በዕኩለ ቀን ላይ ከተማዋን እየዞርኩ ስለነበር የሰውን የመንገድ ላይ እንቅስቃሴ በሚገባ ለማስተዋል አልከበደኝም። ውስጤን ፈትሾ ልዩ ስሜት በሚሰጠኝ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ነዋሪዎችን ለማውጋት ወደ አንዱ መንደር ጎራ አልኩ። ቦታው ነቀምቴ ከተማ 03 ቀበሌ በተለምዶ ጨለለቂ ተብላ በምትጠራው አካባቢ ነው። ሠላምታቸውን ከፈገግታ ጋር ያልነፈጉኝ የዕድሜ ባለፀጋዋ ወይዘሮ ዘውዴ ሞሲሳ በኢትዮጵያዊነት የእንግዳ አቀባበል ወጋችን መሠረት ከተቀመጡበት ተነስተው እንድቀመጥ ጋበዙኝ። አክብሮታቸውን ተቀብዬ ሁለታችንም ከተቀመጥን በኋላ ጋዜጠኛ እንደሆንኩና ምን እንደምፈልግ ስነግራቸው በደስታ ሊነግሩኝ ፈቃደኝነታቸውን ገለጹልኝ።
ወይዘሮ ዘውዴ፤ አካባቢያዊውን የሠላም ሁኔታና ከሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ስላለቸው ግንኙነት የሚመለከተውን ጥያቄዬን ተከትለው ‹‹በአካባቢው ባለፉት ረጅም ዓመታት ብዙ ማኅበራዊ ችግሮች በተደጋጋሚ ሲከሰቱ ነበር። እንደ ሴትነታቸው የሠላም ችግር በነበረበት ወቅት ሠላም እንዲሰፍን ሠርተናል። ረሐብ ሲከሰት ሁሉም የተቸገረ ሰው እንዲረዳ አድርገናል። ዜጎች ከቀዬና ንብረታቸው ሲፈናቀሉ የአካባቢው ማኅበረሰብ ድጋፍ እንዲያደርግ ሠርተናል። ይህንን ሁሉ ስናደርግ አንድም ቀን ሰውን በብሔር ለይተን አናውቅም›› በማለት ከሰፊ በጥቂት ቃላት ብዙ መልስ ሰጥተዋል።
በአሁኑ ወቅትም ሌሎች እንደሚያወሩት አካባቢው የብጥብጥ ስፍራ ሳይሆን ሠላም የነገሠበት፣ ችግር ሲፈጠር እኳን መነሻው የማኅበረሰቡ የርዕስ በርዕስ ጥላቻ ሳይሆን የወጣቱ ኃይል የመሠረተ ልማትና ተያያዥ የሥራ ዕድል ጥያቄዎች መሆናቸውን፤ ለዚህም መንግሥት በትኩረት አለመሥራቱ ነገሩ በመግነኑ ሌላ መልክ እንዲይዝ በመደረጉ፤ ወደፊትም ይህ ችግር ካልተቀረፈ ጥያቄው ማቆሚያ እንደሌለው ተናግረዋል።
በነቀምቴ ከተማ የቀበሌ ሰባት ነዋሪ የሆኑት አቶ ተስፋዬ እምሩ በበኩላቸው፤‹‹ወለጋ ውስጥ ሌሎች ብሔረሰቦች በሠላም መኖር አይችሉም ተብሎ በሩቅ እንደሚወራው አይደለም። እኛ ከሁሉም ኢትዮጵያውያን ጋር በአንድነት እየኖርን ነበር፤ አሁንም እየኖርን ነው፤ ወደፊትም ይኸው ይቀጥላል። ነቀምቴ ውስጥ ነዋሪ የሆነው የኦሮሞ ብሔረሰብ ብቻ አይደለም። ሁሉም የአካባቢውን የመኖራችን ምክንያታዊ ጭብጥ የአባቶቻቸው ጉልህና ዕንቁ ታሪክ እንደነበር ያስረዳሉ።
በአካባቢው ሁሉም ሰው ለኃይማኖቱ ተገዥ በመሆኑ ከሁሉም ጋር የመኖር ባህሉ የጠነከረ ነው፤”በየትኛውም የማኅበራዊ ግንኙነት ውስጥ አንድ ቀን እንኳን ሌላውን ለይተን አናውቅም። በአካባቢ ጥላቻ መኖሩን የሚያናፍሱት ሌሎች የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ሌት ተቀን የሚሠሩ አካት ናቸው›› ብለዋል።
ትናንትም ዛሬም ጥያቄያችንና ትልቁ ችግራችን የልማትና የእንጀራ ጉዳይ ነው ያሉት አቶ ተስፋዬ፤ በተለይ የሥራ አጥ ወጣቶች ቁጥር ስለተስፋፋ ወጣቶች በአደባባይ እየወጡ ጥያቄያቸውን ለማቅረብ ተገደዋል። የእነርሱ ጥያቄ ‹‹ወላጆቻችን ያላቸውን መሬትና በሬ ሸጠው አስተምረውናል፤ በተራችን እነርሱን መርዳት አለብን፤ ነገር ግን አልተቻለም›› የሚል ሃሳብ ነው በውስጣቸው ነግሦ በአደባባይ እንዲተነፍሱ ያደረጋቸው ብለዋል።
የነቀምቴ መሬት ሠላምን እንደሚሻ፤ ጥያቄው ከተመለሠም ሙሉ ሠላም እንደሚመለስና የተቸገረ ሠው ለሠላም ቦታ ስለማይኖረው ከዚህ አንፃር መንግሥት ለሥራ አጥ ወጣቶች ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባው አቶ ተስፋይ ተናግረዋል።
በነቀምቴ ከተማ ቀበሌ አራት ነዋሪ የሆኑት አቶ ነሞምሳ ቶሌራ ‹‹እኛ ገበያ ስንሄድ እንኳን ሰዎችን በማንነታቸው ለይተን ተገበያይተን አናውቅም። ይህ ደግሞ የወለጋ ሰው ለሌለው ክብር እንዳለው የሚያሳይ ነው። ብሔር፣ ብሔረሰቦችን በማጋጨት የራሳቸውን ዓላማ የሚያሳኩ ሰዎች መኖራቸውን ተገንዝበናል። በዚህ ስፍራ ኃይማታዊ አስተምህሮን በማጥበቅ በፍቅር አብሮ መኖርን ማዳበር እንዳለብን እየመከርን አሁን አካባቢው ሰላም ነው። የበርካቶች ጥያቄ የሆነው የሥራ ዕድል ጉዳይ ግን መንግሥትን ሊያሳስበው ይገባል›› ይላሉ።
በምሥራቅ ወለጋ ዞን የነቀምት ከተማ ማዘጋጃ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደረጄ ቶሌራ እንደሚሉት፤ በምሥራቅ ወለጋ በተለይም በነቀምት ከተማ የሚወራውና የሚታየው ነገር አንድ አይደለም። ነቀምቴ ለሁሉም አመቺ የሆነች ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚኖርባት ከተማ ናት። በአካባቢው ነዋሪ የሆኑት ማኅበረሰቦች ከሌላ አካባቢ የሚመጡትን ተቀብለው በማስተናገድ ሁሉም ባይተዋርነት ሳይሰማው እንደራሱ ቤት ቆጥሮ የሚኖርባት ናት። ለመሠረተ ልማትም ሆነ ለኢንቨስትመንት እንቅፋት የምትሆን አካባቢ አይደለችም።
ኃላፊው አክለውም፤ ወለጋን እንዳታድግ የሚያደርጋት ሰፊ ተቀናቃኝ ቡድኖች መኖራቸው ሲሆን ይህ ደግሞ በምንም አንፃር ከህዝብ ጋር እንደማይገናኝና ከህዝብና ሃሳብ ጋር የተራራቀ እንደሆነ፤ወለጋን የፈጠራትና ወለጋ ውስጥ የኖረ ህዝብ የወለጋን ዕድገት የሚጠላ አለመሆኑን ይናገራሉ።
በአሁኑ ወቅት ለኢንቨስትመንትም፣ ለቱሪዝም ምቹ ስለሆነች ባለሀብቶች መዋዕለ ነዋያቸውን በማፍሰስ መሥራት እንደሚችሉና የአካባቢው ህዝብም የሚመጣውን መሠረተ ልማትና ኢንቨስትመንት ለመቀበል ዝግጁ መሆኑን ገልጸው የማኅበረሰቡ ጥያቄም ትክክል መሆኑንና ቀጣይነት ያላቸውን የመሰረተ ልማት ሥራዎች ለማስፋፋት እንዲሁም የሥራ አጥ ቁጥርን ለመቀነስ ከክልሉና ከፌዴራል መንግሥት ጋር እንደሚሠራ አስገንዝበዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዚያ 21 ቀን 2011 ዓ.ም
አዲሱ ገረመው