የሪፖርተር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ አቶ ዘካርያስ ስንታየሁ
ዛሬም ድረስ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚዲያ ነፃነት አለ ለማለት የሚያስደፍር ነገር የለም ፤አንጻራዊ በሆነ መልኩ ግን መሻሻሎች እየታዩ ናቸው። በንጉሱ ዘመን የነበሩት ሚዲያዎች የንጉሰ ነገስቱን ሀሳብ ብቻ ሲያንፀባርቁ ነበር ፤በወቅቱ የግል ሚዲያዎችም አልነበሩም።
የንጉሱ ሥርዓት አብቅቶ ደርግ ስልጣኑን ሲቆጣጠር ሚዲያው ጭራሽ የባሰ እስር ቤት ለመግባት ተገደደ ፡፡ለአሥራ ሰባት ዓመታትም የሚዲያ ነፃነት የሚለው ቃል ተነስቶ አያውቅም ።
ኢህአዴግ ሲመጣ ግን ቢያንስ በወረቀት ደረጃ የሚዲያ ነፃነት እንደሚጠበቅ መቀመጡ አንድ የተስፋ እርምጃ ቢሆንም የተባለውን ያህል ግን
አልተተገበረም። ኢህአዴግ የሀገሪቱ የበላይ ገዢ በሆነው ህገ መንግሥት የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ አንቀፅ 19ኝን ቃል በቃል ተርጉሞ አስቀምጦታል።
ይህንን ተከትሎ ጥቂት የማይባሉ የግል የህትመት ሚዲያዎች ወደ ገበያው በመግባት የመንግሥት አፍ ሆነው ከሚያገለግሉት የመንግሥት ሚዲያዎች ውጪ ለህዝቡ አማራጭ ሆነው ማገልገል ችለዋል። በእነዚህ ጊዜያትም ቢሆን ግን እንደፈለጉ በነፃነት መናገርና መጻፍ ይቻል ስላልነበር ከወረቀት በዘለለ የሚዲያው ነፃነት ተከብሮ ነበር ለማለት አያስደፍርም ።
ይህም እስከ 1997 እየተንገዳገደ በዚህ መልኩ መሄድ ቢችልም በምርጫ 97 የተከሰተውን የፖለቲካ ውጥረት ተከትሎ ወደነበረበት ለመመለስ ተገዷል። ከዓመት በፊት በሀገሪቱ የተደረገውን ለውጥ ተከትሎ ከለውጡ በፊት ከነበረው አንፃር መሻሻሎች እየታዩ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ሚዲያዎችም እንደ ልብ የመናገር የመፃፍ እንቅስቃሴ ውስጥ ገብተዋል። አዳዲስ ጋዜጦችና ሚዲያዎችም ዘርፉን እየተቀላቀሉት ይገኛሉ።
ከኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት አንፃር በህትመቱም በሬድዮና ቴሌቪዥንም ያለው የሚዲያ ብዛት በቂ አይደለም ። ይህም በመሆኑ የሀሳብ ነፃነት እንደልብ እንዳይንሸራሸር አንድ መሰናክል ነው ስለ ሚዲያ ነፃነት ሲወራ ወደ ሚዲያው ኢንቨስትመንት ለመግባት ያለው ምቹነትም መታየት አለበት።
በመንግሥት በኩል እንደ ኢንቨስትመንትም ለሚድያው እንደ ሌላው ዘርፍ ማበረታቻ ሲደረግለት አይታይም። የወረቀት ውድነት አለ። የህትመት ዋጋ እየጨመረ ነው ፡፡ይሄ ወደ ዘርፉ ለገቡትም ለሚገቡትም ጋዜጦችና መጽሄቶች ችግር ነው። በሬድዮና በቴሌቪዥኑም በኩል ለማቋቋሚያ የሚጠይቀው ወጪ ከፍተኛ ነው። ወደ ኢንቨስትመንቱ ለመግባት ያለው ዕድል ጠባብ መሆኑ በራሱ የሚዲያውን ነፃነት የሚጋፋ ሆኖ ይገኛል።
በመሆኑም ሚዲያው ለሀገር ሰላም ለዴሞክራሲ መበልጸግ፤ ለማህበረሰብ ንቃተ ህሊና መዳበር እንደሚያስፈልግ በመገንዘብ በመንግሥት በኩል አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግና ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይጠበቅበታል። በተጨማሪም ሚዲያውን የማያንቀሳቅሱ አንዳንድ ህጎችንም ማሻሻል ያስፈልጋል። በሚዲያዎቹም በኩል ሙያውን አክብረው መስራት አለባቸው፡፡ህዝቡ ለሚዲያ ጆሮ እንደሚሰጥና እንደሚያምን ግንዛቤ በመያዝ አሁን በስፋት እንደሚስተዋለው የአንድ ወገን ሀሳብ ይዞ ከመንጎድና ሀሰተኛ መረጃ ከማቅረብ መታቀብና የውስጥ አቅማቸውን መገንባት ይጠበቅባቸዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22/2011