ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት በአገራችን የነበረው የፕሬስ ነፃነት ከምልክት ያለፈ አልነበረም።የወጡ ህጎችም ቢሆኑ ፕሬስ ነፃነቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ነበሩ።ኢህአዴግ በገባበት በ1983 ዓ.ም አካባቢ በአንጻራዊነት ሚዲያው በነፃነት እንዲንቀሳቀስ ተደርጎ ነበር።
ከተወሰነ ቆይታ በኋላ ግን የፕሬስ ነፃነትን የሚጋፉ አሠራሮች ተከስተው የፕሬስ ነፃነት ብቻ ሳይሆን ፕሬሱ ራሱ የለም በሚባል ደረጃ ላይ ሆኖ ቆይቷል። የፕሬስ ነፃነት ህግም ከወረቀት በዘለለ በተግባር ሳይተገበር ቀርቷል። እናም የፕሬስ ነፃነት በሀገራችን መጥፎ ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር ማለት ይቻላል። በተለይም በመንግሥት በኩል ያሉ ችግሮችን የሚያነሱ ሚዲያዎች በከፍተኛ ጫና ስር ሆነው ነበር ሥራቸውን የሚሠሩት።
ምህዳሩን ከማጥበብ ባሻገር ጋዜጠኞች በጻፉት ፅሑፍ፣ በሰጡት አስተያየት እንዲሁም ሃሳብን በነፃ የመግለጽ ህገ መንግሥታዊ መብት በመጠቀም የተለያዩ ፅሑፎችን በሚያወጡበት ወቅት በሥራቸው ብቻ እየተያዙ ወደ አስር ቤት የሚጣሉበት ጊዜ ነበር።በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ ፕሬሱን በማፈን በዓለም አቀፍ ደረጃም በቀዳሚነት ከሚጠሩ አገራት ተመድባ ቆይታለች።
በ2010 ዓ.ም መንግሥት ተቀየረ ማለት ባንችልም፤ በዚያው በኢህአዴግ ውስጥ በተፈጠረ ተሃድሶ የእነዶክተር አብይ አመራር ወደ ስልጣን ሲመጣ የመጀመሪያ ዕርምጃ የነበረው አገሪቱ የፕሬስ ምህዳር እንዲሰፋ ማድረግ ነው።ምክንያቱም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ ማህበረሱ እንዲሁም በአንዳንድ ረጂ ተቋማት ጥርስ ውስጥ የገባቸው ፕሬስን በማፈን ስለነበር ይህንን ከማስቀረት አኳያ እንዲሁም የዴሞክራሲ ምሕዳሩን ለማስፋት ሲባል አንዳንድ ዕርምጃዎች ተወስደዋል።
ከእነዚህም መካከል የታሠሩ ጋዜጠኞችን መፍታት እና የተለያዩ ፕሬስን የሚመለከቱ አፋኝ ህጎችን መሻሻል የሚል ሲሁን በአሁኑ ወቅትም በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ህግ እየወጣ እንደሆነ ይታወቃል፤ ይህን እንደአንድ በጎ ጅማሬ ማየት ይቻላል።ከዚያ ባሻገር የተዘጉ ሚዲያዎች እንዲከፈቱ፣ ከአገር ውጪ የነበሩ ሚዲያዎች እና ጋዜጠኞችም አገር ውስጥ ገብተው እንዲሠሩ ፍቃድ ተስጥቷል።
ይሄ ሁሉ ጅማሮ ቢኖርም ግን አሁንም ሙሉ ነው ብለን መናገር አንችልም።አሁንም በጎን በኩል ለፕሬስ ጠል እና አፍራሽ የሆኑ ሃሳቦች ብቅ እያሉ ነው።ስለዚህ ባሳለፍነው አንድ ዓመት የተሰጠው ነፃነት በጀመረው ልክ ሊቀጥል ይገባል እንጂ አሁን እየበቀ ላላው ችግር ሚዲያውን ምክንያት እያደረጉ የማቅረብ አዝማሚያ ሊቆም ይገባዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 20 ቀን 2011 ዓ.ም