አዲስ አበባ፡- ለውጡን ተከትሎ በኢትዮጵያ እየታየ ያለው ጅምር የሚዲያዎች የነፃነትና አሳታፊነት ጉዞ ዘላቂነት እንዲኖረው መሥራት እንደሚገባ ተገለጸ። አሁን ላይ በተለያየ መልኩ የተቋቋሙ ሚዲያዎች የአግላይነት አካሄድም ሊታረም እንደሚገባው ተጠቁሟል። አዲስ ዘመን ጋዜጣ ያነጋገራቸው የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ ኃላፊዎች እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ታሪክ ከነፃነታቸው ይልቅ ታፍነው መቆየታቸው፤ ለህዝብ ከመወገን ይልቅ በስርዓት አገልጋይነታቸው ጎልቶ ይገለጻል። ሆኖም ከአንድ ዓመት በፊት የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ባገኙት ነፃነት የቀደመ ገጽታ መቀየር የሚችሉበትን ተግባር እያከናወኑ ሲሆን፤ ይሄን ነፃነት ዘላቂ ለማድረግ መሥራት ይገባል። ከዚህ በተጓዳኝም ለውጡን ተከትሎ በተፈጠሩ ሚዲያዎች የሚታይ የአግላይነት አካሄድ ማረም ያስፈልጋል።
የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ(ኢራፓ) ፕሬዚዳንት አቶ ተሻለ ሰብሮ እንደሚሉት፤ በኢትዮጵያ በየዘመናቱ የነበረው የፕሬስ ነፃነት አለ የሚያስብል አልነበረም። ሆኖም በእነዚህ ዘመናት ነፃነቱ የለም፤ሚዲያዎቹም ከህዝብ ይልቅ ለስርዓት ቆመዋል ቢባልም፤ ሁሉም ግን ዝም ብለው ተቀምጠዋል ማለት አይደለም። ምክንያቱም የሚዲያ ነፃነቱ ከወረቀት እንዲያልፍ ህዝብና የሚዲያ ሰዎች በየዘመናቱ ድምፃቸውን እያሰሙ ለፕሬስ ነፃነት ትግል እርሾ በማስቀመጥ ለዛሬ ጅምር የነፃነት ጉዞ አብቅተውታል። ለውጡን ተከትሎ ካለው የሚዲያ ነፃነትና አጠቃቀም አንጻር “በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ አራት ኪሎ ወንበር እንደያዝን ነው የምንቆጥረው፤” የሚሉት አቶ ተሻለ፤ ሚዲያው ከነበረበት ተጽዕኖ ተላቅቆ በዚህ መልኩ መሥራት መጀመሩ ትልቅእምርታ መሆኑን ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ዛሬም በሚዲያዎች ዘንድ የቀደመውን አካሄድ የሚመስሉ የማበላለጥ፣ አንዱን አቅርቦ ሌላውን የማራቅ ሂደቶች መኖራቸውን በመጠቆም፤ ይሄን ችግር ማረምና አበረታች ጅምሩን ስር እንዲሰድ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ለዚህም የሁሉም ጤናማ ጥረት አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል። የመላው ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት(መኢአድ) የውጭ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አበባው መሃሪ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ ሕግ ማውጣትና ተፈጻሚ ማድረግ የተለያዩ ነገሮች ናቸው። በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ታሪክም የሚዲያውን ነፃ መሆን የሚናገር ህግ ቢወጣም ሕግ እንዲያስፈጽሙ የሚቀመጡት ሙያውን የሚያውቁና ለሚዲያው በነፃነት መሥራት የሚጨነቁ ሳይሆኑ የመንግሥት አካላት እና የገዢው መደብ ወይም ፓርቲ አባላት በመሆናቸው ተፈጻሚነቱ ላይ ትልቅ ችግር ነበረበት። ለውጡን ተከትሎ ለአገርና ህዝብ ለተተኪው ትውልድም መልካም ነገር የፈነጠቀ ጥሩ ጅምር መኖሩን እና እየተካሄዱ ያሉ ጅምር ተግባራትም ጥሩ መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ አበባው፤ ይሄን ጅምር የበለጠ አሳታፊ ማድረግ እንደሚገባ ይገልጻሉ።
አሁን ባለው ሂደትም ከቀድሞው የተሻለ ተሳታፊነት መፈጠሩን በመጠቆምም፤ ተሳትፎው ግን በሚፈለገው ልክ ባለመሆኑ በቀጣይ ሁሉም ያለውን ያክል አስተዋጽዖ እንዲያበረክት ዕድሉን ማስፋት እንደሚገባ ተናግረዋል። እንደ አቶ ተሻለ እና አቶ አበባው ገለጻ፤ ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት ገፍቶ የመጣውን የህዝብ ጥያቄና ጫና ተከትሎ በርካታ ሚዲያዎች ተፈጥረዋል። በዚህ መልኩ የሚዲያ አማራጭ መፈጠሩም መልካም ነው። አሁን ባለው ሂደት ግን ሚዲያዎቹ በአገራዊ ገጽታ ሳይሆን በድርጅት፣ በግለሰብ፣ በአካባቢ፣ በቋንቋ፣ በባህልና በተለያዩ አስተሳሰቦችና አካሄዶች ተደራጅተዋል።
ለምሳሌ፣ አክቲቪስቶች ሚዲያ አቋቁመዋል፤ የተለያዩ ቡድኖችም በተመሳሳይ የሚዲያ ባለቤት ሆነዋል። እነዚህ ሚዲያዎች ግን ሙሉ የኢትዮጵያን ህዝብ እንዲያገለግሉ ይጠበቅባቸዋል። ሆኖም ሚዲያዎቹ ለድርጅቶቻቸው ልዕልና፤ ካልሆነም በስም ለወከሉት ህብረሰተብ ብቻ በመቆም ወግነው ሲሠሩ ይታያል። በዚህ መልኩ በየመንደሩ የሚፈጠሩ ሚዲያዎችም የህዝቦች ሳሆን የግልሰቦች፣ የድርጅቶችና ቡድኖች ድምፅና ፍላጎት ጎልቶ እንዲሰማ እየሆነ ነው። እንዲህ ዓይነት አካሄድ ደግሞ ለአገርም፣ ለህዝብም አደጋ እንደመሆኑ አስፈላጊው ማስተካከያ ሊደረግበት ይገባል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 21/2011
ወንድወሰን ሽመልስ