አዲስ አበባ፡- መገናኛ ብዙኃን ለሰላም ግንባታ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ከተፈለገ አሰራራቸው በሰላም ጋዜጠኝነት መርህ የተቃኘ ሊሆን እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን መምህር ዶክተር አደም ጫኔ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤ በተለይ አሁን ባለው የኢትዮጵያ ሁኔታ መገናኛ ብዙኃን ሰላምን ለማስፈን ለሚደረገው ጥረት አወንታዊ አስተዋጽኦ ለማበርከት ግጭቶችን ከሚያቀጣጥሉ አዘጋገቦች መቆጠብና ሥራቸውንም በኃላፊነት ስሜት ሊያከናውኑ ይገባል፡፡ ፕሮግራሞችንና ጽሑፎችን ሲያዘጋጁና ሲያቀርቡ ከሚጠቀሟቸው ቃላት ጀምሮ እስከ አቀራረቡ ድረስ መጠንቀቅ ይገባቸዋል።
ግጭትና መፈናቀል በስፋት በሚታይባቸው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት «የመገናኛ ብዙኃን ሚና ምን መሆን አለበት?» የሚለው ጉዳይ ወሳኝና መገናኛ ብዙኃን እንደ ተቋም፤ ጋዜጠኞችም እንደ ባለሙያ በየዕለት ሥራቸው ላይ ሊያስቡት የሚገባ ትልቅ አጀንዳ መሆን አለበት፡፡
እንደእርሳቸው ገለፃ፤ የመገናኛ ብዙኃን ነፃነት ኃላፊነትንም ጭምር ያካተተ በመሆኑ ጋዜጠኛውም ሆነ ተቋሙ ማኅበራዊ ኃላፊነት እንዳለባቸው ተገንዝበውና በሰላም ጋዜጠኝነት ላይ ተመርኩዘው በመስራት ሰላም ማስፈንና በዘርፉ ብሎም በአጠቃላይ የአገሪቱ ፖለቲካ ላይ የታየውን ለውጥ ለማስቀጠል መንቀሳቀስ አለባቸው፡፡
«እውነትን መደበቅ ሰላም አያሰፍንም፤ እንዲያውም ችግሩን ያባብሰዋል» የሚሉት ዶክተር አደም፣ መገናኛ ብዙኃን ችግሮች ሲፈጠሩ እንዳላዩና እንዳልሰሙ ሆነው ከማለፍ ይልቅ ሚዛናዊ በሆነ መልኩ፤ በሰላም ጋዜጠኝነት ተቃኝተውና መዳረሻቸውን ሰላም አድርገው መረጃ ለሕብረተሰቡ ማድረስ እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡ ፡
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን በመንታ መንገድ ላይ እንደሚገኙ የጠቆሙት ዶክተር አደም፤ የውይይትና የክርክር መድረኮችን፤ እንዲሁም በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ሳይንሳዊ ትንታኔዎችን በማቅረብ ሙያውን መሰረት አድርገው ለመስራት ጥረት የሚያደርጉ መገናኛ ብዙኃን እንዳሉ ሁሉ፤ ዋልታ ረገጥ የሆነ አካሄድን እየተከተሉ ያሉ መገናኛ ብዙኃንም እንዳሉ ገልፀዋል፡፡
«ከሰላም ጋዜጠኝነት መርሆዎች አንዱ ‹ድምፅ ለሌላቸው ድምፅ መሆን› ነው፡፡ ችግሮች የሚዘገቡበት መንገድ ግጭትን የሚያባብስ ሳይሆን በውይይትና በንግግር ላይ ያተኮረ፤ እንዲሁም የሁሉንም ወገኖች ሃሳቦች ያካተተ መሆን ይኖርበታል» ብለዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም፤ መገናኛ ብዙኃን ራሳቸውን ነፃና ገለልተኛ ተቋም አድርገው ቢያጠናክሩ የራሱ የሆነ ዓላማ ያለው ማንኛውም አካል ወደፈለገው የፖለቲካ መስመር እንዳይጎትታቸውና ገለልተኛ ሆነው ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት እንደሚያስችላቸውም ዶክተር አደም አስረድተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 23/2011
በአንተነህ ቸሬ