እየሱስ ክርስቶስ የአዳምን በደል ለመሻር ከሰማየ፣ ሰማያት ወርዶ ከድንግል ማርያም ተወልዶ ሰላሳሦስት ዓመታትን በምድር ሲያስተምር ኖረ። ጊዜው ሲደርስ በራሱ ፈቃድና በአይሁድ ክፋት ከፍ ያለ መከራን ሊቀበል፣ ከመስቀል ተቸንክሮ ሊሰቀል ግድ ሆነ። ሞት የማይቀርለት ዕዳ ሆኖም ለሰውልጆች ሀጢያት ሲል ራሱን አሳልፎ ሰጠ። በዕለተ ዓርብ ነፍሱ ከስጋው ተለይታ ወደ መቃብር ወረደ።
እነሆ በዚህ ቀን ከፍ ያለ ኀዘንና ለቅሶ ሆነ። ምድር ተንቀጠቀተች፣ ቀኑ ጨለመ፣ መጋረጃዎች ለሁለት ተሰነጠቁ። የክርስቶስን ሞት ያዩ ሁሉ አንገታቸውን ደፉ። በእርሱ ላይ ግን የአብ አባቱ ቃል ፈጽሞ አልተሻረም። በሦስተኛው ቀን ሞትን ድል ነስቶ፣ መቃብር ፈንቅሎ ለዓለም ሕያው ሆነ።
በሕዝበ ክርስቲያን ዘንድ የክርስቶስን ከሞት መነሳት እንደማየት የሚያሰደስት እውነት የለም። ይህ ቀንም ዕለተ ትንሳኤ ወይም ፋሲካ ተብሎ ይጠራል። ጌታ እየሱስ ክርስቶስ መከራና ስቃይ የተቀበለባቸው ቀናት ‹‹ሰሞነ ሕማማት›› ተብለው ይጠራሉ። እነዚህ ጊዜያት ‹‹ሰሞነ ከሚለው ቃል ተዋደው ሳምንቱን ወይም ስምንቱን ቀናት በማስታወስ ስድስቱን የስቃይና መከራ ቀናት የሚያመላክቱ ናቸው፡ ፡‹‹ሀመ›› የሚለው ቃል በግዕዝ ‹‹ታመመ›› የሚለውን ፍቺ ይይዛል።
እየሱስ ክርስቶስ ወደእየሩሳሌም ከገባ አንስቶ ከትንሳኤው ቀናት በፊት ያሳለፋቸው የመከራ ቀናት የመጨረሻ ሳምንት ‹‹ሰሞነ ህማማት›› ተብሎ ይጠራል። ይህ ሳምንት ክርስቶስ የበረከተ ችግርና መከራ፣ ስቃይና አበሳ የተቀበለበት ነውና ህመሙ በተለየ ሁኔታ ይታወስበታል።
የመስቀሉ ህማሞች በአስራሦስት የስቃይ መገለጫዎች ይተነተናሉ። ሳዶር፣ አላዶር፣ አዴራ፣ ዳናትና ሮዳስ በተሰኙ አምስቱ ቅንዋተ መስቀል ክርስቶስ በችንካር መሰቀሉም ይገለጥበታል። የሰሞነ ህማማት ቃል ሲፈተሽ ‹‹ሰመነ›› ማለት ሳምንት አደረገ ከሚል ትርጓሜ ያደርሳል። ይህም ከዕለተ ሆሳዕና እስከ ትንሳኤ ሌሊት ያሉትን ስምንት ቀናት የሚያመላክት ነው።
‹‹ሀመ›› ማለት ታመመ ማለት ነው። ይህም እየሱስ ክርስቶስ የሰውልጆችን ከዲያብሎስ የባርነት ግዛት ነፃ ለማውጣት በፈቃዱ የተቀበላቸውን የስቃይና መከራ ቀናት የሚያስታውስ ነው። የሰሞነ ህመማት ቀናት ሲታውሱ በተለየ ሥርዓትና ልማድ ነው። በነዚህ ቀናት ሕዝበ ክርስቲያኑ የክርስቶስን ውለታና ስቃይ የሚያስቡት በኀዘንና በለቅሶ፣ በጾምና ስግደት ይሆናል።
በሰሞነ ህማማት ጊዜ መስቀል መሳለም፣ የትከሻ ሰላምታን መለዋወጥ፣ በተለይም መሳሳም አይፈቀድም። እንዲህ ማድረጉ አይሁዶች ክርስቶስን ለመስቀል ከሰኞ አስከ አርብ ተሰባስበው የመከሩበትን፣ ‹‹እንስቀለው›› ሲሉ የተንሾካሾኩበትን፣ በክፋት የተገናኙበትን ጊዜ ያስታውሳል።
በቅዱስ መጽሐፍ እንደተጠቀሰው ይሁዳ ክርስቶስን ለጠላቶቹ አሳልፎ ለመስጠት የተጠቀመው ምልክት ትከሻውን በመሳም ነበር። ይህ ዓይነቱ ሰላምታ ፍጹም ሰላም የራቀው፣ ፍቅር ያልነበረውና በተንኮል የተዋጠ መሆኑ ይታሰባል። ይህ ወቅት ፍቅር ያልታየበት፣ ሰላም ያልወረደበት፣ መልካም ጉዳዮች ያልሆኑበት ነውና ያለአንዳች ሰላምታ ጊዜውን በማሰብ ይታወሳል።
ሰሞነ ህማማት በገባ ጊዜ ሥርዓተ ቅዳሴ አይኖርም። ማንም ሰው ቢሞት ሥርዓተ ፍታት አይደረግም። አስቀድሞ ጸሎትና ፍታቱ በየቤተክርስቲያናቱ ይካሄዳል። የሃይማኖቱ አስተምህሮ እንደሚያስረዳው በዚህ ሳምንት የሰው ልጆች ከሞት ወደ ሕይወት የተሸጋገሩበት፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን ያለፉበት ተምሳሌት ሆኖ ይጠቀሳል። በሰሞነ ህማማት ከሰኞ እስከ ዕሁድ ያሉት ቀናት የራሳቸውን ምስጢር ይዘው ተቀርጸዋል። በእያንዳንዳቸው ቀናት ላይ የሚያርፈው ምሳሌም በዚህ መልኩ ይተነተናል።
ሰኞ
በዕለተ ሰኞ፡- እየሱስ ክርስቶስ ‹‹ቤቴ የእግዚአብሔር ቤት ተብላ ትጠራለች እናንተ ግን መነገጃ አደረጋችሁት›› ሲል በስፍራው ሲነግዱ የዋሉትን ሰዎች የማስወጣቱን እውነት ይጠቁማል።
ማክሰኞ
በዕለተ ማክሰኞ፡- እየሱስ ክርስቶስ ከመሰቀሉ አስቀድሞ ለመጨረሻ ጊዜ ደቀመዛሙርቱን ሰብስቦ ያስተማረበትን ጊዜ ያስታውሳል።
ረቡዕ
ዕለተ፡- ረቡዕ አይሁድ በክርስቶስ ላይ የመከሩበት ነው። ይህ ቀን መግደላዊት ማርያም እያለቀሰች የእየሱስ ክርስቶስን እግር በሽቶ ያጠበችበት ቀን መሆኑ ይታወቃል። ከዚሁ ጋር ተያይዞም ዕለቱ የመልካም መዓዛና የዕንባ ቀን በሚል ይታሰባል።
ሐሙስ
ዕለተ፡- ሐሙስ በሌላ ስያሜው ጸሎተ ሐሙስ በሚል ይጠራል። በዚህ ቀን እየሱስ ክርስቶስ ትህትናን ለዓለም ለማስተማር ዝቅ ብሎ የሐዋርያትን እግር ያጠበበት ነው። ዕለቱን ደቀመዛሙርቱ ራት ባዘጋጁ ጊዜም ክርስቶስ አስቀድሞ ሞቱን ያውቅ ነበርና ከቀረበው ቂጣና ወይን ባርኮ ‹‹ስጋና ደሜ›› ይህ ነው ሲል የሰጣቸውን እውነት ያስታውሳል።
አርብ
ዕለተ አርብ፡- እየሱስ ክርስቶስ ስለሰው ልጆች ሐጢያትና በደል በመስቀል ተቸንክሮ በታላቅ ስቃይና ሕመም የሞት ጽዋን የተጎነጨበት ቀን ነው።
ቅዳሜ
ዕለተ፡- ቅዳሜ የእየሱስ ክርስቶስ የሞቱ ማግስት ነው። በዚህ ቀን ወደ ሲዖል ወርዶ በስፍራው ላሉት ሁሉ ሰላምን እየሰበከ ወደ ገነት ያስገባቸውን ምሳሌ ይጠቁማል።
ዕሁድ
ዕለተ፡- ዕሁድ የእየሱስ ክርስቶስን ከሞት የመነሳት ትንሳኤ ያበስራል። ይህ ቀን ክርስቶስ ከሙታን መሀል ከፈኑን ገልጦ፣ መቃብር ፈንቅሎ፣ ሞትን ድል የነሳበት ታላቅ ዕለት ነው። ይህም ቀን በሕዝበ ክርስቲያኑ ዘንድ ፋሲካ ተብሎ ይከበራል ።
በነዚህ ሰባት ሰሞነ ሕማማት የእየሱስ ክርስቶስን የጭንቅ ቀናት ለማሰብ ሕዝበ ክርስቲያን፣ ካህናትና ዲያቆናት፣ በቤተክርስቲያን አጸድ ይሰባሰባሉ። ከምግብና መጠጥ ተቆጥበውም ራሳቸውን በጾም፣ በስግደት ያደክማሉ። ውስጣቸውን በንስሀና ያነጻሉ።
በዚህ ሳምንት የእየሱስን ስቃይና መከራ በኀዘን የሚያስቡ ዜማዎች ብቻ ይደመጣሉ። ጊዜው ደስታና ጨዋታን አይፈቅድምና ‹‹ግብረ ህማም›› የተሰኘ መጽሐፍ እየተነበበ ራስን ለስግደትና ጾም ማስገዛት ግድ ነው።
በዚህ ሳምንት ከሕዝበ ክርስቲያኑ አንደበት መደመጥ ያለበት ዜማ የክርስቶስን ኀዘንና መከራ የሚያስታውስ፣ ስቃይ መከራውን የሚዘክር የንስሀ መዝሙርና የዘለሰኛ ዜማ ነው።
የዘለሰኛ መዝሙሮች በአብዛኛው ከተለመዱት ስንኞች ወጣ ያሉ ናቸው። ልብ ብሎ ላዳመጣቸው ትርጓሜያቸው በብዙ ፍቺ ይገለጻል። የዓለምን ከንቱነት፣ የሰውልጆችን ማንነት በተለየ ምስጢር ይጠቁማሉ። ፈጣሪን ለማመስገንም ቅድሚያውን ይሰጣሉ እንዲህ በማለት።
ክበር ተመስገን የኛ ጌታ፣
ከጠዋት አንስቶ እስከ ማታ።
እዛ ላይ ሆኖ ቢጠራኝ፣
ወይ እንዳልለው ድምጽ የለኝ።
ባልሰማ እንጂ ነው ዝምታዬ፣
አቤት አቤቱ ጌታዬ ።
በእሳት ዙፋን ላይ ይቀመጣል፣
በድምጹ ምድርን ያናውጣል።
ሰይፍ ይመዘዛል ከአንደበቱ፣
እንደጌታችን ማነው ብርቱ።
ገጹ እንደ ፀሐይ የሚያበራ፣
ግርማ ሞገሱ የሚያስፈራ።
የዘለሰኛ ግጥሞች በአንድ ትርጉም ብቻ አለመፈታታቸው አድማጩን በተለየ ጥበብ እንዲመራመር ያደርጋል። ለምሳሌ ቀጥሎ የቀረበው የዘለሰኛ ስንኝ የሰውን ከንቱነት፣ ድንገት ወጥቶ ከመቅረቱ፣ እንዲሁም ህማማትን ከሀሜት ጋር በማያያዝ እንዲህ ይገልጸዋል።
ይፍቱኝ አባቴ በጠዋቱ፣
ወጥቶ ቀሪ ነው ሰው በከንቱ።
ይፍቱኝ ላይል የበረረ፣
እንደታሰረ በዚያው ቀረ።
ቅዳሴ ቅኔ ማህሌቱ፣
አቤት ማማሩ አይ ውበቱ።
ሥራውም ቀሏል ከትናንቱ፣
ተጣልቻለሁ ከአባቶቼ ፣
የጾሙን መብዛት ጠልቼ።
አርባ ቀን ፆመን በነበር ፣
ምነው ማማቱ ቢቀር።
የፆም አትክልቱ፣ እልበት ሽንኩርቱ፣
እንደ ጥሬ ስጋ ምነው መበላቱ፣
እስቲ ቀንሱለት ባይሆን ለማማቱ።
ስጋ በእሳት ነበር የሚቀቀል ድሮ፣
መጥበስ ተጀምሯል በምላስ ዘንድሮ።
ዓርብና ዕሮቡን ቆጥረን ብንጾመው፣
በማማት መብላቱን ምነው አልተውነው።
በዘለሰኛ የአምላክ ቸርነት፣ የዚህ ዓለም ሕይወት ደጋግሞ ይሰበካል። የሰውልጅ ማንነትና የእግዜአብሔር ኃያልነት ይወሳል። ለፈጣሪ የሚቸር፣ ምስጋናና ክብር ሁሉ በስንኝ ተቋጥሮ፣ በዜማ ታጅቦ ይደመጣል።
ትዕግስትህ ብዙ ነውና፣
ኃያል እግዚአብሔር ገናና።
ነነዌን አይተህ የራራህ፣
በል ስማኝ ዛሬም ስጠራህ።
ሰውማ ትቷል ነገሩን፣
በአንተ ላይ ራስ መጣሉን።
መልከ ፈጣሪን የመሰለ፣
እንደሰው ፍጡር የታለ።
የእየሩሳሌም ገዳም ቄስ
አሜን ሲል ያድራል ሲቀደስ
ምን አስጨነቀው ለኛ ሰው
ዓለም በቃኝ ላለው።
አንዳንዴ በሰዎች ላይ የሚደርሰው ድንገቴ ሞት ብዙ ለሚያስብ፣ ለሚያቅደው ሁሉ ያስደነግጣል። ከምንም በላይ ግን ራስን በንስሀ አንጽቶ ላልቆየው ምዕመን ይህ ዓይነቱ አጋጣሚ የማስጠንቀቂያን መልዕክት ያስተላልፋል። የዘለሰኛ ስንኝም እንዲህ ዓይነቱን እውነት በዚህ መልክ ይገልጸዋል።
ለመኖር ስመኝ በመሬት፣
ንብረት አፍርቼ ልሰራ ቤት፣
ጥሪው ደረሰኝ በሌሊት፣
በከንቱ ቀረ ያሰብኩት።
የሰውልጅ ሲመኝ ሰፊ ርዕስት፣
እየመሰለው የማይሞት።
እልፍ የጥበብ ዘር ያለአግባብ አግብቶ፣
በአገልግል፣ በሙዳይ ስንት ቀለም ሞልቶ፣
ልቆርጠው ነው አለኝ ሳላስበው ገብቶ።
ሞት ለሰውልጆች ሁሉ የተሰጠ ግዴታ ነው። ማንም ቢሆን በምድር ኖሮ ማለፉ፣ ጊዜው ሲደርሰ መሞቱ አይቀርም። የዘለሰኛ ግጥሞችም በአብዛኛው የምድር ሕይወትንና አይቀሬውን ሞት ሳያነሳሱት አያልፉም። እየደጋገሙ እንዲህ ያወሱታል።
ሦስት ክንድ ለክቶ ሲሰጥ በየቤቱ፣
እኔን ያሳዘነኝ ሁሉም መዘጋቱ።
ቋሚ የሚሆን ጠፋ ሰው፣
እየወሰደ ጨረሰው።
እየጣለው ሄደ እያየው አለፈ፣
አቤት ስንቱ ቀለም በከንቱ ረገፈ።
ካሰበውም ሳይደርስ በከንቱ እየቀረ፣
ወጥኖ ወጥኖ ስንቱ ተቸገረ።
እነዛ ቢሄዱ ቀድመው ከፊታችሁ፣
እናንተም ከኋላ ትከተላላችሁ።
በዘለሰኛ ስንኝ መሀል ምንጊዜም ፈጣሪን ማሰብና ማወደስ የተለመደ ነው። በተለይ ደግሞ ከሞት በኋላ ለሚኖረው ሰማያዊ ሕይወት ፈጣሪን ‹‹ከሀጢያት አንጻኝ፣ ከመንግሥትህ አስበኝ፣ ይቅር በለኝ›› ብሎ መማጸኑ አይቀርም። ይህ በሰውልጆች ማንነት ውስጥ የተቀረጸ እውነት ታዲያ በዘለሰኛው ቅኔ እንዲህ ተብሎ ይገለጻል።
አምላኬ አምላኬ እያልኩህ፣
እኔስ በመጮህ ጠራሁህ፣
ከሲዖል ስቃይ ጠብቀኝ፣
በቀኝህ ልሁን አስበኝ።
በአብዛኛው የሰውልጅ በምድር ሲኖር ከነፍሱ ይልቅ ለስጋው ያደላል። ይህ የዓለም እውነታም እስከዛሬ የኖረና ወደፊትም የማይቀር ነው። እንዲህ ዓይነቱ ሀቅ ሲገለጽ ደግሞ ምስጢራቱ ሁሉ ከማይቀረው ሞትና ከወዲያኛው ዓለም እየተናበበ እንዲህ ይገለጻል። በመስንቆው ዘለስኛ።
አምላክ ግብር ጠርቶ ደግሶ ሲያበላ፣
ትንሹም ትልቁም ለስጋው አደላ።
የልደቱን በሬ ማነው ያረደው፣
መረረኝ እንደሬት ገና ሳልቀምሰው፣
መብላቴ የማይቀር ነው አሁንስ ባየው፣
ባገር የለም አሉ ያ ሞት ያልነካው።
የሰለሰኛ መዝሙሮች ጠንካራ መልዕክቶች አላቸው፣ የዓለም እውነታን ገልጠው ሰውን ከራሱ፣ ሰውን ከአምላኩ ያስታርቃሉ። መልካም ምግባር እንዲኖር፣ መተሳሰብ እንዲለመድ ይጠቁማሉ። ፍቅርን እየሰበኩ፣ መከባበር፣ መዋደድ እንዲኖር ያስተምራሉ። በሚከተለው ሁኔታ።
እርስ በርሳችን እንፋቀር፣
ልጆች እንድንሆን ለእግዚአብሔር።
ከሁሉ በላይ ፍቅር ይጸናል፣
ጌታም በቃሉ እንዲህ ብሏል።
ከአንድ መንፈስ ተወልደን፣
ከአንዱ አምላክ ተከፍለን።
ተፈጥረን ሳለ ከአንድ አባት፣
ከወዴት መጣ መለያየት።
የመዲናና ዘለሰኛ ግጥሞች መልካም ድምጽን በተቸራቸው አንደበት፤ በመሰንቆ ታጅበው ሲደመጡ ልብን ያረካሉ፣ መንፈስን ይማርካሉ። በአብዛኛው የሚያሳድሩት ስሜትም ከተለመደው ዓለማዊ ሙዚቃና ዘፈን የሚያርቅ ነው። ብዙዎች እንደሚሉት የዘለሰኛ ዜማዎች የተለየ ኃይልና ጉልበት አላቸው። ሰው ከራሱ ጋር እንዲመክር፣ ከፈጣሪው እንዲገናኝ፣ የዓለምን እውነታ መርምሮ እንዲፈትሽ ያደርጋሉ።
እነሆ ዛሬ ዕለተ ሐሙስ ነው። ይህ ቀን ደግሞ ‹‹ጸሎተ ሐሙስ›› ተብሎ ይጠራል። በዚህ ቀን እየሱስ ክርስቶስ ትህትናን ለዓለም ለማስተማር ዝቅ ብሎ የሐዋርያትን እግር አጥቧል። ደቀመዛሙርቱ ራት ባዘጋጁ ጊዜም ከቀረበው ቂጣና ወይን ባርኮ ‹‹ስጋና ደሜ›› ይህ ነው ሲል የሰጣቸው ቀን መታሰቢያ ነው።
ቀኑ እስራኤላውያን ከግብጽ ባርነት በችኮላ መውጣታቸውን ለማሰብ ሲባል የሚታወስ የእስራኤላውያን ትውፊት ነው። ይህ ትውፊት እስራኤላውያን በችኮላ በወጡ ጊዜ የመንገዳቸው ስንቅ በወጉ ያልበሰለ ቂጣ፣ ንፍሮና መሰል ሆድ መሙያዎች እንደነበሩ ያስታውሳል።
ዕለቱ በተለይ በአገራችን ባሉ የኦርቶዶክስ ዕምነት ተከታዮች ዘንድ በተለየ ሥርዓት ይታወሳል። የዛሬው ቀን ዕለተ -ጉልባን ነው። በየቤቱ ስንዴና ባቄላ ተቀቅሎ ይበላል። ጉልባኑ ጨው በርከት እንዲልበት ይደረጋል። ጨው በባህሪው ውሀ ያስጠጣል። የዚህ ምሳሌም ክርስቶስ ሲሰቀል በውሀ ጥም መሰቃየቱን ለማሰብ ነው።
ለጉልባኑ የሚቀቀለው ባቄላ ቅርፊቱ ተልጦ ይከካል። የዚህ ምሳሌም አይሁዳውያን የክርስቶስን ልብስ አውልቀው ያንገላቱትን እውነት ለማሰብ ሲባል ነው። ከጸሎተ ሐሙስ ማግስት ስቅለት በዓል ነው። ይህ ቀን እንዳለፈም ‹‹ቅዳም ሹር›› ይከተላል። እየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ተከንችሮ ሞትን ድል የነሳበት፣ መቃብር ፈንቅሎ ህያው የሆነበት ትንሳኤም በዕለተ ዕሁድ ይበሰራል። ይህ ቀን በመላው የክርስትና ዕምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት የሚከበረው ታላቁ የፋሲካ አውደ ዓመት ነው። መልካም የትንሳኤ በዓልን ተመኘን።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 5/2015