እጥረት፣ ከጉዳት እና ብዝበዛ የማዳን ድርሻ አለው፡፡ በዚህ ደግሞ አንዱ የዓለም አካባቢ ከሌላው በባሰ ሁኔታ ውስጥ ሊቆይ ይችላል፡፡ በአንድ ሀገር ውስጥ እንኳን ከዚህ አንጻር ልዩ ልዩነት ይታያል፡፡ በገጠር እና በከተሞችም ልጆች ሰፊ ልዩነት ይታያል፡፡ በሴቶች እና በወንዶች መካከልም እንደዚያው፡፡
ተ.መ.ድ በቀሪዎቹ 12 ዓመታት ቀሪውን ስራ አጠናቆ ስኬታማ ለመሆን የእርምጃውን ፍጥነት በእጅጉ መጨመር ይጠይቃል፡፡ የሲቪክ ተቋማትን የግሉን ሴክተር በስፋት ማሳተፍ ካልተቻለ ለተ.መ.ድ ፈተናው ቀላል አይሆንም፡፡ ዓለም አቀፍ እና አካባቢያዊ ትብብሮች፣ መሰረታዊ መረጃዎችን ማደራጀት እና እርምጃን እየለኩ/እየመዘኑ/ መጓዝ፣ ባደጉትም በማደግ ላይ ባሉ ሀገራትም ቀጣይነት ያለው ተግባር መኖር ወሳኝ ስልቶች ናቸው፡፡
ሌላው ከባድ የተ.መ.ድ ፈተና ሆኖ ያለው ከላይ አስቀድመን እንደጠቀስነው የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ነው፡፡ በፓሪስ የተደረገውን ስምምነት አስጠብቆ ማስቀጠል የተ.መ.ድ ፈተና ነው፡፡ ኃያላን ሀገራቱን ከማሳመን በተጨማሪ በጉዳዩ ላይ ምክክር በማድረግ ጫና እንዲፈጥሩ የሚፈለጉት የአካባቢ መሪዎች፣ ሳይንቲስቶች፣ ተማሪዎች፣ ለትርፍ ያልተቋቋሙ ድርጅቶች፣ የቢዝነስ ድርጅቶች ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡት የማድረግ ስራም የተ.መ.ድ ድርሻ ነው፡፡ ሀገራት የአረንጓዴ/ታዳሽ/ የኃይል ምንጮችን እንዲያስፋፉ፣ ሰፊ የካርበን ንግድ ጅማሮ እንዲያሳዩ ማበረታታት ያስፈልገዋል፡፡
የተ.መ.ድ ተግባራት ሌላው ያለባቸው ፈተና የበጀት ውስንነት ነው፡፡ በመንግሥታት ድጋፍ እና ትብብር ብቻ ይቃናል ማለት የማይቻል ነው፡፡ የፋይናንስ ኢንዱስትሪውን እና የተለያዩ ኩባንያዎችን ጨምሮ የግሉ ሴክተር አስፈላጊውን ሚና መጫወት ካልቻለ ብዙ ትሪሊዮኖችን የሚፈልጉት የሚሌኒየም የልማት ግቦችም ሆኑ የፓሪሱ የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ላይ የተደረሰው ስምምነት ሥራ እውን ለማድረግ ሳንካ ሊገጥመው ይችላል፡፡ ለዚህም ተ.መ.ድ የሚያዘጋጃቸው የኢንቨስተሮች ጉባኤያት አቅሙን ለማሳደግ ሳያባክን ሊጠቀምባቸው የሚገቡ ናቸው፡፡
ሌላው የተ.መ.ድ ፈተና እጅግ እየተባባሰ በመጣው የአለማችን የመጤ ጠልነት፣ ግጭት እና ጦርነቶች ውስጥ እየፈላ ያለውን የፍልሰተኞች ጉዳይ ነው፡፡ ለስደተኞቹ ድምጽ በመሆን፣ ሰላም እና ደህንነታቸውን የማስጠበቅ፣ ድጋፍ እና ክብካቤ የማቅረብ መብቶቻቸውን የማስጠበቅ ፈተና ነው፡፡ ፍልሰተኞችን ለጤና፣ ለትምህርት፣ ለአስፈላጊ የኑሮ አቅርቦቶች እድል የማስፋት ተቀባይ መንግሥታት ስደተኞችን እንዲያስጠጉ እና በአግባቡ እንዲቀበሉ በቀላሉ ጫና የማሳደር ፈተና ነው፡፡
ማጠቃለያ
የተ.መ.ድ ተሐድሶ የወደፊቱ የድርጅቱ ጉዞ ወይም እጣ ፈንታም ይወስናል፡፡ ይህ ደግሞ በድርጅቱ አባላት ጥንካሬ፣ በባለሥልጣናቱ ቁርጠኝነት ላይ የወደቀ ነው፡፡ በጥር 2018 ወደ ሥልጣን የመጡት ጉቴሬዥ ለ72 አመታት ያህል ሲንከባለሉ የመጡ እና አዲስ የተወለዱ የድርጅቱን ተግዳሮቶች ተቋቁመው የተ.መ.ድን አስፈላጊነት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማስገንዘብ የማይቀር የቤት ሥራቸው ነው፡፡ ተደቅነው ያሉ ወሳኝ ፈታኝ ጥያቄዎችም ከፊታቸው አሉ፡፡
ከዚሁ አንጻር ተ.መ.ድ ሊያደርግ ባሰበው ተሐድሶ ውስጥ የሁሉም አባል ሀገራት ዜጎች ጥያቄዎችን የሚመልስ ቁመና ላይ መገኘት አለበት፡፡ ተ.መ.ድ በሰብአዊ መብት አለም አቀፍ ህጎችን የሚተላለፉ ሀገራት ላይ እርምጃ ለመውሰድ ይችላል? አምስቱን ቋሚ መቀመጫ ያላቸውን ሀገራትስ ከራሳቸው ጠባብ ፍላጎት ባሻገር አይተው የጦርነትን ስቃይ ለማስቆም ይሰራሉ? የሰላም ማስከበር ተልእኮዎችስ ሰላማዊ ዜጎችን ከለላ ለመስጠት በሚያስችል ቁመና ላይ እንዲገኙ ማድረግ ይችላል? ሀገራት የካርቦን ልቀት ምጣኔያቸውን ለመቀነስ የገቡትን ቃል እንዲጠብቁ ማሳመን ይችላል? ከአየር ንብረት ለውጡ መዘዝ የሚሰቃዩ ወገኖችንስ መርዳት ይቻለዋል? በአጠቃላይ ተ.መ.ድ የተመሰረተበትን እና ኃላፊነት የወሰደበትን ዓለምን የተሻለ እና ሰላማዊ እንዲሆን የመሥራት ኃላፊነቱን መወጣት ይችላል? የሚሉት ወሳኝ ጥያቄዎች ናቸው፡፡
በመሆኑም ፖርቹጋላዊው ጉቴሬዥ የድርጅቱን የጠፋ ስም በዓለም መድረክ አድሰው ለመውጣት ከአሁኑ ጠንካራ አቋም ይዘው መራመድ ይገባቸዋል፡፡ ዋና ጸሐፊው ድርጅቱን ማሻሻል ከፈለጉ ውሳኔዎቹን፣ ስምምነቶቹን፣ የመፍትሔ እርምጃዎችን ለመተግበር የሚያስችለው እውነተኛ ሥልጣን ባለቤት መሆን ይገባዋል፡፡ ለድርጅቱ ወሳኝ ሹመቶች ዴሞክራሲያዊ በሆነና በግልጽነት በሚፈጸሙ ምልመላዎች ሰዎችን ማጨት ይገባዋል፡፡ ድምፅን በድምፅ በመሻር ሥልጣን ውስጥ የሚታዩ ኢ-ፍትሐዊ አካሄዶች ማብቃት አለባቸው፡፡ ድርጅቱ ‹‹የሰዎች መሰብሰቢያ፣ ማውሪያ እና ጥሩ ጊዜ ማሳለፊያ ክለብ ነው›› በማለት እንደተሳለቁበት እንደ ትራምፕ ዓይነቱን መሪ ተገዳድሮ፣ የአሜሪካን እና የራሺያን ተላላፊነት ተቋቁሞ የድርጅቱን ህልውናና እና አቅም ለማስጠበቅ ካልቻለ ድርጅቱ በአሮጌነቱ ይቀጥላል፡፡ ከዚህ ቀውስ መውጣት የሚችለው ድርጅቱን የምር ማደስ እና አባላቱ ለድርጅቱ ትኩረት፣ ድጋፍ እና ሥልጣን እንዲሰጡ በማድረግ ነው፡፡
ማለደ ዋስይሁን
ዘመን መፅሄት ጥቅምት 2011