በአገሪቱ ከሃምሳ በላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ሌሎች በርካታ የምርምር ተቋማት ይገኛሉ። እነዚህ የትምህርትና የምርምር ተቋማት ግን ለአገር ግንባታ የሚፈለገውን ያክል አስተዋፅኦ እያደረጉ አለመሆኑን በጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶክተር የሺጥላ ወንድምነህ እንደሚሉት፤ በአገሪቱ ያሉት የትምህርትና የምርምር ሥራዎች በአገር ግንባታላይ ምንም ዓይነት ለውጥ አላመጡም። ለዚህ ደግሞ አገራችን አሁን ያለችበት ነባራዊ ሁኔታ ማሳያ ነው። የግብርናው አለመለወጥ፣ የከተሞች ዕድገት ተመጣጣኝ አለመሆን፣ የርስበርስ የባህል ልውውጥ ደካማ መሆን እንዲሁም የማህበራዊ እንቅስቃሴ መዳከም ዋና ዋና የችግሮቹ ማሳዎች ናቸው።
ችግሮቹን ለመፍታትም በገጠርና በከተሞች የሚገኙ ምሁራን በቂ ክህሎት አለመያዝ፣ በምርምር ሥራ ውጤታማ የሆነ ሰው አለመኖር እና በአገሪቱ ያለው ደካማ የትምህርት መዋቅር ችግሩ እንዳይፈታ አድርገውታል። በተለይ በትላልቅ ከተሞች የሚገኙ ምሁራን በቅርበት ትምህርት የማግኘት ዕድሎች እንዳሏቸው የጠቀሱት ዶክተር የሺጥላ፤ ሆኖም አብዛኞቹ ለስልጣን ሲሉ ብሄር ላይ ባተኮረ ክርክር ጊዜያቸውን እንደሚያሳልፉ ይገልጻሉ። በአሁን ወቅት በገጠርና በከተማ የሚገኙ ምሁራንም የሃሳብ አንድነት እንደሌላቸውና በሁለቱ መካከልም የዕውቀት ልዩነት መኖሩን ነው የሚያብራሩት። የትምህርትና የዕውቀት ልዩነት መኖር የአገር ግንባታው ላይ ችግር መፍጠሩን ያመለክታሉ።
በለንደን ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶክተር ዲባባ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ የትምህርትና የምርምር ሥራዎች የተዳከሙ በመሆናቸው የአገሪቱ ህዝብ ራሱ በፈጠረው ችግር የአዕምሮ ቅኝ ግዛት ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል ይላሉ። ለዚህ ደግሞ የዴሞክራሲ እጦት፣ ነፃነት አለመኖር፣ የፍትህ መጓደል እና ፖለቲከኞች ቃላቸውን አለመጠበቅ ለአዕምሮ ቅኝ መገዛት በምክንያትነት ይጠቅሳሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ምሁራን የበኩላቸውን አስተዋፅኦ አለመወጣት፣ ያለው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ምቹ አለመሆን፣ ቀድሞ የነበሩ ታሪካዊ ሁነቶችን በአግባቡ ለትውልድ አለማስተላለፍ እና ታሪኮችን በአግባቡ አለመረዳት ለአገር ግንባታ መዳከም ዋነኛ ምክንያት ናቸው ሲሉ ዶክተር ዲባባ ያስረዳሉ። የምርምር ሥራዎች የአገር ግንባታ ላይ ያተኮሩ አለመሆናቸውና ታሪካዊ ሁነቶች ላይ እየተሠራ ባለመሆኑ ከአንድነት ይልቅ መለያየት እየተስተዋለ እንደሚገኝ ያስረዳሉ።
እንደ ዶክተር ዲባባ ገለጻ፤ ከላይ ለተቀመጡት ችግሮች መፈጠር የአገሪቱ የትምህርት አሰጣጥ ደካማ መሆን በምክንትነት ይጠቀሳል። አንድ ብሄር እንዲህ አድርጎኛል የሚል አስተሳሰብ መኖር፣ በታሪክ ትምህርት ላይ የሚቀመጡ ክስተቶች ትክክል አለመሆን እንዲሁም የአገሪቱ ምሁራን የተበላሸ ታሪክ ለማስተካከል አለመሞከር የህዝቡን አንድነት አናግቶታል። የትምህርትና የምርምር ሥራ ለማህበራዊ ሀብት ያለው ጠቀሜታ ላይ ጥናት ያደረጉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ መንግሥቱ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ በአገሪቱ በአሁን ወቅት ብሄሮች የተለያዩ እንደሆኑ የሚሰበክ በመሆኑ ማህበራዊ ግንኙነቶች ላልተዋል። ይህ ሁኔታም የአገር ግንባታው ባለበት እንዲቆም አድርጎታል። በትምህርትና በምርምር ሥራዎች የህዝብ ማህበራዊ መስተጋብሮች ከማጉላት ይልቅ ልዩነት ላይ ያጠነጠኑ መሆናቸውን ይጠቁማሉ።
በኢትዮጵያ ብሄር ማለት አንድ ነገር ለግሌ ይገባኛል የሚል ትርጉም እየተሰጠው እንደሚገኝ በመጥቀስ፤ ለዚህ ደግሞ የአመለካከት ችግር መሆኑን ይናገራሉ። በአገሪቱ ያለው የትምህርትና ስልጠና ውጤታማ አለመሆኑን አገር ግንባታው ላይ ችግር መፍጠሩን ይጠቅሳሉ። እያንዳንዱ ማህበራዊ ትስስሮች እንዳይላሉ በትምህርትና በምርምር እየታገዙ አለመሆን አሁን እየታየ ላለው ልዩነት መሰረት መሆኑን ያስገነዝባሉ። በህዝቡ ላይ የአመለካከት ለውጥ የሚያመጣ የምርምር ሥራ እንደሚያስፈልግ ያመለክታሉ። በኢትዮጵያ የአገር ግንባታ ተጀምሮበታል የሚባለው ጊዜ አከራካሪ ጉዳይ ነው። የአገር ግንባታ የተጀመረው በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን ነው የሚሉ ምሁራን አሉ። የተወሰኑ ምሁራን ደግሞ የአገር ግንባታ የተጀመረው በአፄ ምንሊክ ዘመነ መንግሥት ነው የሚል አስተያየት ይሰጣሉ።
የተቀሩት ደግሞ በኢትዮጵያ የአገር ግንባታ የተጀመረው በ20ኛው ክፍለዘመን ነው ብለው ይከራከራሉ። በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት አንድ ቋንቋ፣ ሃይማኖትና ባህል እንዲኖር ተደርጎ የአገር ግንባታ ተጀምሯል። በደርግ ዘመን ደግሞ የተሞከረው የአገር ግንባታ ውጤት አላመጣም ነበር። በኢህአዴግ ደግሞ የብሄሮች መብት ላይ ያተኮረ አገር ግንባታ እየተካሄደ ይገኛል። በአገሪቱ አንድ ላይ ለመኖር የማህበረሰብ አንድነት መፍጠር፣ የጋራ ተጠቃሚነት ማሳደግ፣ ለአገር ግንባታ ጠንክሮ መሥራት፣ ለአገር ጉዳይ መስዋዕት ለመሆን መዘጋጀት እንዲሁም ማንኛውም ሰው የጋራ ተጠቃሚነት እንዳለ አምኖ በመቀበል ለዚያ መሥራት እንደሚገባ ዶክተር ዲባባ ያብራራሉ። እነዚህን ጉዳዮች ለመሟላት ጠንካራ ትምህርት እና የምርምር ሥራ መሥራት ካልተቻለ የአገር ግንባታው ውጤታማ እንደማይሆን ምሁራኑ ይጠቁማሉ።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 21/2011
መርድ ክፍሉ