አራት ኪሎ ጆሊ ባር ፊት ለፊት በርካታ የህትመት ውጤቶች ለሽያጭ ከሚቀርቡባቸው አካባቢዎች አንዱ ነው። በአካባቢው አልፎ ሂያጁም ሆነ ሥራ ፈላጊው በዚህ ስፍራ የሚሸጡ ጋዜጦችና መፅሔቶችን ሳያገላብጥ ማለፍ አይሆንለትም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ አካባቢው ላይ የሚሸጡ የህትመት ውጤቶች ቁጥር ጨምሯል። በዚሁ አካባቢ ጋዜጣ በማንበብ ላይ ያገኘኋቸው አቶ የሻውል አባቡ የጋዜጦቹ ቋሚ ተጠቃሚ ናቸው።
ከመንግሥት መስርያ ቤት ጡረታ ከወጡ ሦስት ዓመታት እንዳለፋቸው የሚናገሩት አቶ የሻውል አሁን አብዛኛውን ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት ጋዜጣ በማንበብናሚዲያ በመከታል እንደሆነም ይናገራሉ። እንደ አቶ የሻውል ገለጻ በአገራችን የተፈጠረውን የፖለቲካ ለውጥ ተከትሎ በአገራችን የተጀመሩት አዳዲስ የህትመት ውጤቶች የተሻለ የህትመት ውጤቶች አማራጭ እዲኖረን አድርጓል። በዚህም በተለይ በወቅታዊው አገራችን ጉዳይ የተለያዩ ጎኖችን እንድንመለከት ዕድል ፈጥሮልናል ይላሉ።
አቶ የሻውል እንደሚሉት በ1980ዎቹ በአገራችን የሚዲያ ታሪክ ትልቅ እመርታ የታየበት ነበር። እሳቸውም በዚያን ወቅት የነበሩ የተለያዩ የህትመት ውጤቶችን ይከታተሉ እንደነበር ያስታውሳሉ። በዚህም የአገራቸውን ነባራዊ ሁኔታ በሰፊው እንዲገነዘቡ ዕድል ፈጥሮላቸዋል። ያም ሆኖ ግን በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ “የስሜታዊነት ሚዲያ የተስፋፋበት” በማለት ይገልጹታል። በወቅቱ አብዛኛው ጋዜጣ ሲታተም የነበረው ገንዘብ ለማግኘት ወይም የራስን የፖለቲካ ፍላጎት ለማንፀባረቅ እንጂ ለህዝብ ትክክለኛ መረጃ ለመስጠት እንዳልነበረም በትዝብት ያስታውሳሉ።
ለዚህም በአንድ ወቅት አንድ ስሙን የዘነጉት ጋዜጣ በፊት ገፁ ላይ ‘መንግሥቱ ኃይለማያም ለፍርድ ቀረቡ’ የሚል ዜና ይዞ መውጣቱንና ጋዜጣውንም በርካታ ሰዎች ሲቀባበሉት እንደነበር ያስታውሳሉ። በተለይ በወቅቱ የደርግ ስሜት ገና ከአብዛኛው ልብ ውስጥ ያልወጣ በመሆኑ ይህ ዜና ለብዙ ሰዎች ስሜት ኮርኳሪ እንደነበርና በዚህም የተነሳ ሰዎች ጋዜጣው ላይ ሲሻሙ እንደነበርም ያስታውሳሉ። ሆኖም ዜናው በዟሪ ገፁ መጨረሻ ላይ “ውድ ደንበኞቻችን ይህ ዜና የደረሰን የአፕሪል ዘፉል ዕለት ነው” በሚል መልሰው እነሱም አንባቢያቸው ላይ “አፕሪል ዘፉል” እንደተጫወቱበት በቀልድ መልኩ ያስታውሳሉ። ከዚህም ባሻገር በወቅቱ የነበረውን የፖለቲካ ሁኔታ በማራገብና ኃላፊነት በጎደለው መልኩ የርስ በርስ ግጭትን ለመፍጠር የሚደረጉ ጥረቶች እንደነበሩም ያስታውሳሉ። እርሳቸው ግን ሚዛናዊ በሆነ ሁኔታ ሁሉንም ጋዜጣ በማንበብ ሚዛናዊ እይታ እንደሚይዙ ነው ያጫወቱኝ።
አራት ኪሎ ጋዜጣ በመሸጥ ላይ ያገኘነው ወጣት ዘነበ ሙላቱ በበኩሉ እንደሚለው አሁን አሁን የጋዜጣና የመፅሔት ገበያ እየተሻሻለ መጥቷል። በተለይ ለውጡን ተከትሎ አዳዲስ ጋዜጦችና መፅሔቶች ወደ ገበያ በመግባታቸውየአንባቢውን ፍላጎት ለማሟላት እና አማራጭ ሃሳቦችን ለማቅረብ ትልቅ በር ተከፍቷል። ከዚህ በፊት የነበሩት ጋዜጦችና መፅሔቶች አብዛኞቹ የመንግሥት እንደነበሩ የሚያስታውሰው ወጣት ዘነበ አሁን ግን የግል ጋዜጦችና መፅሔቶች በአማራጭነት መምጣታቸው የአንባቢውን ቁጥር እንደጨመረውም ይናገራል። አሁን ባለው ሁኔታም በህትመት ገበያው ላይ የተሻለ መነቃቃት መፈጠሩን ነው የሚናገረው።
በ2010 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሲቪል ምህንድስና መመረቁን የነገረን ወጣት አለማየሁ እንዳለ ግን አሁንም ቢሆን በገበያው ላይ ያሉ የህትመት ውጤቶች የህብረተሰቡን ፍላጎት የሚያረኩ አለመሆናቸውን ይናገራል። እንደ ወጣት አለማየሁ ገለጻ አብዛኛው ሰው የሚያነበው የሥራ ማስታወቂያዎችን ነው። እሱም ቢሆን ጥቂት የፊት ለፊት ገፅ ላይ የሚወጡ ዜናዎችን ከማንበብ የዘለለ ጋዜጣውን በሙሉ የማንበብ ፍላጎት የለውም። ለዚህ ደግሞ የጋዜጦቹ የፅሑፍ አቀራረብ ሚዛናዊ ባለመሆኑ እንደሆነ ይናገራል። ወጣት አለማየሁ “እኔ የምመርጠው በተቻለ መጠን ሁሉንም አስተሳሰብ ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ያቀርባሉ ብዬ የማምንባቸውን ጋዜጦች ነው” ሲልም የራሱ ምርጫ እንዳለው ይናገራል። በአገራችን ያሉት ጋዜጦች ነባራዊ ሁኔታ ግን ከዚህ የተለየ እንደሆነ ነው የሚያምነው።
በዚህም መሰረት የመንግሥት ጋዜጦች በፌስ ቡክና በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች የሚራገቡትን ለመዘገብ አመድፈራቸውና የግሎቹ ደግሞ ፈጽሞ በጎ ነገር ማውራት አለመፈለጋቸው አሁንም ከህትመት ሚዲያው ላይ ያልተነቀለ ሰንኮፍ ነው ሲል አክሏል። ስለዚህ “አሁንም ቢሆን በመረጃ የተደገፈና አገራችንን ለመለወጥ የሚያስችል ተጽዕኖ ፈጣሪ ሚዲያ ብዙም የለም” ሲል ጉድለት መኖሩን ይናገራል። እነዚህን ሃሳቦች በአዕምሮዬ ይዤ ወደ ፒያሳ አቀናሁ። ከሚኒልክ አደባባይ አጠገብ የተለያዩ ጋዜጦችን የሚሸጡ የጋዜጣ አዟሪዎችን ገበያ እንዴት ነው? ስል ጠየኩ። ወጣት ደሳለኝ ሁንዴ በአካባቢው ጋዜጣ በመሸጥ የሚተዳደር ወጣት ነው።
እሱ እንደሚለው ለውጡን ተከትሎ በአገራችን የጋዜጣ ገበያ በመጠኑ መሻሻል አሳይቷል። በተለይ ከቅርብ ወራት ወዲህ ቀደም ሲል ተዘግተው የነበሩ የህትመት ውጤቶች ጭምር በአዲስ መልኩ በመከፈታቸው አዳዲስ አንባቢዎችም እየመጡ ነው። ይህ ደግሞ የህትመት ገበያው ላይ የራሱ ጠቀሜታ ይኖረዋል። ያም ሆኖ ግን አሁንም ቢሆን የማንበብ ባህላችን ገና አነስተኛ መሆኑን ነው ወጣት ደሳለኝ የሚገልጸው። አብዛኛው አንባቢ የማስታወቂያ ደንበኛ ነው የሚለው ወጣት ደሳለኝ በጋዜጣ የሚወጡ ጥሑፎችን በጥልቀት የሚያነቡት ጥቂት ሰዎች እንደሆኑና እነሱም የሚታወቁ ቋሚ ደንበኞች መሆናቸውን ይናገራል። አብዛኛውን ጊዜ ለንባብ የሚመጡትም የመንግሥት ሠራተኞችና በጡረታ ላይ የሚገኙ አዛውንቶች ሲሆኑ ከሴቶች ይልቅም ወንዶች ቋሚ ደንበኞቻቸው እንደሆኑ ይናገራል። የጋዜጣ ገበያ ተለዋዋጭ እንደሆነ የሚናገረው ሌላው የጋዜጣ ሻጭ አቶ ወንድወሰን ክፍሌ በተለይ በፖለቲካው ላይ ያለው ሁኔታ ውጥረት ሲበዛበት የጋዜጦች አንባቢ ቁጥር እደሚጨምርም ይናገራል።
አብዛኛው አንባቢ ከሚዛናዊ ዘገባ ይልቅ ስሜታዊነት እና የሚጮሁ ርዕሰ ጉዳዮችን መርጦ እንደሚያነብም አቶ ወንድወሰን ይናገራል። ያም ሆኖ ግን በተለይ ወጣቶችና ተማሪዎች ጋዜጦችን የማንበብ ባህላቸው አነስተኛ እንደሆነ ከልምድ መገንዘቡን በመናገርም ይህም መስተካከል እዳለበት ይጠቁማል። በአገራችን የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ትልቅ ተሳትፎ ያለው ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ሆኖ ሳለ ሚዲያን የመከታተል ባህሉ አነስተኛ ከሆነ ሚዛናዊና ምክንያታዊ አስተሳሰቦችን ለማራመድ የሚቸግር በመሆኑ ሊታስብበት ይገባል ሲል አስተያየቱን ቋጭቷል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 21/2011
ወርቁ ማሩ