የፋሽን ዲዛይን አሁን አሁን በስፋት እየተዋወቀ የመጣ ዘርፍ ነው። በተለይም በሀገር ውስጥ በሚመረቱ የጨርቃጨርቅ ምርቶች፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች እንዲሁም የእደጥበብ ውጤቶችን በመጠቀም እጅግ ውብና ማራኪ በሆኑ ዲዛይኖች የተለያዩ አልባሳት ይመረታሉ።
እነዚህ አልባሳት ታድያ በቀደመው ጊዜ ለአልባሳት ሲውሉ እምብዛም አይስተዋሉም ነበር። አሁን ላይ ግን በተለይም የቆዳ ምርቶች ለፋሽን ኢንዱስትሪው ድምቀት ከመሆን ባለፈ በሥራ ዕድል ፈጠራና በውጭ ምንዛሪ ግኝት ጉልህ ድርሻ እያበረከቱ ይገኛሉ። ከሰሞኑ 13ኛው የመላው አፍሪካ አለም አቀፍ የቆዳ ንግድ ትርዒት በሚሊኒየም አዳራሽ ተካሂዶ እንደነበር ይታወሳል።
የዝግጅት ክፍላችንም ይህንኑ ትርዒት ለመታደም በቦታው በተገኘበት ወቅት እጅግ ውብ የሆኑ የእጅ ሥራዎች በቆዳ ላይ አርፈው ተመልክተናል። ከመግቢያ በር ጀምሮ ወደ ውስጥ ስንዘልቅ አይንን አፍዝዘው የሚያስቀሩ በአማረ ዲዛይን የተሰሩ የቆዳ ውጤቶች አይተናል። ከግራ ወደ ቀኝ በማለት በአግራሞት ካስተዋልናቸው የቆዳ ምርቶች በተጨማሪ በአዳራሹ የፋሽን ትርዒት የሚያሳዩ ሞዴሎች ቀልብ ይስቡ ነበር።
ሞዴሎቹ በተለያየ ቀለምና ዲዛይን ከቆዳ የተሰሩ አልበሳት እንዲሁም ጫማ ተጫምተዋል። አልባሳቱም ሆነ ጫማዎቹ በሞዴሎች ሰውነት ላይ ሲታዩ ቀልብ የሚስቡ ናቸው። በቃላት የማይገለጽ ውበት ያላቸው እነዚህ የቆዳ ውጤቶች በአገር ልጆች ተሰሩ ለማለት ይከብዳል። ይሁንና ዲዛይነሮቹ ያማረ ሥራቸውን ይዘው ቀርበዋል።
የፋሽን ትርዒቱን ካዘጋጁት አካላት መካከል የፋሽን ትርዒት አቅራቢዋ ማህሌት ተክለማርያም አንዷ ናት። ማህሌት የፋሽን ትርዒት በማዘጋጀት ረጅም ልምድ አላት። በዚህ በመላው አፍሪካ የቆዳ ኢግዚቢሽን ላይ ያሉትን ምርቶች በሞዴሎች አማካይነት ማቅረብ እንደቻለች ገልጻለች።
እሷ እንዳለችው የፋሽን ትርዒት የቆዳ ምርቶችን ፋሽን ለማስተዋወቅ የቀረበ ነው። በዕለቱ ከጠዋት ጀምሮ ሞዴሎችን በማልበስ በፋሽን ትርዒት መልኩ አልባሳትን እንዲያሳዩ በማድረግ የቆዳ ምርቶችን በደንብ ማስተዋወቃቸውን ትናገራለች። ይህ ደግሞ የቆዳ ምርቶችን ኤክስፖርት ለማድረግ ትልቅ ሚና አለው።
በርካታ የሀገር ውስጥ አምራቾች በልብስ፣ በጫማና በቦርሳ ብዙ የተለያዩ ፋሽኖች ዲዛይን ያደርጋሉ የምትለው ማህሌት፤ በፋሽን ትርዒቱም ዘመነ አሞር ፣ ሜሮን አዲስ አበባ፣ ሩት ስታይል፣ ኬሬዥ፣ ታፋ እና ሌሎችም አቅራቢዎች ተሳታፊ መሆናቸው ገልጻለች። ኦስሞን ዲዛይን ደግሞ ለፋሽን ትርዒቱ የሚሆኑ ሙሉ ልብሶችን ከጫማዎቹ ጋር ዲዛይን በማድረግ ማቅረቡን ትናገራለች።
ይህ የፋሽን ትርዒት የተዘጋጀበት ዋና ዓላማ ምርቶቹን ለማስተዋወቅ እንደሆነ የምትገልጸው ማህሌት፤ የቆዳ ኢንዱስትሪው እንዲበረታታ የሀገር ውስጥ ሸማቾች የቆዳ ምርቶች መሸመት እንዳለበቸው ትናግራለች። ምርቶቹ ጥራታቸውን ጠብቀው የተዘጋጁ መሆናቸውን ጠቅሳ፣ ምርቶቹ በብዛት ወደ ውጪ ሀገራት ኤክስፖርት የሚደረጉ ቢሆኑም በሀገር ውስጥ በርካታ የመግዛት አቅም ያለው ሰው ምርቶቹን ገዝቶ መጠቀም አለበት ብዬ አምናለሁ ትላለች።
‹‹ሀብ ኦፍ አፍሪካ›› በሚል በየዓመቱ የሚዘጋጅ የፋሽን ትርዒት ስለመኖሩ ያነሳችው ማህሌት፤ አሁን ላይ የፋሽን ኢንደስትሪው ትርጉም ያለው ለውጥ እያሳየ እንደሆነ ነው የገለጸችው። የፋሽን ትርዒት በፋሽን ኢንዱስትሪው ሆነ በሞዴሎች ላይ ያለው አመለካከት ለመለወጥ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አንስታ፤ ልብሱ ተለብሶ ሲቀርብ ከሚሰጠው ደስታ ባሻገር ትልቅ ገቢ የሚያስገኝ ኢንዱስትሪ መሆኑንም ነው የገለጸችው።
አሁን ላይ የቆዳው ዘርፍ ማህበራት ይህንን ትርዒት በማዘጋጀት ከውጭ ሀገር ካሉ አካላት ጋር የልምድ ልውውጥ እንዲካሄድ ማድረጋቸው በሀገር ውስጥ ማምረት እንደሚቻልም ያሳዩበት አንዱ መንገድ ነው። በቀጣይም ዘርፉን ይበልጥ ለማሳደግ እንዲህ ያሉ ዝግጅቶችን በማድረግ ማስተዋወቅና ማበረታታት ይገባልም ብላለች ። ሰዓሊና የፋሽን ዲዛይነር አቶ ኦስማን መሐመድ በበኩሉ፤ በፋሽን ትርዒቱ አለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ፣ ቡድን ባለው የልብስ አሠራርና ፈጠራ የታከለባቸው ጫማዎችና አልባሳት ዲዛይን አድርጎ ማቅረቡን ይናገራል።
የፋሽን ዲዛይን ሥራዎች ከሌላው ለየት ያሉ መሆናቸውን ሲገልጽ ‹‹ዲዛይኑን ስሰራ የተመሰጥኩበት፣ መሠረት ከሆንኩባቸው ነገሮች በመነሳት ታሪክ በመስጠት ነው የምሰራው። እያንዳንዱ ልብስ ታሪክ አለው፤ እንደታሪካቸው ሁሉ ቀለማቸው ወቅቱን የጠበቀ ሆኖ ይሰራል። ልዩ የሚያደርጋቸው ደግሞ ሙሉ ማሽን ሳይነካቸው በእጅ ብቻ የሚሰሩ መሆናቸው ነው፤ በተለይ ጫማዎቹ›› ይላል ።
ሙያውን ወዶትና ከውስጡ በመነሳት የሚሰራው ስለሆነ በብዙ ሰዎች ዘንድ እንደሚወደድለትም ይናገራል። በመሆኑም በፋሽን ትርዒቱ ላይ አልባሳቱም ሆኑ ጫማዎቹን ያዩትም ሆነ ለብሰው ያሳዩት ይማረኩበታል። አልባሳቱም ሆነ ጫማዎቹ እራሳቸው የሚያወሩ፣ አይነት ታሪክ ያላቸው እንደሆኑም ተናግሯል።
አቶ ኦስማን እንደሚለው፤ የሥራዎቹ ለውጭ ገበያ ቅርብ የሆኑ አይነት ዲዛይን ያላቸው ናቸው። ውጭ ሀገር ፈጠራ የተሟላበት ነገር የማድነቁም ሆነ ባለቤት የመሆኑ እድል የበለጠ ነው። እኛ ጋ ግን እይታው በራሱ አዲስ ነው። ልብሶች ላይ ያለው እይታ የሚያነቃቃ ነው፤ ግድብ ያለ ስሜት የለውም፤ ደስታና ነፃነትን ያሳያል ።
ከዚህ ቀደም በተለያዩ ዓለም አገራት በፋሽን ዲዛይን ለየት ያለው ፈጠራ የታከለበት ተፅእኖ ፈጣሪ ዲዛይነሮች በመስራት መሸለሙን የሚናገረው ኦስማን፤ በፋሽኑ ተፅእኖ መፍጠር ማለት አንድ የሚሰራ ልብስ የራሱ የሆነ ታሪክ ሊኖረውና የሚታዩ ነገሮች ሁሉ ወደ ሀሳብ ተቀይረው ውጤት ማምጣቱ ማሳየት ሲቻል ነው ይላል። ከዚህ በተጨማሪ አነጋጋሪ የሆነ ሥራን ሰርቶ ወጣ ብሎ ማየትን፣ ሰፋ አድርጎ ማሰብን ድፍረትን የሚጠይቅ መሆኑን በመግለጽ፤ በዚህ ሥራ ላይ በቆዳ ብዙ ነገር መፍጠር እንደሚቻልም ለማንፀባረቅ እንደሞከረ ነው ያስረዳው።
አቶ ኦስማን የፋሽን ዲዛይኑ እንዲህ አይነት መድረክ ሲፈጠርለት የገበያ ትስስር ከመፍጠር በዘለለ አዲስ ነገር በየጊዜው የማስተዋወቅ በየዓመቱ አእምሮአችንን መፍጠር የሚችለውን ሥራ ጥግ ድረስ መጠቀም እንዲችል ያግዛል ይላል። ይህ ማለት ደግሞ የሥራ እድሉንም የሚጨምርና የቆዳ ኢንዱስትሪ ላይ ሲባክን የነበረውን ያስቀራል። ታይቶ ያልታወቀው ነገሮች እንዲታዩና የልምድ ልውውጥ እንዲኖርም እድል ይፈጥራል ሲል ያብራራል።
‹‹ከውጪ የሚገቡ ( ኢንፖርት) የተደረጉ ልብሶችም ሆኑ ጫማዎችን መጠቀም ሁልጊዜ ፍላጎታች ነው›› የሚለው ኦስማን ፤ በፋሽን ዲዛይን ኢንዱስትሪው ከተለመደ ውጭ የሆነ የተሻለ ሥራ እንዲሠራ እና ኤክስፖርቱ እንዲሰፋ ለማድረግ እንዲህ አይነት መድረክ ትልቅ እድል ይፈጥራል በማለት ሀሳቡን አጠቃሏል። እንደዚህ አይነት ኤግዚቢሽኖች ደግሞ እርስ በእርስ በማስተዋወቅ አንዱ ከአንዱ ልምድ እንዲቀስም እድሉን ይፈጥራል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 16 ቀን 2015 ዓ.ም