አዳማ፤ የኦሮሚያ እና የሱማሌ ክልል ህዝቦች በሰላምና በፍቅር አብረው ለመኖርና ለመስራት ግንኙነታቸውን ማጠናከር በሚችሉባቸው ሁኔታ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚመክር የህዝብ ለህዝብ መድረክ በኦሮሚያ ክልል በአዳማ ከተማ በመካሄድ ላይ ነው፡፡
በምክክር መድረኩ፤ የሁለቱ ክልል ወንድማማች ህዝቦች የነበራቸውን መልካም ግንኙነት በማጉላት ቀጣይ የጋራ ስኬትና ጉዞን ማስቀጠል በሚችሉበት ሁኔታ እንደሚመክር ይጠበቃል፡፡
ችግሮችን በባህላዊ የችግር ማስወገጃ እሴቶች መፍታት፣ በሁለቱ ክልል ህዝቦች ወሰን አካባቢ ሰላም ማረጋገጥ፣ የዜጎችን የመዘዋወርና የመስራት መብቶችን ማስከበር፣ ጥቂት ፖለቲከኞች በሚፈጥሩት አጀንዳ እየተከሰተ ያለውን የእርስ በእርስ መጠራጠር በማስወገድ፣ በመከባበርና በመደጋገፍ ስኬትን እንዲፋጠን በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ እንደሚወያዩ ይጠበቃል፡፡
ከክልሉ የኮሙኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በሁለቱ ክልሎች ባለስልጣናትና የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል የሚካሄደው የህዝብ ለህዝብ መድረክ የሁለቱ ክልል ህዝቦች እንደ ቀድሞው በሰላምና በፍቅር ግንኙነታቸው የሚጠናከርበት ሁኔታ ላይ ያተኩራል፡፡
ሁለቱ ህዝቦች ረጅም ወሰን የሚካለሉ በመሆኑም በመካከላቸው ያለውን መልካም ግንኙነት በሚጠናከርበት ሁኔታ ላይ እንደሚመክሩም ነው የተገለጸው፡፡ ከዚህ ቀደም የተከሰቱ ችግሮች የሁለቱ ህዝቦች አጀንዳ አለመሆናቸውንና በተፈጠረው ችግር ማዘናቸውም ተገልጿል፡፡
ወደፊትም ተመሳሳይ ችግር እንዳይከሰት ጥንቃቄ ማድረግ ይገባልም ብለዋል፡፡ እንዲህ አይነት ድርጊት እንዲፈጸም የሚጥሩ ሃይሎችን በማጋለጥ ለመተባበር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ምክክር እንደሚደረግም ነው የተብራራው፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 23/2011
በአጎናፍር ገዛኸኝ