አዲስ አበባ፡- በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ግቢ በ40 ሚሊዮን ዩሮ ወጪ ለሚገነባው የልብ ህክምና ማዕከል የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ።
የጤና ሚኒስትሩ ዶክተር አሚን አማን የመሰረት ድንጋዩን በኢትዮጵያ ከኔዘርላንድ አምባሳደር ቬንጌት ቫን ሉደርስከት ጋር በመሆን ባስቀመጡበት ወቅት እንዳሉት፤ ህንጻው የሚገነባው በኢትዮጵያ መንግሥት እና ኔዘርላንድ መንግሥት ትብብር ነው። ህንጻው ባለሰባት ወለል ሲሆን፣ የወጪውን ግማሽ የኢትዮጵያ መንግሥት ቀሪውን ደግሞ የኔዘርላንድ መንግሥት የሚሸፍኑ ይሆናል። የህክምና ህንፃ ግንባታው የህክምና መሣሪያና የጤና ባለሙያ በአንድ ላይ ተሟልተው እንዲጀምሩ ታቅዶ የሚካሄድ መሆኑ ፕሮጀክቱን ከሌሎች ፕሮጀክቶች ልዩ ያደርገዋል።
ከ2016 ጀምሮ በተደረጉ ጥናቶች 51 በመቶ የሚሆኑት ዜጎች የህመም ምክንያት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መሆናቸውን ሚኒስትሩ አያይዘው ጠቅሰው፣ለእዚህ ህክምናም አራት ትልልቅ ፕሮጀክቶች እንደሚጀመሩ ጠቁመዋል።
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤የልብ ህክምና ማዕከሉን ጨምሮ በአስር ሚሊዮን ዶላር የጨረር ካንሰር ህክምናን በሌላ ማሽን ለመቀየር እና በአንድ ወር ሥራ ለመጀመር ታስቧል፡፡ በጥቁር አንበሳ የኩላሊት ህክምና አገልግሎት ለመስጠት 30 ሚሊዮን ዶላር ተይዟል፡፡
በሆስፒታሉ የልብ ቀዶ ህክምና ከፍተኛ አማካሪ እና የብሔራዊ ፕሮጀክቱን ላለፉት አምስት ዓመታት በአስተባባሪነት የመሩት ዶክተር ብርሃኑ ነጋ እንዳሉት፤ ፕሮጀክቱ የልብ ህክምና ማዕከሉ ወጪን፣ የህንፃ ግንባታን፣ የህክምና መሣሪያዎች ግዢን፣የስምንት ዓመት የልብ ህክምና መሣሪያዎች የጥገና ወጪን ይሸፍናል፡፡ የልብ ህሙማን ህክምና ተቋም ተደራጅቶ ህክምና ከመስጠት ባለፈ ለሁለት ዓመታት ሥልጠና የሚሰጥበትም ይሆናል፡፡
‹‹ከሠራተኞቻችን ሲሶው የሚገኘው በዚህ ኮሌጅ ውስጥ ነው ››ያሉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና፣ የልብ ህክምና ማዕከሉ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ ሀገሪቱን በምስራቅ አፍሪካ የተሻለ እና የላቀ ደረጃ ላይ እንደሚያደርሳት ተናግረዋል፡፡
እንደ ፕሮፌሰር ጣሰው ገለጻ፤በልብ ህክምና ሥርዓተ ትምህርት ተዘጋጅቶ ትምህርት እየተሰጠ ሲሆን፣ለዘህም ከኬፕታውን ዩኒቨርሲቲ ስምምነት ተፈጥሯል፡፡ ከኖርዌይ እና ካናዳ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋርም የህክምና ባለሙያዎችን ለማሰልጠን እየተሠራ ነው።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዳዊት ወንድማገኝ በስነስርዓቱ ላይ እንደገለፁት፤ የልብ ህክምና ማዕከሉ 100 አልጋዎች ይኖሩታል፡፡ በየዓመቱ 5ሺ የሚደርሱ ታካሚዎችን የሚቀበል ሲሆን፣ 35 በመቶ የሚሆኑ የድሃ ድሃ ለሆኑ ታካሚዎች በነፃ ህክምና የሚሰጥም ይሆናል፡፡ 20በመቶ ታዋቂና ተከባሪ ሰዎችን በተጨማሪ ክፍያ ታካሚዎችን በልዩ ክፍል ተቀብሎ ለማከም ታስቦም ነው የሚገነባው።
የህክምና ማዕከሉን ለመገንባት ከሦስት ዓመታት በፊት የአዋጪነት ጥናት የተካሄደ ሲሆን፣ግንባታውም በሦስት ዓመታት ውስጥ የሚጠናቀቅ ይሆናል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22/2011
በኃይለማርያም ወንድሙ