በሀገሪቱ እየተፈጠሩ ያሉ አለመግባባቶችንና ግጭቶችን በማባባስ በኩል አንዳንድ የግልም ሆነ የመንግስት ሚዲያዎች ሚና አላቸው፡፡ የሚያስተላልፏቸው መልእክቶች የሚዲያ ስነ ምግባር የጎደላቸውና ማህበራዊ ኃላፊነትን ከግምት ውስጥ ያላስገቡ በመሆናቸው የቁጥጥር ስርአት መዘርጋት አስፈላጊነት መሆኑን ባለሙያዎች ይጠቁማሉ።
የጂማ ዩኒቨርሲቲ የሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ትምህርት ክፍል መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ደመላሽ መንግስቱ፤ አንዳንድ ሚዲያዎች ከስነ ምግባር ውጭ በሆነ መልኩ የሚያስተላልፉት መረጃ ህዝብ የሚከፋፍልና ሀገርም የሚያፈርስ መሆኑን ይጠቁማሉ።ሚዲያዎቹ የራሳቸው አጀንዳ እና ከጀርባ ሆነው የሚቆጣጠሯቸው
አካላት ያሏቸው በመሆናቸው የጋዜጠኝነት ስነ ምግባር ተከትለው አይሰሩም ሲሉ ያብራራሉ፡፡
‹‹በኢትዮጵያ ከዴሞክራሲና ከሚዲያ ነፃነት ጋር በተያያዘ በርካታ ገንዘብ ያላቸው አካላት አሉ፤ በፖለቲካ አመለካከታቸው ደጋፊ ስላላቸው ብቻ ሚድያ የሚያቋቁሙም አሉ››ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ እነዚህ ፖለቲከኞች አላማቸውን ለማሳካት በአንድ ወገን የህዝቡን ባህልና እውቀት ለመናድ በሌላ በኩል የራሳቸውን አዲስ ሀሳብ በህብረተሰቡ ላይ ለመጫን ሚዲያውን ሲጠቀሙበት ማየት እየተለመደ መጥቷል ይላሉ።
የከፊሎቹ ሚዲያዎች የገንዘብ ምንጭም እነዚሁ አካላት መሆናቸውን ይጠቁሙና ሚዲያዎቹ ቅድሚያ የሚሰጡት ለጋዜጠኝነት ስነ ምግባር ሳይሆን ለሚደግፏቸው አካላት አመለካከት ይሆንና ህዝብንም ሀገርንም ለአደጋ የሚያጋልጥ
ስራ ሲሰሩ ይታያል ሲሉ ያብራራሉ። የመንጋ/ የጎዳና ላይ ፍትህ፤ ለመንግስት አልገዛም ባይነት እንዲከሰት በማድረግ በኩል የሚዲያው እጅ እንዳለበትም የሚናገሩት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ ይህ በዚሁ ከቀጠለ ጥያቄ ውስጥ የሚገባው እንደ ሀገር መቀጠላችን ብቻ ሳይሆን፣ ከፍተኛ ውድመትና እልቂትም ሊከሰት የሚችልበት እድል ሰፊ መሆኑንም ያስገነዝባሉ።
የሪፖርተር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ አቶ ዘካርያስ ስንታየሁ በሚዲያዎች በኩል ስነምግባር በጎደለው መልኩ ፅንፍ መያዝና መወገን እንደሚታይባቸው በመግለጽ የረዳት ፕሮፌሰሩን ሃሳብ ያጠናክራሉ፡፡ የዘር ፖለቲካ እንቅስቃሴም ሚዲያዎችን ወደ ራሱ እየጎተታቸው መሆኑም ሌላው ስጋት ነው ይላሉ።
እንደ ዋና አዘጋጁ ገለጻ፤ በአሁኑ ወቅትአብዛኛው ሚዲያ የራሱን የፖለቲካ መስመር ይዞ መጓዝ ይታይበታል።ይህም በነፃው ሚዲያ ብቻ ሳይሆን በመንግስትና በክልል ሚዲያዎችም ይስተዋላል። የፖለቲካ ፓርቲዎችና አክቲቪስቶች በሚያራምዱት ሀሳብ የተቃኙ የሚዲያ ተቋማትም በርካታ ናቸው።የጥላቻ ፖለቲካና ንግግርም እየተስፋፉ ሲሆን፣ እነዚህ ችግሮች በመደበኛው ሚዲያ ድጋፍ ሲያገኙ የሚፈጠረው ችግር የከፋ ይሆናል።
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ገብረጊዮርጊስ አብርሃ፤፤ሚዲያዎች ቁጥራቸው እየጨመረ መምጣቱን ይጠቅሱና፣ የሀሳብ ብዝሀነትን በማራመድ ረገድ ክፍተት እንዳለባቸው ይጠቁማሉ። አብዛኛው ሚድያ ከጋዜጠነኝነት ስነምግባር ባፈነገጠ መልኩ የአንድ ወገን ሀሳብ ብቻ በማራመድ ላይ እንደሚገኝም በመጥቀስ የረዳት ፕሮፌሰሩንና ዋና አዘጋጁን ሀሳቦች ያጠናክራሉ።
በአሁኑ ወቅት ሚዲያዎች በህዝቦች መካከል አለመተማመንና መጠራጠርን እንዲኖር የሚያደርጉ ዘገባዎች በስፋት ሲያስተላልፉ እንደሚስተዋሉ፣ ይህም አንደኛ የሀገሪቱን ህግ ባለመከተል በሁለተኛ ደረጃም ሞያውን ካለማወቅ እንደሚመነጭ ያብራራሉ፡፡ ህጉን እያወቁ የማያከብሩም እንዳሉም ያመለክታሉ።
‹‹የመንግስት ሚዲያዎች ሚዛናዊነት የጎደላቸው ስራዎችን ብቻ በማቅረብ ሲጠመዱ ሌሎቹ በተቃራኒው ጎራ ተሰልፈው ይታያሉ›› ያሉት አቶ ገብረጊዮርጊስ፣ የአንድ ወገን ዘገባ ይዞ መውጣት አንዱ የስነ ምግባር ጉድለት መሆኑን፣ ይህም የመገናኛ ብዙኃኑ ተቀዳሚ አላማ የሆነውን ህዝብ ማገልገልን ጥያቄ ውስጥ እንደሚያስገባው ነው የሚናገሩት፡፡
ረዳት ፕሮፌሰሩ ዶክተር ደመላሽ፤ መንግስት ሚዲያውን በሙሉ ለቆ ማንም ያሻውን የሚሰራ ከሆነ አገር ማፍረስ ለሚፈልገውም በር እንደሚከፈት በመግለጽ፣ መንግስት የመቆጣጠር ኃላፊነት እንዳለበት ያመለክታሉ። መንግስት ይሄን ሲያደርግ የተለመደው የሚዲያ አፈና ተደረገ የሚል ትችትና ቅሬታ መነሳቱ አይቀርም ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ ሰዎች ከመሞታቸውና ወደ እርስ በእርስ ግጭትና እልቂት ከመገባቱ በፊት ሚዲያው ላይ ገደብ ሊያደርግ እንደሚገባም ነው የሚያስገነዝቡት። ይህን ለማድረግ በአንድ ጊዜ ውሳኔ ማሳለፍ እንደማይገባም አመልክተው፣ ከምሁራን ከሚዲያውና ከህዝቡ ጋር በመወያየት ፖሊሲ፤ ህግ፤ መመሪያና ደንብ ማዘጋጀት ይጠበቃል ሲሉ ተናግረዋል።
‹‹የትኛውም ሚዲያ ዜግነት፤ብሄር፤ሀይማኖት ሊኖረው አይገባም፤ ህዝባዊና ሀገራዊ ሀላፊነት በመያዝ የሁሉንም ህብረተሰብ ድምፅ ስነምግባርና ሀላፊነት በተሞላበት መልኩ ማስተናገድ ይጠበቅበታል።›› ያሉት የሪፖርተር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ፣ ከተጽእኖ ነጻ ከመሆን ባለፈ የጋዜጠኝነት ስነ ምግባርን ማወቅ እንደሚያስፈልግ፣ ለዚህም ሚዲያዎች መመራትም ሆነ መስራት ያለባቸው በዘርፉ በሰለጠኑ ባለሙያዎች መሆን እንዳለበት ያስገነዝባሉ። በፍላጎትና በተፈጥሮ ስጦታ የሚሰሩ ካሉም የቀጠሯቸው ሚዲያዎች የጋዜጠኝነትን ስነ ምግባር የማስተማርና የመቆጣጠር ኃላፊነት አለባቸው ይላሉ።
ዋና አዘጋጁ ሚዲያዎችን መንግስት ይቆጣጠራቸው በሚለው ሀሳብ አይስማሙም። መንግስት የራሱ ፍላጎትና አላማ እንዳለው በመጥቀስ፣ እንደ ከዚህ ቀደሙ ለራሱ አላማ ማሳኪያ ሊያደርጋቸው ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ይጠቁማሉ። ሚዲያዎች ተሰባስበው የራሳቸውን ካውንስል በማቋቋም ህግና ደንብ በማውጣት ራሳቸውን መቆጣጠር እንደሚኖርባቸው ያመለከቱት ዋና አዘጋጁ፣ በዚህም አስተማሪ ቅጣት ማስተላለፍ የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደሚችሉም ይጠቁማሉ።
አቶ ገብረጊዮርጊስ ከዴሞክራሲው ጋር አብሮ የሚያድግ፣ ግጭትን የሚከላከል፣ አንድነትን የሚያጎለብት፣ ልማትን የሚያፋጥን ሚዲያ እንደሚያስፈልግ እና ሚዲያዎችን እንደ ተቋም መቆጣጠር ያለበት የብሮድካሰት ባለስልጣን መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ለዚህም የተጀመሩ ስራዎች እንዳሉ ጠቅሰው፣ ባለስልጣኑ ባደራጀው የመገናኛ ብዙሃን ክትትልና አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት በኩል ከህብረተሰቡ የሚቀርቡ ጥቆማዎችንና አስተያየቶችን በመሰብሰብ፤ የመስክ ምልከታ በማደረግ እርምጃ እስከ መውሰድ ድረስ እየሰራ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡
ዳይሬክተሩ የሚድያ ፖሊሲ አለመኖሩ አንዱ ችግር እንደነበር ይጠቅሱና ይህም እየተዘጋጀ መሆኑንና ምን ይዘት ሊኖረው ይገባል በሚለው ላይ ግብአት ለማከል ከሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይት እንደተካሄደበትም ያብራራሉ፡፡
የቁጥጥር ስራው ብቻውን ውጤታማ ያደርጋል ተብሎ አይታመንም የሚሉት ኃላፊው፣ ክፍተቶችን መሰረት ያደረገና የግጭት አዘጋገብ እንዴት መሆን እንዳለበት ለጋዜጠኞች ስልጠና መስጠት ከሚዲያዎችም ይጠበቃል ይላሉ። ህብረተሰቡን በስነ ምግባር በመቅረፅ የሰላምና የልማት አቅጣጫዎችን በማመላከት ረገድ ማህበራዊ ኃላፊነት እንዳለባቸው እና ሞያው የሚጠይቀውን ስነ ምግባር ተከትለው መስራት እንደሚጠበቅባቸውም ያስገንዝባሉ።
በአሁኑ ወቅት ሚዲያዎች ህዝብን ከህዝብ፣ ብሄርን ከብሄር፣ ሀይማኖትን ከሀይማኖት በማቃቃር ለሚፈጠር ግጭት መነሻ እየሆኑ መምጣታቸው ይታወቃል። በቅርቡ የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ምቹ መደላድል ለማዘጀት ፋይዳ ያላቸው የመገናኛ ብዙኃን የመረጃ ነጻነት አዋጅ 590/2000 እና የብሮድካስት አገልግሎት አዋጅ ቁጥር 533/1999 እየተሻሻሉ መሆናቸውን አስታውቋል።
ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ተግባራዊ ሲያደረግ የሌሎችን ሰላምና ደህንነት ማእከል ያደረገና ሰብአዊ ክብርን የማይነካ መሆን እንዳለበት ይታወቃል። ወደ ስራ ሲገባም የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛና ምንጫቸው ያልታወቀ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል የሚያስችል አዋጅም ተረቋል። አዋጁ ሁሉንም የመንግስትና የግል ሚዲያዎች እና ማህበራዊ ድረ ገፆችን የሚቆጣጠር ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ ውጪ ያሉትንም እንዲያካትት ካሉበት ሀገር ጋር ውይይት እንደሚደረግም ተጠቁሟል።
ሚዲያው ስነምግባርን በተላበሰ መልኩ ኃላፊነቱን እንዲወጣ መንግስት እያሻሻላቸው የሚገኙ የዘርፉ አዋጆችና እና የጥላቻ ንግግርን ማስቀረት የሚያስችለው አዋጅ ጸድቀው በአስቸኳይ ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረግ ይገባል፡፡ በሚዲያዎች በኩልም የሚዲያ ካውንስሉን በማቋቋም እና ወደ ስራ እንዲገባ በማድረግ ተቋማቱ በካውንስሉ በኩል የሚመሩበትን ስርአት መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22/2011
በራስወርቅ ሙሉጌታ