አዲስ አበባ፡- በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ የተከሰተው ግጭት እንዳይስፋፋና የስጋት ቀጣናዎችን ከስጋት ውጭ ለማድረግ የአማራና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች አመራሮች እየሰሩ መሆናቸው ተገለጸ፡፡
የአማራ ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ አሰማኸኝ አስረስ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ችግሩ ከተከሰተበት ወቅት ጀምሮ የአማራና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ከፍተኛ የሥራ አመራሮች ምክክር እያደረጉ ቆይተዋል፡፡
በጋራ በመሆን ባስቀመጡት አቅጣጫና የመፍትሄ እርምጃ ግጭቱ እንዳይስፋፋና የስጋት ቀጣናዎችን ከስጋት ውጭ ለማድረግ እየተሰራ ነው፡፡ በተደረገው የጋራ ምክክርም አካባቢው ላይ የመከላከያ ሠራዊትን ጨምሮ የፌዴራል ፖሊስና ሌሎች የጸጥታ ሀይሎች እንዲገቡ ተደርጓል፡፡
በትናንትናው እለትም ከሁለቱ ክልሎች የተወጣጡ ከፍተኛ የስራ አመራሮች ለችግሩ መፍትሄ ለማስቀመጥ እንዲሁም ተጨማሪ ተፈናቃዮች እንዳይኖሩ ለማድረግ፤ በአካባቢው ላይ ያሉና ለማፈናቀል የሚፈልጉ እኩይ ዓላማ ያላቸውን አካላት ቅስቀሳዎች ለማክሸፍ እርምጃዎች እየወሰደ ችግሩን በዘላቂነት የሚፈታ ቡድንም ተቋቁሞ ስራ ጀምሯል፡፡
በአሁኑ ወቅት ችግሩ መኖሩን አምኖ ከመቀበል ጀምሮ መፍትሄ ለማምጣት በጋራ እስከ መስራት በሁለቱ ክልል መንግስታት መካከል ጥሩ ግንኙነት መኖሩን የገለጹት አቶ አሰማኸኝ፤ የሁለቱ ክልል መንግስታት
ርዕሰ መስተዳድሮችን ጨምሮ ሌሎችም አካላት ለዚህ ጉዳይ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ቆስለው ወደ ሆስፒታል ለገቡት ሰዎች አስቸኳይ ድጋፍና የህክምና ክትትል እንዲደረግላቸውና ተጎጂዎችን ሊታደግ የሚችል ሥራ እንዲሰራ አቅጣጫ መሰጠቱንም ተናግረዋል፡፡
ችግሩ ሚያዚያ 17 ቀን 2011 ዓ.ም የተከሰተ መሆኑን፤ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን በዳንጉር ወረዳ አይስካል ቀበሌ በሚባል ቦታ ላይ በጫኝና አውራጅ ግለሰቦች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ግጭት መፈጠሩን፤ በአካባቢው የነበረ የፌዴራል ፖሊስ ሠላሙን ወደ ነበረበት ቦታ ለመመለስ ሳይቻለው ቀርቶ በግጭቱ ምክንያት ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ የሟቾች ቁጥር 17 መሆናቸውን አቶ አሰማኸኝ አብራርተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22/2011
በአዲሱ ገረመው