አዲስ አበባ፡- የአዲስ አዳማን የክፍያ መንገድ ሙሉ ለሙሉ እንዲሁም በቀጣይ የሚገነቡ የክፍያ መንገዶችን የማስተዳደር እና የመጠገን አቅሙን ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ አስታወቀ። ባለፉት አራት ዓመታት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ገለጸ።
የኢንተርፕራይዙ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዓቢይ ወረታው በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ኢንተርፕራይዙ የአዲስ አዳማ የክፍያ መንገድን እያስተዳደረ ሲሆን፣ መንገዱ ወደ ሥራ ከገባ ከ2007 ዓ.ም አንስቶም አንድ ቢሊዮን ብር መሰብሰብ ችሏል፡፡
የመንገዱ ተፈላጊነት እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰው፣ የሚያስተናግዳቸው ተሽከርካሪዎች ብዛትም ወደ ሥራ ሲገባ ከነበረው 8 ሺ ወደ 24 ሺ ማደጉንም ተናግረዋል፡፡ ይህ አሀዝ በቀጣይም እንደሚጨምር የሚጠበቅ መሆኑን ጠቁመዋል።
ምክትል ሥራ አስኪያጁ የድሬዳዋ ደወሌ መንገድ በፍጥነት መንገድ ደረጃ እንዳልተገነባ ጠቅሰው፣ የክፍያ መንገድ ሆኖ እንዲያገልግል እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይህን በቅርቡ ወደ ሥራ የሚገባ መንገድ ለማስተዳደርም ኢንተርፕራይዙ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የሞጆ ሀዋሳ እና የአዳማ አዋሽና የፍጥነት መንገዶች በክፍያ የሚሆኑበት ሁኔታ እንደሚኖር ጠቁመው፣ኢንተርፕራይዙ እነዚህን መንገዶች የማስተዳደር አቅሙን ለመገንባት በውስጥ አቅም እየተዘጋጀ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
እንደ ምክትል ሥራ አስኪያጁ ገለጻ፤ከዓለም ባንክ በተገኘ ብድር ተቋማዊ አቅምን የማሳደግ ሥራ ለመሥራት የአማካሪ ቅጥር ለማካሄድ ኢንተርፕራይዙ ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ጋር በመተባበር እየሰራ ነው። በዚህም በሚቀጥሉት ዓመታት አሁን ያሉትን የሥራ ክፍሎቹን እና ወደፊት የሚመጡትንም የክፍያ መንገዶች ለማስተዳደር የሚያስችል ተቋማዊ አቅም ይኖረዋል።
የኢንተርፕራይዙ ዋና ተግባር መንገድ ማስተዳደር ብቻ እንዳልሆነም አመልክተው፣መጠገንም ሌላው ሥራው መሆኑን አስታውቀዋል።የአዲስ አዳማ መንገድ እስከ አሁን በጥራት ዋስትና (ዋራንቲ ፔሬድ) ውስጥ መሆኑን ተናግረው፣ የታዩ ክፍተቶችን ተቋራጩ እያስተካከለ መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ ምክትል ሥራ አስኪያጁ ገለጻ፤ ከአንድ ዓመት በኋላ ይህ የተቋራጩ ሥራ የሚያበቃ ስለሚሆን፣ ኢንተርፕራይዙ የጥገና ሥራውን ለማካሄድ ክህሎቱን ማስፋት ይኖርበታል። ለዚህም የጥገና ስትራቴጂ እያዘጋጀ ይገኛል። ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮም ሙሉ ለሙሉ መንገዱን የማስተዳደር እንዲሁም የመጠገን፣ የማስጠገንም አቅም ለማዳበር አቅዶ እየሰራ ይገኛል።
‹‹ጥገናውን እንዴት እንመራዋለን የሚለውን ይዘን እየሰራን ነው፡፡ የአቅም ግንባታችን አንድ ክፍል የጥገና አቅምን ማሳደግ ነው።›› ሲሉ ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22/2011
በኃይለማርያም ወንድሙ