አዲስ አበባ፡- የዘንድሮው አለም አቀፍ የሰራተኛች ቀን መንግስት ሰላምን እንዲያስከብር በመጠየቅ የሚከበር መሆኑን የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን አስታወቀ፡፡
ኮንፌዴሬሽኑ ዘንድሮ በኢትዮጵያ ለ44ኛ፤ በአለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ130ኛ ጊዜ ነገ
የሚከበረውን አለም አቀፍ የሰራተኞች ቀን አስመልክቶ ትናንት በፅህፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ እንደገለፁት፤ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች በርካታ ሰራተኞች ተረጋግተውና ከቦታ ቦታ እንደልብ ተንቀሳቅሰው ለመስራት አልቻሉም፡፡
የሀገር አንድነት፣ የሰራተኛው መደራጀትና ሁለንተናዊ እድገት መምጣት የሚችለው ሰላም ሲፈጠር መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ጠቅሰው፣ መንግስት ሰላምን እንዲያስከብር ለመጠየቅ የዘንድሮው አለም አቀፍ የሰራተኞች ቀን ‹‹ሰላም ለሃገር እድገት፣ ለሰራተኛው መደራጀትና ሁለንተናዊ እድገት መሰረት ነው›› በሚል መሪ ቃል እንደሚከበር አስታውቀዋል፡፡
ቀኑ በአለም አቀፍም ሆነ በሃገር አቀፍ ደረጃ ለሰራተኞች መብትና ጥቅም ሲታገሉ መስዋትነት የከፈሉ አባት ሰራተኞችን በመዘከርና የትግል አንድነት ቃልን በማደስ ጭምር ይከበራል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ በተለይ የወቅቱ የሰራተኞች አንገብጋቢ ጥያቄዎችን ለመንግስት በማቅረብ ምላሽ እንዲያገኙ ጥረት እንደሚደረግም አስታውቀዋል፡፡
እንደ አቶ ካሳሁን ገለጻ፤በዋናነትም በግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ የሚሰሩ ሰራተኞች የመደራጀት መብት ትኩረት እንዲሰጠው፣ በህገ መንግስቱ እውቅና የተሰጠው የመንግስት ሰራተኞች የመደራጀትና የመደራደር መብት ተግባራዊ እንዲሆን፣ ሀገር አቀፍ የመነሻ ደሞዝ ወለል እንዲኖር፣ የስራ ቦታዎች ከአደጋና ከበሽታዎች የፀዱ እንዲሆኑና የወጡ የሞያ ደህንነትና ጤንነት አጠባበቅ ፖሊሲዎች፣ ህጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ተግባራዊነት በተሻለ መልኩ ስራ ላይ እንዲውሉ ስራዎች የሚሰሩበት ነው፡፡
በሰራተኞች ላይ ምንም ሳይሰሩ የሚነግዱ ኤጀንሲዎች ወይም ደላሎች ላይ አስፈላጊው ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ፣ በኢትዮጵያውያን ሊሸፈኑ የሚችሉ ዝቀተኛ የስራ መደቦች ላይ የውጪ ዜጎችን መቅጠር እንዲቆም፣ ከመንግስት ወደ ግል በፕራይቬታይዜሽን የሚዘዋወሩ ድርጅቶች አቅም ለሌላቸው ባለሃብቶች በመሸጣቸው ምክንያት የሰራተኛው የስራ ዋስትና አደጋ ላይ መውደቅና የስራ ዋስትናውን ማጣት የሚሉ ዋና ዋና ጉዳዮችና ሌሎችም መሰል የሰራተኞች ጥያቄዎች የሚስታጋቡበት ቀን መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22/2011
በአስናቀ ፀጋዬ