አዲስ አበባ፡– በአዲስ አበባ በመንገድ ሃብቶች ላይ ጉዳት የሚያደርሱ አካላትን ተጠያቂ ማድረግ የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ አለመኖሩ የመንገድ ሀብቶች ለጉዳት እየተዳረጉ መሆናቸውን የከተማዋ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
የባለስልጣኑ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ጥዑማይ ወልደገብርኤል በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤ ለመንገድ ሀብቶች መጎዳት ከፍተኛውን ድርሻ የሚወስዱት የተሽከርካሪ ግጭቶች ናቸው፡፡
ዳይሬክተሩ በተያዘው በጀት ዓመት ባለፉት ሰባት ወራት ውስጥ በቀለበት መንገድ ላይና
ከቀለበት መንገድ ውጪ በደረሱ 272 የግጭት አደጋዎች የመንገድ ዳር መብራቶች፣ የትራፊክ ምልክቶች፣ የአቅጣጫና የርቀት አመልካች ሰሌዳዎች፣ የእግረኛ መከላከያ አጥሮች፣ የመንገድ ማካፈያ ግንቦች እንዲሁም የውሃ መውረጃ ቱቦዎችና ክዳኖች ላይ ጉዳት መድረሱን ለአብነት ጠቅሰዋል::
በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በኩል ኃላፊነት ወስዶ የመንገዶቹን ደህንነት የሚጠብቅና ጉዳት ሲደርስም ተከታትሎ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ የሚያደርግ አካልና የህግ አሰራር እንደሌለም ጠቅሰው፣ ብቻ 4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር የሚገመት ጉዳት በመንገዶችና በመንገድ አካላት ላይ መድረሱን ጠቅሰዋል፡፡
በመንገድ ሀብቶች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት መልሶ ለመጠገን ጉዳት አድራሾች ተመጣጣኝ የጉዳት ካሳ እንዲከፍሉ የሚገደዱ መሆናቸውን ዳይሬክተሩ ተናግረው፣በመረጃ በተደገፈ መልኩ ተጠያቂ የሚሆኑበት የህግ አሰራር ግን እንደሌለ አስታውቀዋል፡፡ በዚህም የተነሳ የሚፈለገውን ያህል የጉዳት ካሳ ክፍያ መቀበል እንዳልተቻለ ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል፡፡ ለመንገድ ሃብት መልሶ ጥገና የሚደረገው ወጪም ከሚከፈለው ካሳ በላይ መሆኑን የሚገልጹት ዳይሬክተሩ፣ በተያዘው በጀት አመት በመጀመሪያ ግማሽ ዓመት ብቻ በመንገድ ሀብት ላይ ከደረሰው የጉዳት ካሳ ክፍያ መገኘት ከነበረበት 4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ውስጥ ማስመለስ የተቻለው 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ብቻ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
አቶ ጥኡማይ እንዳሉት፤ በመንገድ ሀብት ላይ ጉዳት የሚያደርሱ አካላትን ተጠያቂ የሚያደርጉ ህጎች እንዲኖሩና ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የመንገዶችና የመንገድ አካላትን በአግባቡ የሚያስተዳድርበት አቅጣጫ እያየ ነው፡፡ የመንገድ ሀብት አስተዳደሮችን በአምስት ቢሮዎች በማዋቀርና ቢሮዎቹ የራሳቸውን የህግ ባለሙያ ቀጥረው በመንገድ ሀብት ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን ተከታትለው እንዲያስፈፅሙና ክስ መስርተው ተገቢውን ካሳ እንዲቀበሉ ለማድረግ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ይህ አሰራር በደንብና አዋጅ መደገፍ የሚኖርበት ሲሆን፣ ተግባርና ኃላፊነቱም ለባለስልጣን መስሪያ ቤቱ መሰጠት ይኖርበታል፡፡
በመንገድ ሀብቶች ላይ በተለይም በመንገድ ዳር መብራቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተሉ ካሉ ምክንያቶች ውስጥ የስርቆት ወንጀሎች እንደሚጠቀሱም ዳይሬክተሩ አያይዘው አስታውቀዋል፡፡ ይህን ለመቆጣጠር ህብረተሰቡ በየአካባቢው ከሚገኙ የፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር ለመንገድ ሀብቶች ጥበቃ ሊያደርግላቸው እንደሚገባም አስገንዝበዋል። የስርቆት ወንጀሎች ሲያጋጥሙም በነፃ የስልክ መስመር 8267 ላይ በመደወል መጠቆም እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22/2011
በአስናቀ ፀጋዬ