መገናኛ ብዙሃን ከለውጡ በፊት የታፈኑ ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ስለመንግሥት ብቻ የሚዘግቡ ይበዙ ነበር፡፡ ብዙ ጊዜ ከመንግሥት በኩል ያለው ነገር ብቻ ነበር የሚሰማው፡፡ የህዝቡን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ነቅሰው አውጥተው የሚሰማበት አግባብ አልነበረም፡፡ ይህንን የሚያደርጉ መገናኛ ብዙሃን አብዛኛው የመንግሥት ኃላፊዎች የመሳደድዕድላቸው ከፍተኛ ነበር። ከለውጡ በፊት መገናኛ ብዙሃን ተገቢውን ሚና አልተወጡም። መገናኛ ብዙሃን በህዝብና በመንግሥት መካከል እንዲሁም በህዝቦች መካከል ብሄራዊ መግባባት ከመፍጠር አንፃር ውስንነቶች ነበሩባቸው።
ከለውጡ በኋላ መገናኛ ብዙሃን ለውጥ አሳይተዋል። የመናገር መብት መከበር በጥሩ መንገድ እየሄደ ነው። ይሄ ደግሞ የህዝቡን ድምፅ ከማሰማት አንፃር ጥሩ ለውጦች አሉ። የህዝቡንም ድምፅ በተለይ የነበሩ ቅሬታዎችን እንዲሁም መስተካከል ያለባቸውን ነገሮች መገናኛ ብዙሃን አጉልተው እያሳዩ ያለበት ሁኔታ አለ። ነገር ግን ከለውጡ በኋላ መገናኛ ብዙሃን ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች አሉ። መገኛኛ ብዙሃን የተቀመጠላቸውን የስነምግባር መርህ ተከትለው በተለይ ህዝቦችን ከማቀራረብ በኩል ክፍተቶች አሉ። ብዙ ጊዜ የአንድ ወገን ጉዳይ ብቻ የማቅረብ ነገሮች ይስተዋላሉ። በአገሪቱ ከብዝሐነት ጋር ተያይዞ እና ከዴሞክራሲ ዕድገት አንፃር ሙያ ኃላፊነትን ባልተከተለ መልኩ የሚቀርቡ ዘገባዎች አሉ።
መገናኛ ብዙሃን የህዝቡ ዓይንና ጆሮ ናቸው። በአገሪቱ ካለው ዝቅተኛ የዴሞክራሲ ዕድገት እና የልማት እንቅስቃሴው ይሄ ነው የሚባል ደረጃ አልተደረሰም። መገናኛ ብዙሃን መንግሥትን መተቸት ብቻ ሳይሆን መንግሥት አቅጣጫ ማሳየት እና ህዝቡን አቅጣጫ ማሳየት አለባቸው። ምክንያቱም ሁልጊዜ መንግሥት መጠየቅ ብቻ ሳይሆን ህዝቡ ምን ማድረግ እንዳለበት ማስተማር ከመገናኛ ብዙሃን በቀጣይ ይጠበቃል። ህዝቡን ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ ከመምራት አንፃር ኃላፊነት በሚሰማቸው መልኩ መገናኛ ብዙሃኑ እየተቃኙ የዴሞክራሲው ዕድገት የአገሪቱ ዕድገት ብሎም እንዲመጣ መሥራት አለባቸው።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 21/2011